1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥር 27 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥር 27 2011

አርጀንቲናዊው አጥቂ እና አብራሪውን እንዳሳፈረች ከራዳር ውጪ ተሰውራ የነበረችው አነስተኛ አውሮፕላን ዛሬ በፈረንሳይና ብሪታንያ መሀል ከባሕር ጠለል ስር ተከስክሳ ተገኝታለች። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናልን ትናንት ጉድ የሠራው ማንቸስተር ሲቲ የሊቨርፑል ግስጋሴ ላይ ተቃርቧል። በእስያ እግር ኳስ ዋንጫ ፍልሚያ ጃፓን ለኳታር እጅ ሰጥታለች።

https://p.dw.com/p/3ChmW
Großbritannien FA Cup | Swansea City vs. Gillingham | Blumen für Emiliano Sala
ምስል Getty Images/S. Forster

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

አርጀንቲናዊው አጥቂ እና አብራሪውን እንዳሳፈረች የዛሬ 15 ቀን ከራዳር ውጪ ተሰውራ የነበረችው አነስተኛ አውሮፕላን ዛሬ በፈረንሳይ እና ብሪታንያ መሀል ከባሕር ጠለል ስር ተከስክሳ ተገኝታለች።  በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናልን ትናንት ጉድ የሠራው ማንቸስተር ሲቲ የሊቨርፑል ግስጋሴ ላይ ተቃርቧል። መሪው ሊቨርፑል ዛሬ ከዌስትሐም ጋር የሚያደርገው ተስተካካይ ግጥሚያ ግን የነጥብ ልዩነቱን ወደ ቀድሞው አምስት ሊመልሰው ይችል ይኾናል። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ። በቡንደስሊጋው ባየር ሙይንሽን ዳግም ሽንፈት ሲገጥመው፤ መሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነጥብ ጥሏል። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ስር ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በእስያ እግር ኳስ ዋንጫ ፍልሚያ ጃፓን ለኳታር  እጅ ሰጥታለች።  

እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከ2015 በፊት እዚህ ግባ የሚባል ቡድን አልነበረም፤ የኳታር ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን። ስፔናዊው አሰልጣኝ ፌሊክስ ሳንቼዝ ቡድኑን በፈጣን ግስጋሴ ከፍተኛ ማማ ላይ አድርሰውታል። ምናልባት ሀገሪቱ በምታሰናዳው በ2022ቱ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ከኳታር ቡድን ጋር አብረው ላይኾኑ ይችላሉ። ኾኖም ግን ሣንቼዝ ቡድኑን ከፍ ከፍ በማድረጋቸው ከኳታሮች ልብ መቼም የሚወጡ አይመስልም።።

ዓርብ ዕለት የኳታሯ መዲና ዶሀ በደጋፊዎች ደስታ እና ፈንጠዝያ ደምቃ ነበር ያመሸችው፤ የፈንጠዝያው ሰበብ ደግሞ እኒሁ ስፔናዊ አሰልጣኝ ፌሊክስ ሳንቼዝ ናቸው። የኳታርን ቡድን መርተው የዓለም ዋንጫ ልምድ ያለውን የጃፓን ቡድን 3 ለ1 ድል ነስተው ዋንጫውን ዶሃ ይዘው ሲገቡ መላው ኳታር በፌሽታ ሰክሯል።  

BG Katars Trainer Felix Sanchez | WM 2018 - Qualifikationsspiele
ምስል picture alliance / Zhong Zhenbin/Imaginechina/dpa

ፌሊክስ ለድል ያበቁትን ቡድን ሲመሰርቱ ከታች «ሀ» ብለው ነው። አብዛኞቹ የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በኳታር እግር ኳስ አካዳሚ ከዘጠኝ ዓመታቸው ጀምሮ ሲሰለጥኑ የቆዩ ናቸው። ስፔናዊው አሰልጣኝ፦ የኳታርን ቡድን ይዘው የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ድላቸው የተመዘገበው ከአምስት ዓመታት በፊት በ2014 ነበር።  ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የእስያ ዋንጫም የድል አቦሉን ቀመሱ። በዚያ ግን አልረኩም። ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚፎካከሩበት ሌላኛው የእስያ እግር ኳስ ፍልሚያ ባለፈው ዓመት ለግማሽ ፍጻሜ ደርሰው ነበር። ዘንድሮ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን መርተው፤ ዐርብ ዕለት የእስያን ዋንጫ አስጨብጠው መላ ኳታርን በደስታ አስክረዋል። ፌሊክስ የኳታር ቡድን 11ኛው አሰልጣኝ ኾነው ብቅ ካሉበት ጊዜ አንስቶ ግስጋሴያቸው ኹሉ በከፍታ ላይ ነው።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ መሪው ሊቨርፑል ዛሬ ማታ ከዌስትሀም ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነው። 61 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የኹለት ነጥብ ልዩነት ወደ ቀድሞው 5 ከፍ ለማድረግ በዛሬው ተስተካካይ ጨዋታው ማሸነፍ ይጠበቅበታል። 

ከስድስት ሳምንት በኋላ ለሊቨርፑል ይሰለፋል ተብሎ የነበረው ተከላካይ ጆ ጎሜዝ በዛሬው ውድድር አይሰለፍም ተብሏል። ከጉዳቱ በማገገም ላይ የሚገኘው ጆ ጎሜዝ ለቡድኑ በቅርቡ የመሰለፉ ነገር አሳሳቢ ነው። የ21 ዓመቱ ተከላካይ ጉዳት የደረሰበት የዛሬ ሁለት ወር ሊቨርፑል በርንሌይን ገጥሞ 3 ለ1 ባሸነፈበት ጨዋታ ነው።  ከቀዶ ጥገናው በማገገም ላይ ስለሚገኘው ተከላካይ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ሲናገሩ፦ «ለወጣቱም ኾነ ለእኛ ቅስም ሰባሪ ነው፤ ከጉዳቱ በፊት በድንቅ ይዞታ ላይ ነበርና» ብለዋል።

ሊቨርፑል በዛሬው ጨዋታ ብዙም ስጋት እንደማይገባው የተፋላሚው ቡድን አሰልጣኝ ተናግረዋል። ቺሊያዊው የዌስትሀም ዩናይትድ አሰልጣኝ ማኑዌል ፔሌግሪኒ፦ ሊቨርፑል ከሀገር ውስጥ ሌሎች ውድድሮች በጊዜ መሰናበቱ ፕሬሚየር  ሊግ እና ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ረድቶታል ብለዋል። በ24 ግጥሚያዎች 61 ነጥብ ይዞ በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ዘንጠረዥ አናት ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ ኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲን በአምስት ነጥብ መራቅ ይችላል ሲሉ የዌስት ሐም ዩናይትድ አሰልጣኝ መስክረዋል። ሊቨርፑል እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1990 ወዲህ የመጀመሪያቸው የሚኾነውን የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ በእጃቸው ለማስገባት በጠንካራ የማሸነፍ መንፈስ ውስጥ ናቸው ብለዋል።

Fußball Jürgen Klopp Liverpool FC v Crystal Palace - Premier League
ምስል Getty Images/AFP/P. Ellis

የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑል ከሊጉ ዋንጫ እና ኤፍ ኤ ካፕ ውድድሮች በጊዜ በመሰናበቱ ዘንድሮ ትኩረቱ ፕሬሚየር ሊግ እና ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ብቻ ነው። በአንጻሩ ተፎካካሪው ማንቸስተር ሲቲ ሊቨርፑል በተዋቸው ውድድሮች ላይ መሳተፉ ለቡድኑ ጫናውን ከፍ ያደርግበታል። «አራት ፉክክሮች ውስጥ ከገባ ቡድን ጋር ሲነጻጸር በኹለት ውድድሮች ብቻ ለሚሳተፈው ቡድን ይበልጥ ቀላል ነው» ብለዋል የዌስት ሐሙ አሰልጣኝ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲን በማነጻጸር። ማንቸስተር ሲቲ በሊጉ ዋንጫ ውድድር ተሳታፊ ከመኾኑ ባሻገር በኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ካለፈ ቡድኑ በፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ላይ የሚኖረው ጫና ከፍ እያለ ነው የሚሄደው።

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ባለፈው ግጥሚያ በኒውካስትል መሸነፋቸው ከፕሬሚየር ሊጉ ፉክክር ያስወጣናል ሲሉ ፈርተው እንደነበር አልሸሸጉም። ኾኖም ትናንት አርሰናልን 3 ለ1 መቅጣታቸው ግን ቡድናቸውን ዋንጫ ወደማደን ፉክክሩ ዳግም መልሶታል። «አኹን የኹለት ነጥብ ልዩነት ላይ ነን፤ ያም በመኾኑ የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ብዙም ማፍጠጥ አይጠበቅብንም» ብለዋል የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ። «ዌስት ሐም ዩናይትድ ሊቨርፑልን ቢያሸንፍ ምርጫችን እንደኾነ መካድ አልችልም፤ ግን ደግሞ ሊቨርፑሎችም አርሰናል እንዲያሸንፈን ሳይመርጡ አልቀረም» ሲሉ ፔፕ ጓርዲዮላ ሊቨርፑል እንዲሸነፍ ምኞታቸውን ገልጠዋል። የዛሬው ማታ ውጤት ምንም ኾነ ምን በደረጃ ሰንጠረዡ ዘጠነኛ ላይ ከሚገኘው ኤቨርተን ጋር ረቡዕ ዕለት  የሚያደርጉት ቀጣይ ጨዋታቸው የዋንጫ ፉክክሩ ቅርጽን መቀየሩ አይቀርም።

ቅዳሜ ዕለት ኒውካስትልን 1 ለ0 ያሸነፈው ቶትንሀም በ57 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ ማታ ሁደርስፊልድን 5 ለ 0 ያሸማቀቀው ቸልሲ 50 ነጥብ ይዞ ደረጃው አራተኛ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተለዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ላይስተር ሲቲን ያሸነፈበት 1 ለ0 ውጤቱ ተደምሮ እስካሁን ቡድኑ በአሰልጣኝ ኦሌ ጉነር በጊዜያዊነት ከተያዘ ጀምሮ በዐሥር ጨዋታዎች የሚረታው ጠፍቷል። 

ቡንደስ ሊጋ

Deutschland Bundesliga Bayer Leverkusen - Bayern München
ምስል Reuters/W. Rattay

ቅዳሜ ዕለት በባየር ሌቨርኩሰን 3 ለ1 ሽንፈት የገጠመው ባየር ሙይንሽን ወሳኝ ግብ ጠባቂ ከጉዳቱ አኹንም አላገገመም። ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር በደረሰበት የቀኝ አውራ ጣት ጉዳት ረቡዕ ዕለት ከሔርታ ቤርሊን ጋር ለሚኖረው የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ግጥሚያ አይሰለፍም። ባየር ሙይንሽን በሻምፒዮንስ ሊግ 16 ቡድኖች ፍልሚያ የዛሬ 15 ቀን ከሊቨርፑል ጋር ለሚያደርገው ግጥሚያ ግን ምናልባት ሙሉ ለሙሉ ድኖ ሊሰለፍ ይችል ይኾናል ተብሏል።  ተደጋጋሚ ሽንፈት የገጠመው ባየር ሙይንሽን በጀርመን ቡንደስሊጋ የደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ነው። ኹለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ጋር እኩል 42 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ግን ይበለጣል። 49 ነጥብ ይዞ መሪነቱን አኹንም ያስጠበቀው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ተጋጥሞ ነጥብ በመጣሉ በ9 ነጥብ ርቆ ለመምራት የነበረውን ዕድል አምክኗል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በነገው የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ግጥሚያ ቬርደር ብሬመንን ድል አድርጎ ይበልጥ ይነቃቃል ተብሎ ተገምቷል። ነገ እና ከነገ በስተያ 16 ቡድኖች ለጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ይጋጠማሉ።

በስፔን ላሊጋ በስድስት ነጥብ ርቀት ባርሴሎና የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ይገኛል። ዋነኛ ተፎካካሪው ሪያል ማድሪድ ትናንት አላቬስን 3 ለ0 ድል ቢነሳም 50 ነጥብ ከሰበሰበው ባርሴሎና በ8 ነጥብ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የኹለተኛ ደረጃውን አትሌቲኮ ማድሪድ በ44 ነጥብ ተቆናጧል።  

በሳምንቱ እጅግ አሳዛኝ የእግር ኳስ ዜና፦ የካርዲፉ የ28 ዓመት ወጣት እግር ኳስ ተጨዋች እና አብራሪውን አሳፍራ የዛሬ 15 ቀን ከራዳር እይታ የተሰወረችው የግል አውሮፕላን ባሕር ውስጥ ተከስክሳ መገኘቷ ነው። ለፈረንሳዩ ናንቴ ቡድን ይጫወት የነበረው አርጀንቲናዊው አጥቂ ኤሚሊያኖ ራውል ሳላ ተሳፍሮባት የነበረችው ማሊቡ N264DB አነስተኛ አውሮፕላን ደብዛዋ የጠፋው ሰኞ ጥር 13 ቀን 2011 ዓም ወደ እንግሊዙ ካርዲፍ ቡድን ሲያቀና ነበር። 

Artgentinien Emiliano Sala das Flugzeugwrack unter Wasser
ምስል Reuters/AAIB

አርጀንቲናዊው አጥቂ እና የ59 ዓመቱ አውሮፕላን አብራሪ ኢቦትሰን ምናልባት በሕይወት ይገኙ ይኾናል በሚል የነበረው የባሕር ላይ አሰሳ ሰዎቹ የመገኘታቸው ተስፋ በመመናመኑ የተቋረጠው ከአራት ቀናት ፍልጋ በኋላ ሐሙስ ቀን ነበር። ተስፋ ያልቆረጠችው የሳላ እህት  ሮሚና ግን ፍለጋው በግል እንዲቀጥል ለማስቻል ትናንት የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ አስጀምራ 371 ሺህ ዩሮ ደርሳ ነበር። ዳቪድ ሚረንስ የተባሉ የጠፉ አውሮፕላኖችን አፈላላጊ የግል ኩባንያ ሠራተኛ ለሳላ እህት በማዘን በፍለጋው ተባብረው የአውሮፕላኗ ስብርባሪን በሁለት ሰአት አሠሣ ማግኘት ችለዋል። «ያቺ ልጅ ርዳታ እንደሚያስፈልጋት ስለተሰማኝ ነው የተባበርኳት»  ሲሉም ቃለ መጠይቅ ላደረገላቸው 4 ኤስ ራዲዮ ተናግረዋል። የአውሮፕላኑን ስባሪ ያገኙትም ከባሕር ጠለል በታች 63 ሜትር ርቀት ላይ መኾኑን ገልጠዋል።  ሳላ ለካርዲፍ የፈረመው በቡድኑ ታሪክ ክብር ወሰን በሚባል የ15 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ነበር። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ