1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሰኔ 4 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሰኔ 4 2010

በዳያመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው ሰለሞን ባረጋ ድል ሲቀዳጅ፤ በ1500 ሜትር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋዬ አሸንፋለች። ትናንት ሉሲዎቹ በሚል የሚጠሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ግን ምንም ጥሩ ቢጫወት ተሸንፏል። ስለ ዓለም ዋንጫም ዝርዝር ነጥቦችን ይዘናል።

https://p.dw.com/p/2zJeY
Russland, Moskau: WM 2018, FIFA Symbolbild
ምስል Getty Images/AFP/S. Khan

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በስቶክሆልሙ የዳያመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሩጫ ውድድር ሰለሞን ባረጋ ድል መቀዳጀቱ የተሰማው ትናንት ነበር። ሰለሞን ውድድሩን ለመጨረስ የፈጀበት ጊዜ  13:04.05  ነው። የትናንቱ ውድድር ሊጠናቀቅ ሦስት ዙሮች ሲቀሩት ውድድሩ በሁለት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያዊ መካከል ነበር። በተለይ በአሸናፊው ሰለሞን ባረጋ  እና ብርሃኑ ባለው መካከል ጠንካራ ፉክክር ታይቶ ነበር። ለባህሬን ተሰልፎ የሚሮጠው ትውልደ-ኢትዮጵያዊው ብርሃኑ ባለው  በሰለሞን የተቀደመው ከሰከንድ ባነሰ በ20 ማይክሮ ሰከንድ ነው። ሁለተኛ ደረጃን ለማግኘት  13:04.25 ብቻ ነው ያስፈለገው።

የመጨረሻው ዙር ሊጠናቀቅ 200 ሜትሮች ሲቀሩት የተፈተለኩት ሰለሞንን እና ብርሃኑን በመከተል የሦስተኛ ደረጃን ያገኘው አባዲ ሐዲስ ነው። በአጠቃላይ የዳያመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አሸናፊው ሰለሞን በድምር ውጤት 8 ነጥብ አለው። ብርሃኑ በ7 ሐዲስ በ6 ነጥብ ይከተላል። 

በሴቶች  የ1500 ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋዬ በስቶክሆልም ኦሎምፒክ ስታዲየም  3:57.64  በመሮጥ ድል ተቀዳጅታለች።   የብሪታንያዋ ላውራ ሙይር የሁለተኛ ደረጃን ስታገኝ፤ ሞሮካዊቷ ራቤ አራፊ ሦስተኛ ወጥታለች።

Symbolbild Startlinie Startschuss
ምስል picture-alliance/Rolf Kosecki

የዳያመንድ ሊግ ፍጻሜ ከሁለት ወራት በኋላ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓም የሚከናወነው በቤልጂየም መዲና ብራስልስ ከተማ ውስጥ ነው።

ጋና ውስጥ በሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ለመሳተፍ የመጨረሻ ዙር ግጥሚያውን ትናንት ያከናወነው  የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአልጀሪያ ቡድን ተሸንፎ ከውድድሩ ወጥቷል። ሉሲዎቹ ትናንት 3 ለ2 ቀደም ሲል አልጀሪያ  ውስጥ ደግሞ 3 ለ1 በድምሩ 6 ለ3 በኾነ ውጤት በመሸነፋቸው የአልጄሪያ ብሔራዊ የሴቶች ቡድን ወደ ጋናው የአፍሪቃ ዋንጫ  አልፏል። የአልጀሪያው አሰልጣኝ አምነው እንደተቀበሉት በትናንቱ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡድን በማጥቃት የተሻለ ኾኖ ነበር። ኾኖም ተጋጣሚው አልጀሪያ በመልሶ ማጥቃት ስልት ያስቆጠራቸውን ግቦች በማስጠበቁ ድል ተቀዳጅቷል። የትናንቱን ጨዋታ ደጋፊዎች  ስታዲየም በነጻ ገብተው ሉሲዎቹን እንዲደግፉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥሪ አስተላልፎ ነበር። ስታዲየም የታደሙ ደጋፊዎች ለቡድኑ ያሳዩት ድጋፍ አልጀሪያዎችን እንዳስደመማቸውም ተናግረዋል።

አሁን ደግሞ አድማጮች ጥቂት ስለ ዓለም ዋንጫ እግር ኳስ የማሟሟቂያ ጨዋታዎች እና ስለ አስተናጋጇ ሩስያ ጥቂት እንበል።  የዓለም ዋንጫ  ከመድረሱ በፊት በሚደረጉ የማሟሟቂያ ግጥሚያዎች ትናንት ብራዚል ኦስትሪያን 3 ለ0 በኾነ ሰፊ ልዩነት ድል አድርጋለች። በኦስትሪያ መዲና ቪዬና ውስጥ በተደረገው ግጥሚያ የተሰለፈው ኔይማር የእግር ቀዶ-ጥገና ከተደረገለት በኋላ የመጀመሪያው የኾነችውን ግብ አስቆጥሯል።  ኔይማር ምንም እንኳን ረዘም ካለ ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰ ቢኾንም፤ ሳይጫወት መቆየቱ እክል እንዳልፈጠረበት በትናንቱ ግጥሚያ አሳይቷል።

Fußball Wien Testspiel Österreich vs Brasilien Marko Arnautovic
ምስል Imago/Eibner

የፓሪስ ሳን ጀርሜኑ ኮከብ ኔይማር ቀደም ሲል ከክሮሺያ ጋር በነበረው የወዳጅነት ግጥሚያ ተቀይሮ ነበር ወደ ሜዳ የገባው። በመጀመሪያው የክሮሺያ እና የብራዚል ግጥሚያ ግብ ያስቆጠረው ኔይማር በትናንቱም መድገሙ አድናቆት አስችሮታል። የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ጋብሬል ጂሰስ ቀዳሚዋን ግብ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ሲያሳርፍ፤ ኔይማር ሁለተኛዋን ነበር ያስቆጠረው። ለብራዚል ከኔይማር እና ጋብሬል ውጪ የባርሴሎናው አማካይ ኩቲንሆ ሦስተኛዋን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።

ጥቂት ስለ ሩስያ የዓለም ዋንጫ ወሳኝ ነጥቦችን እናካፍላችሁ። የሩስያ የዓለም ዋንጫ ከ32 ተሳታፊ ሃገራት ወደ 48 ለመሸጋገር የመጨረሻው ሁለተኛ ውድድር ነው። ከሩስያ ቀጥሎ ከአራት ዓመት በኋላ ካታር በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ላይም ተሳታፊ ሃገራት 32 ሲኾኑ፤ ከዛ በኋላ ግን ተወዳዳሪዎች ቁጥራቸው ከፍ ብሎ 48 ይኾናል።

አይርላንድ እና ፓናማ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያሉ ሃገራት ናቸው። የዓለም ዋንጫ ውድድሮች የሚከናወንባቸው በሀገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኘው ካሊኒንግራድ እና በስተምዕራብ በኩል ያለው የኤካተሪንበርግ ከተሞች ርቀት ከሞሮኮ እስከ ለንደን እንደማለት ነው። በአጠቃላይ በሁለቱ ከተሞች ያለው ርቀት 2,424 ኪሎ ሜትር ይደርሳል።  በዓለም ዋንጫ ታሪክ በሁሉም ውድድሮች ተሳታፊ በመኾን እና 5 ጊዜ ዋንጫ በመብላት ቀዳሚዋ ብራዚል ናት። ምናልባትም ስድስተኛው ሩስያ ላይ ይጠብቃት ይኾናል።

Fußball WM Brasilien Training Qualifikation
ምስል picture-alliance/dpa/J. Jacome

ጀርመን በበኩሏ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1958 እና በ1962 በተከታታይ ብራዚል ዋንጫውን ከወሰደች በኋላ በተከታታይ በማሸነፍ ተከታዩዋ ሀገር ትኾን ይኾናል። ያለፈውን የዓለም ዋንጫ ያሸነፈችው ጀርመን በሩስያው የዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ ሊደርሱ ይችላሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው ሃገራት ትመደባለች። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ውድድር በርካታ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የሚስተካከለው የለም። የጀርመን ቡድን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 18 ግቦችን በ2010 16 እንዲሁም በ2006 14 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

የሩስያው ኦሌግ ሣሌንኮ በዓለም ዋንጫ ውድድር በአንድ ጊዜ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የሚደርስበት የለም። ሀገሩ ሩስያ ከ24 ዓመት በፊት ከካሜሩን ጋር ባደረገችው ግጥሚያ አምስት ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ሩስያ በወቅቱ 6 ለ1 ያሸነፈች ሲኾን፤ ስድስተኛዋን ግብ የዲሚትሪ ሊዮኒዶቪች ራጅቼንኮ ነበር። ካሜሩንን ከ0 የታደጋት የያኔው ምርጥ ሮጀር ሚላ ነበር። ምናልባት ዘንድሮ የጀርመኑ ግብ አዳኝ ቶማስ ሙይለር በርካታ ግቦችን ያስቆጥሮ ይኾናል።  ክብር ወሰኑን ለመስበር ግን ከባድ ሳይኾን አይቀርም።  

Fußball WM 2018 Mannschaftsfoto DFB Nationalteam Deutsche Nationalmannschaft
ምስል Imago/Revierfoto

በአኹኑ ወቅት በዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ከኾኑ ተጨዋቾች መካከል እንደ ቶማስ ሙይለር በርካታ ግቦችን በማስቆጠር እና ለግብ በማመቻቸት የሚስተካከል የለም። ጀርመናዊው አጥቂ እስከ አኹን በተሰለፈባቸው የዓለም ዋንጫ ውድድሮች 10 ግቦችን ማስቆጠር እና 6 ኳሶች ግብ እንዲኾኑ በማመቻቸት የሚስተካከለው የለም። የሁሉም የዓለም ዋንጫ ውድድሮች የዋንጭ ባለድል የኾኑ አሰልጣኞች የሀገራቸውን ቡድን ያሰለጠኑ ናቸው። ምናልባት እንግሊዝ በዚህ ጉዳይ ላይ ልታስብበት ሳይገባ አይቀርም።

ሩስያ ሶቪየት ኅብረት መኾኗ ካከተመ ወዲህ በዓለም ዋንጫ ከምድቧ አልፋ ዐታውቅም። የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ጨዋታን ምናልባት በደጋፊዎቿ ፊት ስለምታከናውን ያ ይረዳት ይኾናል። እንደ ናይጀሪያ ቡድን ከአፍሪቃ በብዛት ለዓለም ዋንጫ የደረሰ ቡድን የለም።  ኃያል ንሥሮቹ ከ1994 ወዲህ ናይጀሪያ ቡድኗ ለዓለም ዋንጫ ሲበቃ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ መኾኑ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1958 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሳታልፍ የቀረችው ሀገር ደግሞ ጣሊያን ናት።

በዓለም ዋንጫ ምንም ሳያሸንፉ ብዙ በመሳተፍ ደግሞ ኔዘርላንዶችን የሚስተካከል የለም።  ብርቱካናማዎቹ ምርጥ ጨዋታ እያሳዩ ዋንጫ እያማራቸው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ለምደውታል። ሩስያ ላይ ይሳካላቸው ይኾን? ከሦስት ቀናት በኋላ በሚጀምረው የዓለም ዋንጫ ውድድር የምናየው ይኾናል።

Formel Eins, Kanada 2018: Sebastian Vettel in Führung
ምስል Imago/Octane

የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም

በሞንትሪያል ካናዳ የትናንቱ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ያሸነፈው ጀርመናዊው ሰባስቲያን  ፌትል  የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የመሪነት ስፍራ ተረክቧል።  በትናንቱ ውድድር ሰባስቲያን ፌትልን በመከተል ቫለሪ ቦታስ፣ ማክስ ፈርሽታፐን እና   ዳኒኤል ሪካርዶ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን  ደረጃ  ወስደዋል። በትናንቱ ሽቅድምምድ የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሀሚልተን  የአምስተኛ ደረጃን አግኝቷል።  ከውድድሩ በኋላ ባደረገው ቃለ መጠይቅ ሌዊስ፦ የአጠቃላይ ውድድሩ ቀዳሚነቱን ሥፍራ ማጣቱ እንደማያስጨንቀው፤ ይልቁንስ ውድድሩን ማጠናቀቁ በራሱ እፎይታ መኾኑን ገልጧል። 

የሜዳ ቴኒስ

Tennis French Open Finalsieger Rafael Nadal mit Pokal
ምስል Getty Images/AFP/T. Samson

17ኛ ታላቅ ድሉን ትናንትና የተቀዳጀው ስፔናዊው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ራፋኤል ናዳል በወንዶች የምንጊዜም ድል ኮከቡ የስዊዘርላንዱ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሮጀር ፌዴሬር ላይ እድረስላሁ ማለት« እብደት ነው» ሲል ተናግሯል። የ32 ዓመቱ ስፔናዊ እስካሁን 11 የፈረንሳይ ፍጻሜ በአጠቃላይ የ17 የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ባለድ ነው። ስዊዘርላንዳዊው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሮጀር ፌዴሬር 20 ጊዜያት በማሸነፍ ኃያልነቱን ያስመሰከረ ስፖርተኛ ነው።  ራፋኤል ናዳል በፈረንሳዩ ፍጻሜ ትናንት  6-4 6 -3 እና 6-2 ያሸነፈው ዶሚኒክ ቲየምን ነው። በአጠቃላይ ድል ራፋኤል ናዳል  ከሮጀር ፌዴሬር በመከተል ሁለተኛ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ