1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአማርኛ ቋንቋ ተቆርቋሪዋ ኒዤሪያዊት የፊልም ባለሞያ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 18 2010

ፊልሟ ውስጥ አማርኛ ጽሑፍ በማስገባት ለአማርኛ ቋንቋ መቆርቋሯን አሳይታለች ኒዤሪያዊቷ የፊልም ባለሞያ ራማቱ ኪየታ፤ አማርኛ የአፍሪቃ ኅብረት ይፋዊ ቋንቋ እስኪሆን ጥረቴን አላቋርጥም ትላለች። ኒዤሪያዊቷ የፊልም ዳይሬክተር በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ በመሳተፍ ለአማርኛ ቋንቋ መሟገቷን ቀጥላለች። 

https://p.dw.com/p/2ma3V
Tunis International film festival 2008 | Emmanuelle Beart & Rahmatou Keita & Nouri Bouzid
ምስል Getty Images/AFP/F. Belaid

የምዕራብ አፍሪቃዊቷ የፊልም ባለሞያ ራማቱ ኪየታ አማርኛ ቋንቋ ከአፍሪቃ ኅብረት ይፋዊ የሥራ ቋንቋዎች መካከል አንዱ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ከጀመረች ሰነባብታለች። ጥረቷን ለማሳካትም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ በአፍሪቃ ኅብረት የተለያዩ ባለሥልጣናትን አነጋግራለች። አሁን ደግሞ  «የጋብቻ ቀለበቱ» የተሰኘው ረዥም የፍቅር ፊልሟን ርእስ እና የፊልም ባለሞያዎች ዝርዝር ከፊልሟ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ በአማርኛ ቋንቋ እንዲጻፍ አድርጋለች። «ይህ ጅማሮ ለጥረቴ መሳካት በግል የማደርገው አንዱ አካል ነው» ያለችው ኒዤሪያዊቷ የፊልም ዳይሬክተር በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ በመሳተፍ ለአማርኛ ቋንቋ መሟገቷን ቀጥላለች። 

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ራማቱ ኪየታ የኒዤር ተወላጅ ጸሐፊና የፊልም ዳይሬክተር ናት።  በእንግሊዝኛ „The wedding ring“  የሚል ስያሜ የሰጠችው ፊልሟን በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በሚነገረው የሐውሳ ቋንቋ «ዝናሪያ» ብላዋለች። ይህን ፊልም ታዲያ ራማቱ ሲኒማ ቤቶች ውስጥ ስታሳይ ርእሱን ወደ አማርኛ «የጋብቻ ቀለበቱ» በሚል ቀይራዋለች። 

በፍቅር ታሪክ ላይ ያጠነጠነው የራማቱ ፊልም አንዲት አውሮጳ ውስጥ ዲግሪዋን ያገኘች የፉላኒ ወጣት አፍሪቃ ውስጥ በሳህል የገዢ መደብ ሥር ወደሚገኘው የዚንደር ሱልጣን ትመለሳለች። እዚያም በባሕላዊ መንገድ ለባል ልትሰጥ ስትል በሚኖረው ውጣ ውረድ ላይ ይሽከረከራል ፊልሙ።  በዋናነት ግን መሽኮርመም የዳሰሰው ፍቅር በአፍሪቃ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ጥረት ያደርጋል። 

ይህ የራማቱ ኪዬታ ፊልም አምስተርዳም ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል (World Cinema Amsterdam) ላይ አምስተርዳም ከተማ ውስጥ ከመታየቱ በፊት እዛው ሆላንድ ሮተርዳም የተሰኘው ሌላ ከተማ ውስጥም ለእይታ በቅቶ ነበር።  

ፊልምሽን እዚህ ሆላንድ ከተማ ሪያልቶ ሲኒማ ቤት ውስጥ ለእይታ ከቀረቡ ሌሎች ፊልሞች ለየት የሚያደርገው አንድ ነገር ተመልክቻለሁ፤ ያ ምን እንደሆነ ለአድማጮቻችን ብትገልጪላቸው ስል ጠየቅኳት ኒዤሪያዊቷ የፊልም ባለሞያን።

«ፊልሙ የፍቅር ታሪክ ነው። ምናልባት አንተ ኢትዮጵያዊ ስለሆንክ የምታወራው የፊልሙ ባለሞያዎች ዝርዝር በአማርኛ መጻፉን ነው። ፊልሙ ሲጀምር እና ሲጠናቀቅ የፊልም ባለሞያዎቹ ዝርዝር ሙሉ ለሙሉ በአማርኛ ቀርቧል።»

Niederlande Amsterdam - Rahmatou Keita "The wedding Ring" in World Cinema Amsterdam 2017
ኒዤሪያዊቷ የፊልም ባለሞያ በስተቀኝ በኩል ሻሽ ያሰረችውምስል DW/M. Sileshi

የራማቱ የፍቅር ፊልም ከመጀመሩ በፊት ለፊልሙ ድጋፍ ያደረጉ ተቋማት ዝርዝር በአማርኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ቀርቧል። ራማቱ የአማርኛ ጽሑፉን በደማቅ ብርቱኳንማ ቀለም ጽፋ ከፈረንሳዪኛው በላይ ነው ያሰፈረችው። 

ለፊልሙ ድጋፍ ካደረጉ ተቋማትና ሃገራት መካከልም በቅድሚያ «የኒጀር ሪፐብሊክ» የሚለው ከመሀከል ብቅ ይላል። ከዚያም በተከታታይ «የኮንጎ ብራዛቪል ሪፐብሊክ»፤ «የአልጀሪያ ሕዝባዊ  ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ»፤  «የሩዋንዳ ሪፐብሊክ»፤ «የዩጋንዳ ሪፐብሊክ»፤ «የሞሮኮ ንጉሣዊ መንግሥት» እንዲሁም «የፓን አፍሪቃ ባህል ፌስቲቫል አልጀርስ -2009» የሚሉ ጽሑፎች በአማርኛ ይነበባሉ። 

«መታሰቢያነቱ ሞያውን ለአወረሰኝ ለእናቴ ወንድም አጎቴ ሳማሪ ኤል-ሀዲ ሐሪንታ ጂቤ ዲያሎ (=1934 -2015)» የሚል የአማርኛ ጽሑፍ ከተነበበ በኋላ ደግሞ ጥንታዊ ህንጻ ውስጥ የተሰባሰቡ ወንዶች ይታያሉ። 

ሙዚቃ እና የአካባቢው ድባባዊ ድምጽ ይሰማል። ግቢ ውስጥ መሬት ላይ ተቀምጠው በአንድ ትሪ ላይ በጋራ የሚመገቡ ሴቶች ይታያሉ። ግንባሯ ላይ የተነቀሰችው ቆንጅዬዋ የፊልሙ ዋና ገጸ ባሕሪ ቲያ ግን ተክዛ አቀርቅራለች። 

ቲያ በሚቀጥለው ትእይንት ጓደኛዋ ጠጠር ቆጣሪ ዘንድ ይዛት ስትሄድ እሷ እውጭ አቧራማ ሜዳው ላይ ተቀምጠው ገበጣ የሚጫወቱት ልጆች ጋር ታመራለች። ጠጠር ቆጣሪው ጋር የገባችው ጓደኛዋ ተመልሳ በመውጣት ቲያ አብራት እንድትገባ ትጠይቃለች። ቲያ ግን «የእሱ ርዳታ የሚያሻው ለአንቺ እንጂ ለእኔ አይደለም። ደሞ አንቺን እንጂ እኔን ሊረዳ አይችልም» ትላታለች።

ጓደኛዋ በሩን በኃይል ዘግታ ወደ ውስጥ ስትመለስ «የጋብቻ ቀለበቱ» የሚለው የፊልሙ ርእስ በአማርኛ ይነበባል። ከዚያም ዝናሪያ የሚለው የሐውሳ ርእስ እና የእንግሊዝኛው„The wedding ring“  ይከተለዋል።  አሁንም በደማቅ ቡኒ ቀለም የተጻፈው የአማርኛ ጽሑፍ ነው ቀድሞ የሚነበበው። 

Niederlande Amsterdam - Rahmatou Keita "The wedding Ring" in World Cinema Amsterdam 2017
ምስል DW/M. Sileshi

ራማቱ ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁሶች ፊልሙ ውስጥ ጎልተው እንዲወጡ ለማድረግ ሞክራለች። ቲያ የምትለብሰው በእደ ጥበብ ባለሞያ በእጅ ስፌት የተሠራው ባህላዊ የሙሽራ ቀሚስን ለማጠናቀቅ ብቻ አንድ ዓመት ያህል ጊዜ መውሰዱንም ገልጣለች።  ከባህላዊ አልባሳቱና ቁሳቁሱ በተጨማሪ ራማቱ ፊልሟ ውስጥ የተለያዩ የአፍሪቃ ቋንቋዎችንም አካታለች። 
በአፍሪቃ በእርግጥም «እጅግ በርካታ ቋንቋዎች አሉ» የምትለው ኒዤሪያዊቷ የፊልም ባለሞያ በሐውሳ ቋንቋ «ዝናሪያ» የሚል ርእስ የሰጠችው ፊልሟ ሦስት የአፍሪቃ ቋንቋዎች ይነገሩበታል፤ ሐውሳ፣ ሶንጎይ እንዲሁም ፉላኒ። ራማቱ የፊልም ባለሞያዎች ዝርዝርን በአማርኛ መጻፉን የመረጠችው አማርኛ ቋንቋ በአፍሪቃ«ልዩ ስለሆነ እና እንክብካቤ ስለሚያስፈልገው ነው» ትላለች።  

«የፊልም ባለሞያዎች ዝርዝርን በአማርኛ ለመጻፍ የመረጥኩበት ምክንያት፤ አማርኛ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑ የዓለማችን የጽሑፍ ቋንቋዎች አንዱ በመሆኑ ነው። በዓለም እንዲህ አይነት ቋንቋዎች ጥቂት ናቸው። ይህ ውብ ፊደላት ያሉት ቋንቋ በኢትዮጵያ እና በጥቂት ሰዎች በኤርትራ ይነገራል። ከመቶ ሚሊዮን አይበልጥም ተናጋሪው፤ ያ ምንም ማለት ነው። ወደ ዐሥር ቢሊዮን እየተጓዘ በሚገኘው የዓለም ቋንቋ ያን ማድረግ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው።»

በዓለም ዙሪያ የሚነገሩ እና በመጥፋት ላይ ያሉ ቋንቋዎች መረጃን ያሰባሰበው «ስነ-ሰብ የዓለም ቋንቋዎች» (Ethnologue: Languages of the World) የተሰኘው ድረ-ገጽ ሰባት ሺህ ግድም ቋንቋዎች በዓለማችን እንደሚገኙ ይጠቅሳል። 
7.6 ቢሊዮን ግድም ነዋሪዎች ባሏት ዓለማችን የቻይና ማንዳሪን ቋንቋ በ898 ሚሊዮን ተናጋሪዎች በቀዳሚነት ይገኛል። ኒዤሪያዊቷ የፊልም ባለሞያ ራማቱ ኪዬታ 1.2 ቢሊዮን ተናጋሪዎች ባሏት አፍሪቃ አማርኛ ቋንቋ ተገቢውን ሥፍራ አላገኘም ባይ ናት። 

«ትግሌ ውብ ባሕላችን ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር ማድረግ ነው፤ ባሕላችንን ካልተንከባከብን እየደበዘዘ ለመክሰም ጊዜ አይፈጅበትም» ያለችው ራማቱ፦ በተጓዘችበት ሥፍራ ሁሉ አማርኛ ከአፍሪቃ ኅብረት ይፋዊ መግባቢያዎች አንዱ እንዲሆን መወትወቷን አታቋርጥም። 

«አፍሪቃ ውስጥ በኛ በፓን አፍሪቃ ፊልም ሠሪዎች ፌዴሬሽን አባልትም ኾነ በአፍሪቃ ኅብረት መካከል ስብሰባ በሚኖርበት እና ጉዞ በማደርግበት ጊዜ አማርኛን ይፋዊ የመግባቢያ ቋንቋቸው አድርገው እንዲጨምሩ እንደወተወትኩ ነው። ብዙውን ጊዜ ታዲያ ይስቁብኛል።»

ራማቱ ሰዎች ሳቁብኝ ብላ ግን ጥረቷን በእንጭጩ አልቀጨችም። ከታዋቂ ሰዎች እስከ ሀገር መሪዎች ድረስ ባገኘችው አጋጣሚ ውትወታዋን አልተወችም። በአንድ አጋጣሚ እንደውም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር መለስ ዜናዊን አዲስ አበባ ውስጥ በዚሁ ጉዳይ አነጋግራ እንደነበር ገልጣለች። 

«ራህማቱ ሙሉ በሙሉ ትክክል ነሽ አሉኝ። ግን ሠነዱ  ጽሑፍ ውስጥ የለም አሉኝ።  እናም እኔ ክቡር ጠቅላይ ሚንሥትር ፅሑፉን እኛ ነን የምናበጀው አልኳቸው።»

Niederlande Amsterdam - Rahmatou Keita "The wedding Ring" in World Cinema Amsterdam 2017
የፊልም አፍቃሪዋ ፊዮና ፎሪክ በአምስተርዳም ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫልምስል DW/M. Sileshi

ራህማቱ የጀመረችውን ጥረት ከዳሩ ለማድረስ «ቋልፉ በእጃችን ነው» ትላለች። እናም «እኛው ጀምረን ካላሳየን ሌላው ሊከተለን አይችልም» በማለት እንደ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ እና አቶ ሰለሞን በቀለ ከመሳሰሉ አንጋፋ እና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የፊልም ሠሪዎች ጋር በመነጋገር ፊልሟ ውስጥ የአማርኛ ቋንቋን ለመንደርደሪያ ያህል በጽሑፍ አስገብታለች። ወደፊት ተባባሪ ካገኘች ሙሉ ፊልሟን በአማርኛ ቋንቋ አስተርጉማ ኢትዮጵያ ውስጥም የማሳየት ዕቅድ ነድፋለች።
 

«ይህን ፊልም ሙሉ በሙሉ በአማርኛ አስተርጉሜ ኢትዮጵያ ውስጥ ማሳየት እፈልጋለሁ።» ያን ለማድረግም በኢትዮጵያ የባህል ሚንሥትርን ማነጋገር እፈልጋለሁ ብላለች። ራማቱ ከአማርኛ ቋንቋ ባሻገር ፊልሟን በዓረቢኛ እና ኪስዋሒሊ ቋንቋዎችም ማስተርጎም ትፈልጋለች። ኒዤሪያዊቷ የፊልም ባለሞያ አፍሪቃውያን ቋንቋ እና ባህላቸውን እርስ በእርስ መተዋወቅ እና መለዋወጥ ያስፈልጋቸዋል ስትልም አስረግጣ ትናገራለች።
 
«አፍሪቃ በጣም ውብ ናት።  እናም ያን ውበቷን ማሳየት አለብን።  ያን እኛ ካላደረግን ማንም አያደርም። ባህላችንን እንዴት እርስ በእርስ ማስተዋወቅ እንዳለብንም ማጤን ያሻል። እኔ ወደ ኢትዮጵያ ስሄድ ሁሉም በአማርኛ ነው የሚያናግሩኝ። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ አይደለሁም። አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የጸጉር አሠራሩ ራሱ ከሀገሬ ጋር ተመሳሳይ ነው።» 

«የጋብቻ ቀለበቱ» በተሰኘው ፊልም ውስጥ ዋናውን ገጸ ባሕሪ የምትጫወተው ተዋናዪት የአዘጋጅዋ ልጅ ናት። የፉላኒ ቋንቋውን ከፊልም ዳይሬክተር እናቷ ነው የተማረችው። ግንባሯ ላይ የተነቀሰችው ምስል እና መልኳን ላየ ኢትዮጵያዊት ናት ብሎ ሊሳሳት ይችላል። ተወልዳ ያደገችው ግን ፈረንሳይ ውስጥ ነው።  

«እኛ በምዕራብ አፍሪቃ የምንገኝ ሰዎች እናንተ ስለእኛ ከምታውቁት በተሻለ ስለእናንተ እናውቃለን። ያ ለምን እንደሆነ እንጃ። ግን እኛ ስለእናንተ ታሪክ፤ ለነፃነት ስላደረጋችሁት ተጋድሎ፤ ስለ ንጉሦቻችሁ እና ታሪካችሁ በአጠቃላይ እናውቃለን። እናንተ ግን ስለ እኛ አታውቁም። ለአብነት ያህል ትልልቅ ጥንታዊ ከተሞች እንዳሉን፤ በፊልሜ ውስጥ እንዳየኸው አይነት ቤተ-መንግሥቶች እንዳሉን፤ ስለ ውብ ሥነ-ሕንጻዎቻችንም አታውቁም። ስለዚህ ያን ማሳየት አለብን። ማንነታችንንም ለእራሳችን እና ለዓለም ማሳየት አለብን። ሌላው ዓለም ስለ አንተ እንዲያሳይ አትጠብቅ።  እነሱ ብዙውን ጊዜ እኛን የሚወዱ አይደሉም። አንተ ማን እንደሆንክ እነሱ ብቻ እንዲነግሩህ አታድርግ።»

ሆላንድ ውስጥ በአምስተርዳም ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ያገኘኋቸው የሲኒማ አፍቃሪዋ ፊዮና ፎሪንክ ላለፉት አምስት ዓመታት በፌስቲቫሉ የቀረቡ ፊልሞች አምልጧቸው አያውቅም። መሰል የፊልም ፌስቲቫሎች ስለ አፍሪቃ እና የአኅጉሪቱ ነዋሪዎች የበለጠ ለማወቅ ይረዳል ይላሉ።

Niederlande Amsterdam - Rahmatou Keita "The wedding Ring" in World Cinema Amsterdam 2017
የፊልም አፍቃሪው ኡቱንግ ቡተር በአምስተርዳም ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫልምስል DW/M. Sileshi

«አፍሪቃን እንደ አንድ ሀገር መመልከቱ አስቂኝ ነው። አፍሪቃ የ,ራሳቸው ባህልና ማንነት ያላቸው በርካታ ሃገራት የሚገኙባት ግዙፍ አኅጉር ናት። በአንዳንድ ሃገራት እንደውም በርካታ ጎሳዎች ይገኛሉ። አፍሪቃ በርካታ ባህል ቢኖራትም እኛ የምናየው ድህነት እና ረሐብ ብቻ ነው። የምናየው ያን ነው እንጂ በዚህ ፌስቲቫል እንደቀረበው አይነት የበለጸገ ባህሏን አናይም። ስለዚህ ፌስቲባሉ የእያታ አድማሴን አስፍቶታል።»
 
በአምስተርዳም ከተማ ነዋሪ የሆኑት ኡንቱንግ ቡተር የራማቱ ኪየታን «የጋብቻ ቀለበቱ» ፊልም መመልከታቸው ስለ አፍሪቃ ባህል የበለጠ እንዲያውቁ አድርጓቸዋል።  
«የትም ሳትጓዝ የተጓዝክ ያህል ዕድል ይሰጥሃል። የዘንድሮው ፌስቲቫል በተለይ የሌላኛው ዓለም ክፍል ምን እንደሚመስል በበርካታ ሃገራት ውክልና አሳይቷል። ለምሳሌ ትናንት አንድ የኒዠር ፊልም ተመልክቻለሁ። ቀደም ሲል ስለ ሀገሪቱ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። ንጉሣዊ ሥርዓት እንደነበራቸውም አላውቅም ነበር።  ስለዚህ ፌስቲቫሉ ሌሎች ሰዎች እንዴት እንደሚኖሩ ምን እንደሚሠሩ የማወቅ ዕድሉን ይሰጥሀል። የሌላ ሀገር ባህልን ከማስተዋወቅም ባሻገር ይበልጥ ቀርበህ እንድትመለከተው ያደርግሀል። ያ የፊልም ውበት ነው።»

«የጋብቻ ቀለበቱ» የተሰኘው የራህማቱ ኪየታ ሁለተኛ ረዥም ፊልም እንደ ቶሮንቶ ባሉ ተለቅ ያሉ ፌስቲቫሎች ላይም ለእይታ ቀርቧል። ራህማቱ «የጋብቻ ቀለበቱ»ን ከመሥራቷ በፊት ቀደም ሲል አሊሲ የተሰኘ በካን ፊልም ፌስቲቫል ላይ ለእይታ የበቃ ዘጋቢ ፊልም ሠርታለች። ራህማቱ በሁለተኛ ፊልሟ ወደ ፊቸር ፊልም ብትዞርም ፊልሙ በአብዛኛው የዘጋቢ ፊልም ላይ በጉልህ የሚስተዋለው እውነታን እንዳለ የማቅረብ ስልት ጠንከር ብሎ ይታይበታል። ኒዠር፤ ቡርኪናፋሶ እና ፈረንሳይ ውስጥ የተሠራው የራህማቱ ፊልም ጀርመን ውስጥ በኮሎኝ እና በሐምቡርግ ከተሞች የታየ ሲሆን በተለያዩ የፊልም ፌስቲቫሎች ለእይታ ይበቃል። እንደ አማርኛ ቋንቋ አምባሳደር በየሀገሩ የምትዘዋወረው ራህማቱም ለአማርኛ ቋንቋ እድገት የጀመረችውን ጥረት መቀጠሏን አታቋርጥም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ