1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አርቲስት አብነት አጎናፍር

እሑድ፣ ታኅሣሥ 12 2007

እስካሁን ሦስት ተከታታይ አልበሞችን አሣትሟል። በቅርቡ ለአድናቂዎቹ ጆሮ ያደረሰው ሲዲ «አስታራቂ» ይሰኛል። ዜማ እና ግጥም ደራሲ፣ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ መሣሪያ ተጨዋች እና ድምፃዊ ነው። አርቲስት አብነት አጎናፍር።

https://p.dw.com/p/1E8AE
Artist Abinet Agonafer
ምስል AB

የዘፈን ግጥሞችን እና ዜማዎችን ይደርሳል። የሙዚቃ መሣሪያዎችን ይጫወታል፤ ያቀናብራል ብሎም ሲዲዎችን ያሳትማል፤ ድምፃዊም ነው። ከኅብረተሰቡ ጋር በስፋት ያስተዋወቀውን የመጀመሪያ አልበሙን ያቀረበው በ1995 ዓም ሲሆን፤ የአልበሙ መጠሪያ «ድብቅ ውበት» ይሰኛል። በ1999 ዓም «ውለታ» የሚል ስያሜ የሰጠውን 2ኛ አልበሙን አስከተለ። ዘንድሮ ሦስተኛ አልበሙን « አስታራቂ» በሚል ርእስ ይዞ ዳግም ብቅ ብሏል፤ አርቲስት አብነት አጎናፍር።

ድምፃዊ አብነት አጎናፈር የሙዚቃ ዓለምን የተቀላቀለው ገና በልጅነቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ነው።

አርቲስት አብነት አጎናፈር
ምስል AB

አርቲስት አብነት ከሱዳን አንስቶ እስከ ማሊ፤ ከዓረብ ሀገር ሙዚቃዎች እስከ ሮክ የሙዚቃ ስልት በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የሙዚቃ ስልቶችን ማድመጥ፣ ማጣጣም እንደሚያስደስተው ይገልጣል። የሀገረሰብ የሙዚቃ ስልቶችን ከውጭሀገር የሙዚቃ ቅኝቶች ጋር አጣጥሞ በአዲስ ለማቅረብም የተለያዩ ሙከራዎችን ያደርጋል።

አብነት የሙዚቃ ችሎታውን ከየካቲት 23 ወይንም ወሠን ሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በመስተዋት የኪነጥበብ ማዕከል ካሟሸ በኋላ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት እና ድምፃዊ ሙያ ወደ ዓረብ ሀገር ያቀናል።

አብነት ከዓረብ ሃገራት የሙዚቃ ሥራ ቆይታው ባሻገር፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ ፣ የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት እና አውሮጳ ውስጥም ተዘዋውሮ ሥራዎቹን በተለያየ ጊዜ አቅርቧል። በአንድ ወቅት ግሪክ የሙዚቃ ሥራውን ለማቅረብ በቅርብ በሚያውቀው ሰው ይጋበዝና ይመጣል።

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ ከታች የሚገኘውን የድምፅ ማጫወቻውን ይጫኑ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ