1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ፕሮፈሰር ዕደማርያም ጸጋ እና አበርክቶቻቸው

ረቡዕ፣ ጥር 16 2010

በኢትዮጵያ የህክምና ትምህርት እንዲያድግ እና አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል ፕሮፈሰር ዕደማርያም ጸጋ ይጠቀሳሉ፡፡ በታህሳስ መጨረሻ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፕሮፌሰር ዕደማርያም የህክምና ትምህርት ክፍልን ከመምራት፣ በመምህርነት ከማገልገል በተጨማሪም ዕውቅ ተመራማሪም ነበሩ፡፡

https://p.dw.com/p/2rStR
Edemariam Tsega Professor Äthiopien
ምስል AAU/School of Medicine

የኢትዮጵያ የህክምና ትምህርት ባለውለታ

ጊዜው በ1960ዎቹ ነው፡፡ በካናዳ እና በእንግሊዝ የህክምና ትምህርቱን የተከታተለው ወጣቱ ዕደማርያም ጸጋ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰበት ወቅት፡፡ ያኔ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቶሎ ወደ ሀገራቸው ገብተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚፈልጉት የዘመኑ ወጣቶች ሁሉ ዕደማርያምም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ትልቅ ርዕይ ሰንቆ ነበር፡፡ በ1950ዎቹ አጋማሽ በተቋቋመው በያኔው የህክምና ትምህርት ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውን ባለሙያዎች እና መምህራንን ቁጥር ለማብዛት ታጥቆ ተነሳ፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገውን የመጀመሪያ እርካብም በአጭር ጊዜ ተቆናጠጠ፡፡ የሚያስተምርበት የውስጥ ደዌ ትምህርት ክፍልን ኃላፊነት ጠቀለለ፡፡

የትምህርት ክፍሉን ለመለወጥ ብዙ የታተረው ወጣቱ ዕደማርያም በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ «በጭራሽ የማይታሰብ» የተባለለትን ውጥን ይዞ ብቅ አለ፡፡ እቅዱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚያን ቀደም በየትኛውም የትምህርት ዘርፍ ያልተተገበረውን የድህረ ምረቃ (postgraduate) ትምህርት መጀመር ነበር፡፡ ከያኔው የዕደማርያም ተማሪዎች አንዱ የነበሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬ በዚያን ወቅት የነበሩትን ተግዳሮቶች ያስታውሳሉ፡፡

Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW

“ይህን የድህረ ምረቃ ትምህርት ለመጀመር ሁለት ወሳኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ አንደኛው የማስተማሪያ ዕቃዎች፣ የህክምና መሳሪያዎች ማሟላት ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መምህራኑን መፍጠር ነበር፡፡ ዕቃዎቹን ለማሟላት ከWHO ጋር ወዲያ ወዲህ ተራሩጦ ብዙ ዕቃዎች እንዲገቡ አደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን መምህራን ለማሟላት አንድ ሌላ ትልቅ ተግዳሮት ነበር፡፡ እዚያው ካሉት ከስራ ጓደኞቹ በተጨማሪ እንዲሁ በትርፍ ጊዜ ሰራተኛ እያደረገ፤ የልብ ህክምናን በተመለከተ ለምሳሌ እነ ዶክተር አክሎግ፣ እንደ ዶክተር አብርሃም የሚባሉ የካቲት ሀስፒታል የሚሰሩ ነበሩ፣ ከጦር ኃይሎች እንደእነ ዶክተር ኃይሉ፣ እንዲሁም ሌሎችን እያሰባሰበ፣ እንደምንም ብሎ  ያንን የድህረ ምረቃ መርኃ ግብር ጀመረ፡፡ ይሄ ድህረ ምረቃ መርኃግብር እውነት ነው የምልህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተጀመረው፡፡ እና በእርሱ ርዕይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው በጣም ትልቅ እውቅና የምሰጠው” ይላሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው፡፡  

ወጣቱ ዕደማርያም የድህረ ምረቃ ትምህርት የማስጀመር ዕቅዴን አሳክቼያለሁ ብሎ በውጤቱ ተደስቶ አልተቀመጠም፡፡ ይልቁንም በሙሉ ጊዜም ሆነ በትርፍ ጊዜው አብረውት ከሚሰሩ ሀኪሞች ጋር በመሆን የድህረ ምረቃ ትምህርት መርኃ ግብሩን ማደራጀቱን እና ማጠናከሩን ገፋበት፡፡ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች ተጨማሪ ስልጠና እንዲያገኙ ይባጅ ያዘ፡፡

“ከስር የሚፈጠሩ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ወደ ፊት አስተማሪ እንዲሆኑ ተጨማሪ subspeciality ስልጠና እንዲያገኙ ካናዳ ከሚገኘው፣ ከማክጊል ዩኒቨርስቲ ጋር ለስድስት ፣ ለሰባት ዓመት የቆየ ትልቅ መርኃ ግብር ጀመረ፡፡ ማክጊል እርሱም የተማረበት ነው፡፡ ይመስለኛል እዚያ ያሉ ወዳጆቹም ረድተውታል፡፡ ከዚሁ በድህረ ምረቃ የተመረቁትን በየዓመቱ ሁለት ሁለት እያስላከ 12 ወይም 14 ገደማ subspeciality እንደሚረቁ አደረገ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ከካናዳ ሁለት ሁለት ‘ስፔሻሊስቶች’ እየመጡ እንዲያስተምሩ እያደረገ የድህረ ምረቃውን አጠናክሯል፡፡ 

ዛሬ እንግዲህ ይህ መርኃ ግብሩ ከ20 በላይ ሆኖታል፡፡ በዚህም በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ‘ስፔሻሊስቶች’ እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ በእርግጥ ከዚያ በኋላ የቀዶ ህክምና እና ሌሎችም ተከተሉት፡፡ አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከ100 በላይ የድህረ ምረቃ መርኃግብር እንዳለ እሰማለሁ፡፡ እኒያ የዚያ ሁሉ ጥንስስ ግን መነሻው እርሱ በድፍረት የጀመረው መርኃ ግብር ነው፡፡ እኔ አንዱ ትልቁ የፕሮፌሰር ዕደማርያም ውርስ (legacy) የምለው ይሄ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው  ። 

የልብ ህክምና ስፔሻሊስቱ ፕሮፌሰር ከበደ ኦሊ በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ የፕሮፌሰር ዕደማርያም ቀደምት ተማሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ የፕሮፌሰር ዕደማርያም አስተዋጽኦ በድህረ ምረቃ ትምህርት ብቻ የተገደበ አልነበረም ይላሉ፡፡ “የህክምናን ትምህርት ደረጃ፣ ጥራት ራሱ በማሳደግ የድህረ ምረቃውን ብቻ አይደለም የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቱን ጭምር የህክምና ተቋሙ በውጭውም ዓለም፣ በሀገር ውስጥም ክብር እንዲያገኝ ያደረጉ ሰው ናቸው፡፡ ብዙ ምሁራንን አፍርተዋል” ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። 

በጀማሪ የህክምና ተማሪዎች ዘንድ የፕሮፌሰር ዕደማርያም ዘመን ተሻጋሪ አበርክቶት አሁንም ድረስ የሚታወሰው በመጽሐፋቸው ነው፡፡ «አረንጓዴው መጽሐፍ» በሚል በተለምዶ የሚጠራው የእርሳቸው መጽሐፍ አሁንም በመማሪያ መጽሐፍነት ያገለግላል፡፡ መጽሐፉ እርሳቸው ተማሪ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ለመማሪያነት መዋሉን ፕሮፌሰር ጌታቸው ይናገራሉ፡፡ “A gudie to writing medical reports” በሚል ርዕስ ስለተሰናዳው ስለዚህ መጽሐፍ ይዘት ፕሮፌሰር ከበደ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ 

Edemariam Tsega Professor Äthiopien
ምስል AAU/School of Medicine

“አረንጓዴው መጽሐፍ እንግዲህ የመጀመሪያ በሽተኛ እንዴት ነው ታሪኩ የሚወሰደው? እንዴት ነው የሚመረመረው? እነዚያን አቀናጅቶ ስለህመሙ እንዴት ነው የምንረዳው? የሚል የመጀመሪያ የህክምና ሳይንስ መሰረት ነው፡፡ ያቺን አረንጓዴ መጽሐፍ በመሳጠር ለተማሪዎች ሁሉ እንድትገባ ለቅድመ ዲግሪ ላሉ ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው፡፡ እና ብዙዎቹ ከኪሳቸው የማይለዩት ነው” ሲሉ ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ።  ሁለቱ ጎምቱ የህክምና ባለሙያዎች ከአረንጓዴው መጽሐፍ ይልቅ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጡት በፕሮፌሰር ዕደማርያም ለተዘጋጁት የህክምና ሥነምግባርን (ethics) የተመለከቱ ጥራዞች ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ከበደ አባባል ፕሮፌሰር ዕደማርያም በህክምና ሥነመግባር ረገድም ቢሆን ፋና ወጊ ነበሩ፡፡  

“በኢትዮጵያ የህክምና አገልግሎት ላይ ሥነምግባር ተረስቶ በነበረበት ሰዓት ስለ ህክምና ሥነምግባር ሲጨነቁ የነበሩ እና የህክምና ሥነምግባርን ደረጃ፣ ኮሚቴ የፈጠሩ፣ ጽሁፎችንም ያወጡ ናቸው፡፡ በዚሁ ላይ አነስተኛ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ ይህ ለብዙ ጊዜ እንደ ማጣቀሻ ሲያገለግል የኖረ ነው፡፡  አሁንም ሲማሩ ከሚጠቀሱ ነገሮች አንዱ ይህ መጽሐፍ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ” ይላሉፕሮፌሰር ከበደ፡፡

ከሁለቱ መጽሐፍት ሌላ በመጽሐፍ መልክ የታተሙት የፕሮፌሰር ዕደማርያም የምርምር ጽሁፎችም በኢትዮጵያ የህክምና ሰዎች ዘንድ ተደጋግሞ ይነሳሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ትምህርት ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ፕሮፌሰር ዕደማርያም ከሰማንያ የሚልቁ የምርምር ወረቀቶችን በህክምና ጆርናሎች እና መጽሐፍት አሳትመዋል፡፡ ከፕሮፌሰር ዕደማርያም የታተሙ የምርምር ሥራዎች በኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች በተለይ የሚጠቀሰው በጉበት እና አንጀት በሽታዎች ላይ ያደረጓቸው ምርምሮች ናቸው፡፡

“ፕሮፌሰር ዕደማርያም የጹሁፍ ሰው ነው፡፡ በሽተኛ ማየት፣ ማስተማር ብቻ ሳይሆን በሙያው ይጽፋል፡፡ አስፈላጊ የሚላቸውን ነገሮች ይጽፋል፡፡ እነዚህ አነስ አነስ ያሉ ጽሁፎች ቢሆኑም በጣም ጠቃሚ የሆኑ ጽሁፎች ነበሩ፡ በአብዛኛው እንግዲህ ከእርሱ ሙያ ጋር የተያያዘ ሄፕታይተስ ቢ እና ሲ የሚባል ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ያልተጠና ነገር ነበር፡፡ እርሱ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጥናት አካሄዶ አሳትሟል፡፡ ብዙዎቹ በመጽሐፍ መልክ ተጠርዘው ወጥተዋል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ለሀገሪቱ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነበሩ” ይላሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው። ፕሮፌሰር ከበደ የቀድሞ መምህራቸው ያደርጉት ስለነበረው የጉበት ምርምር ማብራሪያ አላቸው፡፡  

“የተለያዩ አይነት የጉበት ህመሞች አሉ፡፡ ሄፕታይተስ ቢ እና ሄፕታይተስ ሲ ከባድ የጉበት ጽኑ የጉበት ህመም ከማምጣቱ ውጪ ወደ ጉበት ካንሰርም የሚያመራ ነው፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያውያንም እስከዛሬ ድረስ ህይወታቸውን የሚያጡበት ምክንያት ነው፡፡ እርሳቸው ከሁሉ ሰው ቀድመው ሰዎች ችግሩን ባልተረዱበት ሰዓት ጀምረው ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የሄፕታይተስ ቢ ችግር እንደነበረ፣ በተለያየ የህመም ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ስንት እንደነበሩ፣ በጊዜውም ደግሞ የከፋ ነገር ጉበት ካንሰርም ስለሚያስከትል መደረግ ያለባቸው ነገሮች፣ ወደ ኋላ ላይ መከላከያው ክትባት እንዲገባ ትልቅ ሙከራ ያደረጉ ሰው ነበሩ፡፡ ሄፕታይተስ ቢ የሚባለውን ለመከላከል ከሚረዱን ነገሮች አንዱ ክትባት ነው፡፡ ይሄ ክትባት አሁን ለህጻናት የክትባት መርኃ ግብር ውስጥ ገብቶ የሚሰጥ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ከበደ ፡፡

Edemariam Tsega Professor Äthiopien
ምስል AAU/School of Medicine

ፕሮፌሰር ዕደማርያም እንዲህ በምርምር፣ በጽሁፍ ሥራዎቻቸው እና ለህክምና ትምህርት ዕድገት ባበረከቱት አስተዋጽኦ እንደሚታወሱት ሁሉ በመምህርነታቸውም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው እንደሆኑ የቀድሞ ተማሪዎቻቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጀመሩትን መምህርነት በታህሳስ ወር መጨረሻ በ80 ዓመታቸው ህይወታቸው ባለፈበት ካናዳም ቀጥለውበታል፡፡ ከጎርጎሮሳዊው 1995 ዓ.ም. ጀምሮ መኖሪያቸው ባደረጓት ካናዳ በኒውፋውንድላንድ ሚሞሪያል ዩኒቨርስቲ እንደዚሁም በማክማስተር ዩኒቨርስቲ በህክምና ፕሮፌሰርነት አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ በመምህርነት ዘመናቸው እንዴት ያሉ አስተማሪ ነበሩ? ላለፉት 42 ዓመታት ፕሮፌሰር ዕደማርያምን የሚያውቋቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው የመምህርነት «ተምሳሌት ነበሩ» ይሏቸዋል፡፡ 

“ፕሮፌሰር ዕደማርያም በጣም ስነስርዓት አክባሪ የሆነ አካዳሚሽያን ነው፡፡  በእርግጥ እንደማንኛውም ሰው ትንሽ አንዳንድ ድክመቶች ሊኖሩ ይችላሉ ግን ማድረግ የፈለገውን ነገር የሚያስኬደውን ሁሉ ሄዶ የሚፈጽም ሰው ነበረ፡፡ በአካዳሚክ ውስጥ ምርምር ብዙ ይሰራል፡፡ እኛንም ብዙ ያበረታታናል፡፡ ጥሩ መምህር ነበር በአውነት፡፡ ብዙዎቻችን እንደ ተምሳሌት የምንመለከተው መምህራችን ነበር፡፡ በቃ!  መሰጠቱ ልዩ ነበር፡፡ ለትምህርት፣ ለማስተማር፣ ለበሽተኛ፣ ለህክምና፣ ወደፊት ዕድገት ለማሳየት፣ በዚያ በሙያው አካባቢ ትልቅ ሰው ነበር”  ይላሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው፡፡ 

ከፕሮፌሰር ዕደማርያም ተማሪነት እስከ ህክምና ትምህርት ክፍል ዲን ድረስ የተጓዙት ፕሮፌሰር ከበደም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ “የትጋት፣ የባለሙያነት (professionalism)፣ የሀገር ወዳድነት፣ የትውልድ አፍሪ፣ ምሳሌ ነበሩ፡፡ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ በስብዕናቸው ደግሞ እኔ ሳውቃቸው እንግዲህ ይደንቀኝ የነበረው ጠዋት አንድ ሰዓት ቢሮ ነበሩ፡፡ ሁልጊዜ እዚያ ነው የማገኛቸው፡፡ ማታ ከአንድ ሰዓት በፊት ሲወጡ አላይም፡፡ ምሳ ሰዓት ቢሯቸው ነው፡፡ አጋጥሞኝም አይቼያለሁ ምግብ እንኳ ይዘው የሚመጡት አንድ ዳቦ ማዕከሉ ቲማቲም አልፎ አልፎ ሌላ ነገር የተጨመረበት ብቻ ጎርሰው የሚውሉ ነበሩ፡፡ ስራቸውን በልተው፣ ስራቸውን ኖረው ያለፉ፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የማደንቃቸው መምህር ነበሩ፡፡ እኛ የእርሳቸው ተማሪዎች በመሆናችን ትልቅ ደስታ ይሰማኛል” ሲሉ በኩራት ተሞልተው የቀድሞ መምህራቸውን ይዘክራሉ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ