1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች

ዓርብ፣ ሰኔ 29 2010

በእስራኤል የሚኖሩ አንዳንድ ኢትዮጵያዉያን እንደሚሉት የእስራኤል መንግሥት ኢትዮጵያ አይሁዳዉያን ቤተሰቦቻቸዉ ጋር እንዳይቀላቅሉ አድርጓል በማለት ይወቅሳሉ። ይህም በአናሳዎቹ ኢትዮጵያዉያን ላይ የዘር ጥላቻ ያደርሳል የሚል ቅሪታ አሳድሮአል። ኢትዮጵያ የሚገኙት አንዳንዶቹ የአይሁድ እምነትን ቢፈፅሙም ሁሉም የሚታዩት እንደ ፈላሻ ሞራ ነዉ።

https://p.dw.com/p/30wc9
Israel Altstadt von Jerusalem | Felsendom
ምስል picture-alliance/NurPhoto/O. Messinger

በእስራኤል ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች

በ 1980 ዎቹ እና በ 90 ዎቹ ዓመት እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያዊያን አይሁዶችን በድብቅ በአየር አጓጉዛ ወደ ሃገርዋ አስገብታለች። ጥንታዊዎቹ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ከኢትዮጵያ ወደ አይሁድ ግዛት ለማምጣትና በእስራኤል ኑሮን እንዲለምዱ ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላርን አስከፍሎአል።  እስራኤል ዉስጥ በአሁኑ  ወቅት  ወደ 140,000 የሚሆኑ አይሁድ ኢትዮጵያዉያን ይገኖራሉ ተብሎ ይታመናል። ይህ ቁጥር በእስራኤል ከሚገኙት 8 ሚሊዮን ዜጎች ጋር ሲነጻፀር ኢምንት ነዉ። በእስራኤል የሚገኘዉ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ዳሌ ጋውላክ  የወጣት አይሁድ ኢትዮጵያዉያን በእስራኤል ኑሮን በተመለከተ አንድ ሁለቱን አነጋግሮ ተከታዩን ዘገባ ልኮልናል። 

« አያቴ ወደዚህ ለመምጣት ሕልም ነበረው።  ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ስለነበር መምጣት አልቻለም።  እናቴ ወደ እስራኤል የመጣችዉ አባቴ እኔ ከመወለዴ ከግማሽ ዓመት በፊት እዚህ ስለነበር ነዉ። አባቴ ወደዚህ የመጣዉ ይሁዲ በመሆኑና ወደ አይሁዳዉያን ማኅበረሰብ ቀረብ ማለት ስለፈለገ ሕልሙ ስለነበረ ነዉ። » 

የ 22 ዓመት ወጣቱ ሙሼ ነዉ። ሙሼ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ እስራኤል የመጣዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1990 ዎቹ መገባደጃ ላይ ነበር። ሙሼና ቤተሰቦቹ  እስራኤል እንደገቡ በእስራኤል ተዋህዶና ኑሮዉን ለምዶ ለመኖር እጅግ ከባድ ቢሆንባቸዉም «ኮቴል » በመባል የሚታወቀዉ እና በ 1970 ዎቹ እየሩሳሌምን ለማስለቀቅ በተካሄደዉ ጦርነት የወደመዉ የአይሁድ ቤተ መቅደስ ቅሪት አካባቢ መኖር በመፈለጋቸዉ ነዉ፤ ወደ  እስራኤል ዉስጥ ለመኖር ወሰኑት። ይህ በአሁን ጊዜ እየሩሳሌም ዉስጥ የሚገኘዉ ምኞት መግለጫ ግድግዳ የሚባለዉ የአይሁድ ቤተ-መቅደስ ቅሪት አካባቢ ያለዉ ቦታ የአይሁዳዉያን ቅዱስ ቦታ በመሆኑ ይታወቃል። 

« ወደ እስራኤል ስመጣ ሕጻን ስለነበርኩ  ቆየት ሲል ከማኅበረሰቡ ለመቀላቀል እና ሕይወቴን በቀላሉ ለመምራት ችግር አልገጠመኝም።  በአንፃሩ ወላጆቼ ትንሽ ችግር ገጥሞአቸዉ ነበር። በርግጥ የአይሁድ ቋንቋ «ሂብሩ»ን መናገር የተማሩት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ ፤መስራት የተማሩት ግን እዚህ እስራኤል ከመጡ በኋላ ነዉ። ቤተሰቦቼ  ደስ የሚሉና ጥሩዎች ናቸዉ። አይሁድ ኢትዮጵያዉያን በመላ እስራኤል በሚገኙ ከተሞች ዉስጥ ይኖራሉ። በሃይፋ ቲቤሪያ …በተለያዩ ቦታዎች»          

ሙሼ በእስራኤል የወታደራዊ አገልግሎት ግዳጁን አጠናቆአል። በአሁኑ ጊዜ አንድ ሬስቶራንት ውስጥ በኃላፊነት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ለማገልገል ክፍት የሥራ ቦታ እየፈለገ ነዉ። ሙሼ ስለ ብሔራዊ ዉትድርና ቆይታዉ ምንም ባይናገር ይመርጣል ይልቅዬ ለወታደሮች ምግብ ማብሰል ሥራ መሰማራት ቢችል መምረጡን ነዉ የሚገልፀዉ ።  

ሙሼ - ጥሩ ምግብ ማዘጋጀት ትችላለህ?»

«አዎ ፤ የማዘጋጀዉን ምግብ ሰዎች በልተዉ ጥሩ ምግብ ነበር ብለዉ አስተያየት ሲሰጡ ያስደስታል። በዚህ ሞያ ብዙ ሰዉ ትተዋወቃለህ፤  ለመግባባትም አይከብድህም ። ከሰዎች ምን አይነት አስተያየት እንደሚመጣ ሁሉ ታዉቃለህ፤ ብዙ ጓደኞች ይኖሩሃል። ወጥ ቤት ዉስጥ ጫጫታ ከሰማህ ጥሩ ነገር አለ ማለት ነዉ። የምግብ አብሳይነት ሞያ እንዲህ ነዉ ። በስራ ላይ ብዙ ዉጥረትና የሰዓት እጥረት አለ ። ሙሉ ቀን ስታበስል መዋል ይኖርብሃል። አንዳንድ ጊዜ በምግብ ቤቱ ብቻ ሳይሆን ከዉጭ በስልክ ጥሪ ምግብ እንታዘዛለን።» 

እንደ ሙሼ ጣዕም ያለዉ ምግብን ማሳናዳትን እየወደደና እያዳበረ የመጣዉ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብን እና በዓለም የተለያዩ ሃገሮች የሚወደዱ ምግቦችን በማዘጋጀታቸዉ ከሚታወቁት ከወላጅ እናቱ ተምሮ ነዉ። 

«ምግብ በማብሰል ረገድ እናቴ እስካሁን ብዙ ነገሮችን አስተምራኛለች። በዚህም ምክንያት የተለያዩ ምግቦችን ነዉ የምንመገበዉ። የራሳችን የሆነ የምግብ አበሳሰል ዘዴም አለን። ለምሳሌ እኔ በዶሮ ሥጋ ምግብን ማዘጋጀት እወዳለሁ። የቻይና ምግብን ብዙ ቅመም ሳልጨምር አበስላለሁ። ትንሽ ጨዉ ትንሽ ስኳር ሁሉ እጨምርበታለሁ። በጣም ጣፍጦ ይበላል» 

በማዕከላዊ እየሩሳሌም «ቤን ይሁዳ» በተባለዉ ጎዳና አካባቢ ሰዎች፤ የእቃ መግዣ ሱቆች ፤ ምግብ መሻ መደብርና የመዝናኛ ቦታን ይፈለጉ ይገባሉ። ሞሼና ይህን ዘገባ ያሰናዳዉ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ ዳሌ እየሩሳሌም ነዋሪ እሆነችዉ ሃና ጋር ቤት ሄደዉ ያወራሉ። የሃና ቤተሰቦች ወደ እስራኤል የመጡት በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓ.ም ነዉ። እንደ ሙሼ ሁሉ ሃናም የብሔራዊ ዉትድርና ግዳጅዋን አጠናቃለች።   

« ብሔራዊ ዉትድራናዬን ካጠናቀኩ በኋላ፤ ትምህርቴን መቀጠል ስለፈለኩ አንዳንድ ስራ እየሰራሁ ገንዘብ እያጠራቀምኩ ነዉ። መማር የምፈልገዉ የልብስ ቅድ ሞያን እና ሳይኮሎጂ  ነዉ።»ሙሼ ሕጻን ሳለ በቆዳ ቀለሙ ለየት ስለሚል ብቻ የዘር ጥላቻ ምን እንደሆን በማየት ነዉ ያደገዉ። ዘርን በተመለከተ ምን ያህል ጭፍን አመለካከት እንደነበር መግለፁ ከባድ ነዉ ይላል።  ሃና በበኩልዋ ምንም አይነት የዘር ጥላቻ ገጥሟት እንደማያቅ ነዉ የገለፀችዉ።

«ሕጻን እያለሁ ከሌሎች በመለየቴ ልጆች ሲስቁብኝ ምንም ግድ አይሰጠኝም ነበር። እኔ ደሞ በተራዬ ከእናነተ በተሻለ ፍጥነት መሮጥ እችላለሁ፤ ከአንተ የበለጠ ጠንካራ ነኝ ፤ ብዬ እመልስላቸዋለሁ ነበር። በርግጥም ልጅ ሳለሁ በጣም ጠንካራ ነበርኩ ብዙ ተደባድቤያለሁ። »

ሃና በበኩልዋ ምንም አይነት የዘር ጥላቻ አጋጥሞአት እንደማያዉቅ ተናግራለች። « በኛ እድሜ ክልልላይ በሚገኙት በአዲሱ ትዉልድ ላይ የዘረኝነት ጥላቻ አይታይም።  ግን እድሜያቸዉ ገፋ ያሉ ሰዎች እኛን እንደ ማኅበረሰቡ አካል አድርጎ ለመቀበል ትንሽ ይቸግራቸዋል። ፖሊስም ምንም ችግርና የጥርጣሪ ነገር ሳይኖር መንገድ ላይ አስቁሞ ፓስፖርት ይጠይቃል። ግን ይህ ለሁላችንም ሳይሆን አንዳንዶችን ብቻ ነዉ።» 

በእስራኤል የሚኖሩ አንዳንድ ኢትዮጵያዉያን እንደሚሉት የእስራኤል መንግሥት ኢትዮጵያ አይሁዳዉያን ቤተሰቦቻቸዉ ጋር እንዳይቀላቅሉ አድርጓል በማለት ይወቅሳሉ። ይህም በአናሳዎቹ ኢትዮጵያዉያን ላይ የዘር ጥላቻ ያደርሳል የሚል ቅሪታ አሳድሮአል። ኢትዮጵያ የሚገኙት አንዳንዶቹ የአይሁድ እምነትን ቢፈፅሙም ሁሉም የሚታዩት እንደ ፈላሻ ሞራ ነዉ። ፈላሻ ሞራ ማለት አያት ቅድመ አያቶቻቸዉ ከረጅም ጊዜ በፊት ክርስትና የተቀበሉ ናቸዉ። እነዚህ በእስራኤል የመመለስ ሕግ መሠረት ከአያቶቹ አንዱ ይሁድ የሆነ ግለሰብ እስራኤል የመግባትና ወድያዉም ዜግነት የማግኘት መብት አለዉ። ይሁንና ፈላሻ ሞራዎች እንዲህ አይነቱን መብት አያገኙም ወደ እስራኤል ለመግባት የመንግሥት ፈቃድ ማግኘት አለባቸዉ። 

የሙሼና ፤ የሃና ወላጆች የእስኤልን ባህልና የአኗኗር ዘዴን ለምደዉ መኖር ቢሹም ፤ የኢትዮጵያ የሃገር ባህል ልብሱን ጉዝጓዝ ቡና ዶሮ እንጀራዉን ግን ሊረሱት ሊያስቀሩት አልቻሉም። 

« ኢትዮጵያ ዉስጥ አዲስ ዓመት ሲሆን ፤ በዓሉን እዚህ በጥቂም ቢሆን እናከብራለን። እቤት ዉስጥ ከኢትዮጵያ የመጣና በባህላዊ መንገድ የተፈላ ቡናን እንጠጣለን፤ እንደንሳለን እንዘፍናለን።»

ሃና በተራዋ ፤ «እናቴ ከህጻንነቴ ጀምራ አማርኛ ቋንቋን አስተምራኛለች። የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ እንሰራለን ፤ በቋንቋችን ሙዚቃ እናዳምጣለን ፤ በዚህ መልኩ ባህሉን ከኛ ጋር ይዘን እንጠብቃለን ።  ባህላዊ የቡና ሥነ-ስርዓት በየቀኑ ቀርቶ አያዉቅም፤ አባቴ ከስራ ሲመለስ እናቴ ሁልጊዜ ቡና ታፈላለች። በወቅቱ  አሁን ብዙ በአላት ያሉበት በመሆኑ፤ አንዳንዶች የአበሻ ልብስ ይለብሳሉ፤ ለበዓል ወደኛ ጋር ብዙ እንግዳ ሊመጣ ስለሚችልም አብዛኛዉን ጊዜ ከቤት አንወጣም።»       

ሙሼም ሆኑ ሃና በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በሁሉም ዘርፍ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸዉ በየአቅማቸዉ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። አድማጮች በእየሩሳሌም የዶቼ ቬለ ዘጋቢ ዳሌ ግቫሌክ፤ በእስራኤል የኢትዮጵያዉያ አይሁድ ወጣቶች ሕይወትን የዳሰሰበት ቅንብር እስከዚሁ ነበር። ያቀረብኩላችሁ አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ። 

አዜብ ታደሰ / ዳሌ ጋውላክ

አርያም ተክሌ