1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ቴክኖሎጂን ከግብርና ጋር ያጣመሩትን ሴኔጋልና ዩጋንዳ

ረቡዕ፣ ኅዳር 13 2010

በአፍሪካ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በርካታ አርሶ አደሮች የአጅ ስልክ ባለቤቶች መሆናቸውን ከግምት የከተቱ የአፍሪካ ሀገራት ከግብርና ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው እያሰጧቸው ይገኛሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2o5QX
Symbolbild Düngemitteleinsatz Afrika
ምስል AFP/Getty Images

ቴክኖሎጂን ከግብርና ጋር ያጣመሩትን ሴኔጋልና ዩጋንዳ

ከሴኔጋል መዲና ዳካር በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲኪሎ የተሰኘች አነስተኛ መንደር ትገኛለች፡፡ መኖሪያቸውን በጎጆዎች ውስጥ ያደረጉትን የመንደሪቷን ነዋሪዎች የአንድ የቤተሰብ አባላት መሆን አለመሆናቸውን ለመለየት እምብዛም አይከብድም፡፡ በመንደሪቷ እዚህም  እጅብ ብለው የተኮለኮሉ ጎጆዎች በአንድ ቤተሰብ ጥላ ስር ያሉትን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ጎጆዎቹ ብዙ ቢመስሉም ሆኖ የመንደሪቷ ነዋሪዎች ቁጥር አንድ ሺህ እንኳ አይሞሉም፡፡ እነርሱን እንዲያስተዳድሩ በሰፈር ሹምነት የተመረጡት ደግሞ ደግሞ አሊዮን ዲጄባይ ይባላሉ፡፡ 

አሊዮን እንደ መንደሪቷ ነዋሪዎች ሁሉ አርሶ አደር ናቸው፡፡ ለውዝ እና ማሽላ ያመርታሉ፡፡ በሴኔጋል እንዳሉ አብዛኞዎቹ ገበሬዎች ሁሉ የዝናብ ወቅቱን የሚጀመርበትን ቀን ያለመታከት ይጠብቃሉ፡፡ በአካባቢያቸው ያለው የአየር ሁኔታ ሳይታሰብ መቅሰፍትነት ሊቀየር እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ “የአየር ሁኔታው መጥፎ ዕድላችን ነው፡፡ እህል በምታመርትበት ወቅት ትክክለኛው መረጃ ከሌለህ የምታርሰው በእውር ድንብር ነው ማለት ነው፡፡ እኔ እንደሚታየኝ ለአርሶ አደሮች በጣም ጠቃሚው ነገር የአየር ንብረትን የተመለከተ መረጃ ነው፡፡”

 በሴኔጋል በአብዛኛው የሚመረተው ምርት በዝናብ ላይ ጥገኛ በመሆኑ የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ አድርጎታል፡፡ መቼ እንደሚዘንብ ማወቅ በሰብል ምርት እና ስብሰባ ወቅት ያለውን አደጋ ለመቀነስ ቁልፍ ያደርገዋል፡፡ በተለምዶ የሴኔጋል አርሶ አደሮች የአየር ሁኔታውን ለመገመት ባህላዊ ዕውቀቶቻቸውን ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ዕውቀት በአየር ሁኔታ ጠቋሚ ነገሮች ላይ ይመረኮዛል፡፡ 

የ33 ዓመቷ አርሶ አደር ማሪያማ ኬይታ ስለ ሀገሬው ባህል ታስረዳለች፡፡ “በእኛ ባህል ወፎች ሲዘምሩ ወይም የባኦባብ ዛፍ ቅጠል ማውጣት ሲጀምር ያኔ ዝናብ በቅርቡ መዝነብ እንደሚጀምር እናውቃለን” ትላለች ማሪያማ፡፡ እነዚሀን ጠቋሚ ምልክቶች እና ትውፊቶች የተማሩት ከቀደምት አባቶቻቸው እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ማሪየም አሁን በሰፈሯ መግቢያ ላይ ያለው የባኦባብ ዛፍ ቅጠሎች ማቆጥቆጥ ሲጀምሩ ተመልክታ ዝናብ እንደሚከተል መተንበይ አቁማለች፡፡ ሁኔታዎች ሁሉ እንደቀድሞው አይደሉም፡፡ 
“በርካታ ነገር ተለውጧል፡፡ ቀደም ሲል ብዙ ዝናብ እናገኝ ነበር፡፡ በርካታ ዛፎችም ነበሩ፡፡ አሁን ግን ያለው ውሃ ትንሽ ነው፡፡ ብዙ አይዘንብም፡፡ አርሶ አደሮች ያለውን ትንሽ ውሃ ተጠቅመው ለማምረት ተገደዋል፡፡”
በማሪየማ መንደር ሲኪሎ ዝናብ ከምንጊዜውም በበለጠ ውድ ነገር ሆኗል፡፡ መንደሮቿ በተለወጠው የአየር ሁኔታ ተስፋ በቆረጡበት በዚህ ወቅት ተስፋቸውን ከሚያድስ ቴክኖሎጂ ጋር ተዋውቀዋል፡፡ የቴክኖሎጂው ባለቤት የሴኔጋል ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን እና ሜትሮሎጂ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ የአየር ንብረት ለውጥ ከአገልግሎት ውጭ ያደረጋቸውን ባህላዊ የአየር ሁኔታ ጠቋሚዎችን የተካ ቴክኖሎጂ አምጥቶላቸዋል፡፡ 

Senegal, Alioune Djaby
ምስል E. Landais

መቀመጫውን በመዲናይቱ ዳካር ያደረገው የሜትሮሎጂ ድርጅቱ በሳተላይት እና ከራሱ ጣቢያዎች የሰበሰባቸውን የአየር ሁኔታዎችን የሚያመለክቱ መረጃዎች አቀናብሮ ለአርሶ አደሮቹ በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ይልክላቸዋል፡፡ ሲኪሎ ይህን የድርጅቱን የአጭር የጹሁፍ መልዕክት አገልግሎት መጠቀም የጀመረችው የዛሬ ሰባት ዓመት ግድም ነው፡፡ በዚህም በሴኔጋል ካሉ መንደሮች የመጀመሪያዋ ሆናለች፡፡ አርሶ አደሯ ማሪየማ አገልግሎቱን ከሚጠቀሙት መካከል ናት፡፡ 

“ዘጠና ስምንት በመቶ ትክክል ነው፡፡ መልዕክቶቹ ከበጋው ወቅት በስተቀር በማንኛውም ጊዜ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ መልዕክቶቹ ሲመጡ እንደሚከተለው ሊነበቡ ይችላሉ፡፡ ‘ትንበያ፤ በካፋሪን አካባቢ በሁለት ሰዓት ውስጥ ዝናብ ሊዘንብ ይችላል’፡፡ እንደዚህ ነው መልዕከቶቹን የምናገኘው፡፡”
ማሪየማ አጭር የጹሁፍ መልዕክት ትንበያዎችን ማግኘት ከጀመረች በኋላ በግብርና ምርቷ ላይ ለውጥ መምጣቱን ትናገራለች፡፡ መረጃውን እየተጠቀመች የምታርሰው የለውዝ እርሻዋ በሌላ ቦታ ካለው ማሳዋ በ1.5 ቶን የበለጠ ምርት አስገኝቶላታል፡፡  

በሴኔጋል ዛሬ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያን ከመጠቀም ቀጥሎ ተራ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ወሳኝ መሳሪያዎች ሆነዋል፡፡ በእነዚህ ታግዞ የሚመጣ የተሻለ ምርት ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና መረጋጋጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የሀገሪቱ የግብርና ባለሙያዎች እንደሚገምቱት በጎርጎሮሳዊው 2050 በሴኔጋል የለውዝ ምርት ከአምስት እስከ 25 በመቶ ይቀንሳል፡፡ 

በሴኔጋል የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ማምጣቱን ከጀመረ መቆየቱን የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ድርጅቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በድርጅቱ የአየር ንብረት ተመራማሪ የሆኑት ኦስማኔ ንዴይ ባለፉት 10 ዓመታት በሳህል አካባቢ የተመዘገበው የዝናብ መጠን ከምንጊዜውም አነስተኛ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

M-Farm Preisinformationssystem in Kenia
ምስል Sven Torfinn/MFarm

እንደ ሴኔጋል ሁሉ የምስራቅ አፍሪካዋ ኡጋንዳም የአየርን ንብረት ለውጥን ዳፋ ከቀመሱ ሀገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ ለሀገሪቱ ሁነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሆነው የቡና ንግዷ የከባቢ አየር ለውጡ ተጠቂ ሆኗል፡፡ በአፍሪካ ኢትዮጵያን ተከትላ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ቡና ላኪ ሀገር የሆነችው የኡጋንዳ የቡና ማሳዎች በአየር ንብረት ለውጥ እና ድርቅ ተጎድተዋል፡፡ የብሪታንያው የግብረ ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም መረጃ እንደሚያመለክተው አምስት ሚሊዮን የሀገሪቱ ዜጎች ኑሯቸው ከቡና ምርት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ 
በኡጋንዳ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተው የዝናብ እጥረት የቡና አምራቾችን ብቻ ሳይሆን ሀገሬው ለምግብነት የሚጠቀምባቸውን ሰብሎች የሚያመርቱ አርሶ አደሮችንም ተፈታትኗል፡፡ ሪቻርድ ሙዬንጎ በቆሎ አምራች ናቸው፡፡ 

“ቀደም ሲል ለስምንት ወራት ዝናብ እናገኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ሶስት ወራት ወርዷል፡፡”
ኡጋንዳ የአየር ንብረት ለውጥ በአርሶ አደሮቿ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተመልክታ ዝም አላላችም፡፡ ይልቅስ እንደ ምዕራብ አፍሪካዋ ሴኔጋል መፍትሄ አበጅታለች፡፡ ሀገሪቱ ከሳተላይት የሚገኙ ግብርና ነክ መረጃዎች ለአርሶ አደሮች በሚገባ መልኩ ተጠናቅረው የሚቀርቡበት ፕሮጀክት ዘርግታለች፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ስር ሙዬንጎን ጨምሮ 350 ሺህ አርሶ አደሮች ታቅፈዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የሙቀት፣ እርጥበት እና የጸሀይ ብርሃን የቆይታ ጊዜን ለሶስት ዓመታት ያህል እየተከታተለ  የመተንተን ዓላማን አንግቦ ስራ የጀመረ ነው፡፡

ለፕሮጀክቱ በግብዓትነት የሚያገለግሉ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የኡጋንዳ የግብርና ቴክኒክ እና ገጠር ትብብር ማዕከል ሰራተኛ ወደ ሙዬንጎ ማሳ ብቅ ብለው ነበር፡፡ ሰራተኛው ማሳው የሚገኝበትን ትክክለኛ ቦታ እና ሌሎችም መረጃዎች ከሰበሰቡ በኋላ መቀመጫውን በመዲናይቱ ካምፓላ ወዳደረገው የፕሮጀክቱ ዋና ጽህፈት ቤት ይልካሉ፡፡ እንደዚህ ከየቦታው የተጠናቀረውን መረጃ የሚቀበሉት የፕሮጀክቱ ሰራተኞች የአካባቢውን የአየር ሁኔታ መረጃን ለመገምገም እና ለመተንተን ይጠቀሙበታል፡፡ 
ጄራልድ ኦቲም የፕሮጀክቱ የኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ነው፡፡ 

“ይህ ጥሬ መረጃ ለአርሶ አደሮች ውስብስብ እና ለመቀጠምም ከባድ ነው፡፡ ሰለዚህ እኛ ከእርሻ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ይህን መረጃ ለአርሶ አደሩ በሚስማማ መልኩ በጽሁፍ አዘጋጅተን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው እንልካለን፡፡” 

ለቴክኖሎጂ ውዴታ ያላቸው ወጣት ባለሙያዎችን ይህን የአሰራር ሂደት በማሳቸው ላሉ አርሶ አደሮች ያስረዷቸዋል፡፡ ካሮል ካኮዛ 4.5 ሚሊዮን ዮሮ ያስወጣው የዚህ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ “ይህ ፕሮጀክት ቴክኖሎጂን ያማከለ መሆኑ በርካታ ወጣቶች ወደ እርሱ እንዲሳቡ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ወጣቶች ቴክኖሎጂ ይወዳሉ፡፡ ፕሮጅክቱ ደግሞ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና የመልዕክት ልውውጦችን የሚጠቀም ቴክኖሎጂ አለው፡፡ ይህ ለእነርሱ ይህ ሁነኛ ቦታ ነው፡፡”
ሙዬንጎ ማሳውን ለቀጣዩ የዝናባማ ወቅት ዝግጁ ሲያደርግ በልበሙሉነት ነው፡፡ ከፕሮጀክቱ የአየር ሁኔታው ምን ሊመስል እንደሚችል መረጃ አግኝቷልና- አባባሉስ “መረጃ ኃይል ነው” አይደል የሚለው፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ