1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት ያልተሰጠው ሀብት

ረቡዕ፣ ጥር 22 2011

የአሳ ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ ብዙዎች ይስማማሉ። ዘርፉ መስጠት በሚችለው አቅም ለሀገሪቷ የሚሰጠውን አስተዋጽኦ እየሰጠም እንዳልሆነ ይነገራል። 

https://p.dw.com/p/3CSSG
Kamerun Hafen von Idenau
ምስል DW/F. Muvunyi

ስጋት ያጠላበት የአሳ ሀብት

በኢትዮጵያ የሚገኙት ብዙዎቹ ሀይቆች የአሳ ምርትን መስጠት እያቆሙ እንደሆነ ይነገራል። ችግሩ ቀደም ሲል ያለ ቢሆንም እንደ ችግር ታይቶ፤ ሳይቀረፍ እነሆ ዛሬም የበለጠ አፍጦ መጥቷል ሲሉ ብዙዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ። የአሳ ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ ብዙዎች ይስማማሉ። ዘርፉ መስጠት በሚችለው አቅም ለሀገሪቷ የሚሰጠውን አስተዋጽኦ እየሰጠም እንዳልሆነ ይነገራል። ዶ/ር አበበ አመሀ በኢትዮጵያ ኔዘርላንድ የግብርና እድገት ፕሮግራም የአሳ እርባታ አስተባባሪም በዚህ ይስማማሉ። የአሳ ሀብትን ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽኦ አላበረከተም ይላሉ። በሀገሪቷ በአመት እስከ 94,000 ቶን ማምረት እንደሚቻል ቢታመንም፤ በ2010 ዓ.ም ማምረት የተቻለው ግን 56,000 ቶን ብቻ ነው ብለዋል። “የአሳ ሀብት ልማት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች የግብርና መስኮች ጋር ስናነጻጽረው የሚጠበቀውን ያህል አስተዋችኦ አድርጓል ማለት አይቻልም። የአሳ ሀብት ልማት በአለም ላይ  ፈጣን ዕድገት እያሳየ ያለ ዘርፍ ነው። በኢትዮጵያ በአሳ ሀብት ዘርፍ የሚጠበቀውን ያህል ያልተጠቀመች መሆኑን ያሳያል።” የማምረት አቅሟ ካለፉት ዓመታት ቢጨምርም፤ በንጽጽር ሲታይ ግን የተጠቃሚ ፍላጎት ለማርካት በቂ አይደለም እንደ ዶ/ር አበበ አገላለጽ። በኢትዮጵያ የአሳ ተመጋቢ የነስፍ ወከፍ ፍጆታ በአማካይ 0.5 ኪሎ ግራም ይደርሳል። ይህ ማለት አቅርቦቱ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነና ፍላጎቱን ለማርካት በቂ እንዳልሆነ ዶ/ር አበበ ይገልጻሉ። “በዓመት የአለም አማካይ የነፍስ ወከፍ የአሳ ተመጋቢ ፍጆታ ከ20 ኪሎ ግራም በላይ ነው። በአፍሪካ ስናይ 10 ኪሎ ግራም ነው።  በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉት የሚባሉ ሀገሮች ተብለው የተፈረጁት አማካኝ 8 ኪሎ ግራም ነው የቀርብ ጊዜ ጥናት እንደሚጠቁመው። በኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ 0.5 ኪሎ ነው የሚደርሰው። ይሄ ማለት ያሉን ወንዞች፣ ሀይቆችና ግድቦች የአሳ ምርት የሀገሪቱን ፍላጎት ለማርካት በቂ አይደለም።”በኢትዮጵያ 40,000 ያህል አሳ አስጋሪዎች አሉ። የምርት መጠን መቀነሱ እንደምክንያት የሚያነሱት ዘርፉ ስርዓት ይዞ እየተሰራ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። ከተፈጥሮ አሳ ማስገር ወደ አሳ ማርባት መሻገርም አማራጭ እንደሆነም ዶ/ር አበበ ይጠቅሳሉ።
“ጣና፣ ዝዋይ፣ አርባ ምንጭ፣ አባያ፣ ጫሞ፣ አዋሳ፣ ከወንዞች ባሮ፣ ከግድብ ተከዜ በርካታ የአሳ ማስገር ስራዎች ይካሄዳሉ። በብዛት የሚመረትባቸው የጣና ሀይቆችና የዝዋይ ሀይቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።” የጤና ባለሙያ እና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ መሰለ በገበያው ላይ ያለውን እጥረት በማየት ወደ አሳ ንግድ እንደገቡ ይናገራሉ። በሰው ሰራሽ ሀይቅ ውስጥ አሳ የማርባት ንግድ ውስጥ ለመሰማራት እንቅስቃሴም ላይ ናቸው። የአሳ ምርት አቅርቦቱና ፍላጎት አልተጣጣመም በሚለው ሀሳብ አቶ ተስፋዬም ይስማማሉ። “አቅርቦትና ምርት አልተጣጣመም። አቅርቦት ብዙም የለም። ለጊዜያዊ ጥቅም በሚል ያልሰለጠኑ አስጋሪዎች ናቸው ስራውን እየሰሩ ያሉት። ይሄን በማየት በሰው ሰራሽ ግድብ አሳን በማርባት ለገበያ ለማቅረብ እቅድ ላይ ነን። በሌላ የአለም ሀገራት ይሰራል። እኛ ሀገር ለማስተዋወቅ አዋጭነቱንና ገበያውን እያጠናን ነው።” የአሳ ሀብት ልማት ድርጅት በአሁኑ አጠራር ኢሀይ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የአሳ ምርት ገበያ ድርጅት ከመንግስት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል ከተቀየሩት ድርጅቶች አንዱ ነው። በአሳ ሀብት ዘርፉ ችግሮች እንዳሉ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ተካ ይናገራሉ። አሳ አስጋሪዎች በህገ ወጥ መልኩ ለምግብ ያልደረሱ አሳዎችን እንደሚያሰግሩም ጠቁመዋል። “እራሳችን እያመረትን አይደለም። ከሚያመርቱ ማህበራት ከሚረከቡ ነጋዴዎች አሉ። የኛ ድርሻ ተረክበን ለምግብነት አዘጋጅተን የምናከፋፍል ይሆናል። መንግስት በአሳ ዙሪያ ያወጣው ፖሊሲ ጥሩ ቢሆንም ችግሮች አሉ። ብዙ ወጣቶች በህገ ወጥ ይሁን በህጋዊ መንገድ ያሰግራሉ። በዚህም ጫጩት የሆኑ አሳዎች በመረብ ይወጣሉ። ምርቱ ላይ ችግር እየተፈጠረም ይገኛል።” መንግስት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ ጠቁመው፤ ችግሩን ለመቅረፍም ሀይቆቹ ምርት መስጠት አቁመው ለተወሰነ ጊዜ ቢዘጉና ጥበቃ ቢደረግላቸው ሲሉ አቶ አስናቀ አክለዋል።

Indien Sunderbans
ምስል picture-alliance/Pacific Press/S. Paul

 

ነጃት ኢብራሂም

እሸቴ በቀለ