1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የፕላስቲክ አወጋገድ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 5 2010

ዓለማችን በፕላስቲክ እየታፈነች መሆኑን ከሰሞኑ የተመድ አመክልቷል። የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚለው በየዓመቱ አምስት ትሪሊዮን የዕቃ መያዣ ፕላስቲክ ጥቅም ላይ ይውላል። ፕላስቲክን መጠቀሙ ሳይሆን ዋናው ችግር አወጋገዱ መሆኑን ልብ ይሏል። በየቦታው መጣሉ ለእንስሳት ሕይወትም ሆነ ለአፈር ውኃው ጤንነት ጣጣው ከፍተኛ ነው።

https://p.dw.com/p/2zPFT
Indien Umwelt Verschmutzung Recycling Energie
ምስል Getty Images/AFP

አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮችን አለመጠቀም ይመከራል፤

በጎርጎሪሳዊው የዘመን ቀመር በየዓመቱ ሰኔ አምስት ቀን የአካባቢ ተፈጥሮ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይታሰባል። የዘንድሮውም ባሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ ታስቦ ነበር። የተመድ በዚህ ዓመት ዕለቱ ሲታሰብ ፕላስቲክ ብክለትን እናሸንፍ የሚል ፅንሰ ሀሰብ ነበር መሪ ቃሉ። የመንግሥታቱ ድርጅት በዕለቱ ይፋ ያደረገው ዘገባም ዓለም በፕላስቲክ ውዳቂ ወይም ውጋጅ ልትዋጥ ቀርባለች የሚለውን ስጋት ያሳየ ነው። እንደዘገባው በየዓመቱ አምስት ትሪሊየን የዕቃ መያዣ ፕላስቲክ ጥቅም ላይ ይውላል። ፕላስቲኩን መጠቀሙ ሳይሆን ዋናው ችግር በአብዛኛው ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ አለመደረጉ የተለያዩ ጠንቆችን ማስከተሉ መሆኑንም ዘገባው ይዘረዝራል። ባህር ላይ የሚጣሉት የባህር እንስሳት ቀለብ መሆናቸውን፤ በየጎዳናው የሚጣሉት የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን መድፈናቸውን፤ በየእርሻ ማሳው እና መሬቱ መውደቃቸውንና በእንስሳትም መበላታቸውን ይጠቅሳል። ይህ ደግሞ በአንድም በሌላ መንገድ ወደሰዎች አካላት በተለያየ ምግብ አማካኝነት እየገባ ለጤና ጠንቅ መሆኑንም ያወሳል። እጅግ በርካታ ፕላስቲክ በጥቅም ላይ እንደመዋሉ በያለበት የሚወድቀውን ለመቀነስ መልሶ ጥቅም ላይ የማዋያ ጥረቶች ቢኖሩም ከፕላስቲክ ከተሰሩ ቁሳቁሶች 79 በመቶው ግን እንዲሁ እንደሚጣልም ዘገባው አመልክቷል። በርካታ የላስቲክ ጥርቅም የውኃ መውረጃ ቱቦዎችን የዘጋባቸው እንደ ኒው ዴሊህ ከተማ ያሉ ሌሎች የአዳጊ ሃገራት ከተሞች ፕላስቲክ በየቦታው የመጣሉ ጣጣ ለተላላፊ በሽታ መስፋፊያ ምክንያት ሊፈጥር የመቻሉ ማሳያዎች ተደርገው ቀርበዋል።

የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በአግባቡ ሥራ ላይ በማይውልባቸው ሃገራት ደረቅ ቆሻሻ የሚወገድበት መንገድ መሠረታዊ ችግር መሆኑ የሚታይ ነው። ፕላስቲክን ስንመለከት በቀላል ዋጋ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በነፃ መገኘቱ አገልግሎቱን ተፈላጊ አድርጎት ይታያል። ፕላስቲክ አካባቢን እየበከለ ነው በሚል ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስቡት ወገኖች ችግሩ ያለው መጠቀሙ ላይ ሳይሆን በየቦታው እንዳገኙ መጣሉ ነው በማለት ሰዎች በእጃቸው የገባውን ፕላስቲክ የሚያስወግዱበትን መንገድ እንዲያስቡበት ይመክራሉ።  ኢትዮጵያ ላይ የፕላስቲክ አወጋገድ ምን ይመስላል?   በኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአካባቢ ብክለት አያያዝ ምርምር ክፍል ዳይሬክተር አቶ ያለምሰዉ አደላ፤ የፕላስቲክ ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ የቆሻሻ አወጋገዱ የሚያነጋገር መሆኑን ነው ያመለከቱት።

«እንግዲህ አሁን ፕላስቲክን ነጥለን ከማየታችን በፊት ባጠቃላይ የደረቅም ሆነ የፍሳሽ ውጋጆች እንዴት ነው የሚያዙት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚለውን ያው ውጋጅ የሚለውን ቃል የመረጥኩት (ቆሻሻ የሚለው ሳይንሳዊ አይደለም። ቀጥታ ዌስት ሲተረጎም ቆሻሻ ተብሎ ነው ውጋጅ ያልኩት)። ባጠቃላይ በዚህ ረገድ በጣም ኋላ ቀር የሆነ የደረቅም ሆነ የፍሳሽ ውጋጅ አያያዝ ሥርዓት ነው ያለን። ይሄ ጠቅለል ያለ ዕይታው ነው። እንግዲህ ነጥለን  ካላቸው ባህሪም ተነስተን ፕላስቲኮች እንዴት ነው እዚህ ሀገር የሚያዙት የሚለውን ስናይ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ነው የምናስቀምጣቸው ጥቅም ከሰጡ በኋላ። »

Greenpeace-Protest vor dem G7-Gipfel in Kanada
ምስል © David Kawai / Greenpeace

እንዲያም ሆኖ በመጠኑ በትንንሽ የጎጆ ኢንደስትሪ በሚባል ደረጃ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁመዋል። አቶ ደሳለኝ ፍሬው የጤና ቀበና ግንፍሌን እናጽዳ ማህበር ዳይሬክተር ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ አይነቶች በሕግ ሳይቀር ተደንግገው መቀመጣቸውን በመጥቀስ ዋናው ግን አወጋገዱ ላይ ያለው ችግር ነው የሚለውን ተመሳሳይ ሀሳብ ያነሳል።

«የቀድሞው የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አዋጅና ሕጎችን ስስ ፕላስቲኮችን እንዳይወጡ የሚከለክል የሚያግድ ቢያወጣም የዚህ የስስ ላስቲክ ጉዳይ በሀገራችን አሁን ትልቅ ችግር ነው። ትንሽ ደግሞ ከዚህ ከፋብሪካዎች ማደግ፣ ከኢንዱስትሪዎች ከማሸጊያዎች በመስፋፋቱ የማዕድን ውኃዎችም በየቦታው በመብዛታቸው፤ ከዕለት ወደ ዕለት ደግሞ የፕላስቲክ ውጤቶች እና ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን ብዙም የዳበረ ባለመሆኑ በስፋት ይታያል። ወንዞቻችን ሐይቆቹ በአጠቃላይ የውኃ አካላትም፤ የውኃ መውረጃ ተፋሰሶችም በስፋት የዚህ ችግር ወይም ደግሞ በቆሻሻ  አያያዛች ሥርዓታችን ምክንያት ችግሩ ሰፊ ነው።»

ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረግ ጥረት መኖሩን ቢያመለክትም በኅብረተሰቡም ዘንድ ግን እኩል ግንዛቤ ማለት እንደማይቻል አስገንዝቧል። የሕግ ማዕቀፉም አስገዳጅነት እና ተፈፃሚነት ስለሚጎለውም የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት እንደሚቸግርም አመልክቷል።

Thailand Wal verendet an mehr als 80 Plastiktüten im Magen
ታይላንድ ፕላስቲክ የተመገበ አሳነባሪ ምስል Reuters

የፕላስቲክ ዕቃዎችን በየቦታው እንዳይጣሉ የሚደረገው ምክር እና ቅስቀሳ በአዳጊ ሃገራት ብቻ ሳይሆን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታቸው የተስተካከለ በሚባሉት የበለፀጉ ሃገራትም በአሁኑ ወቅት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአውሮጳ ኅብረት ደረጃ ጥቂት የማይባሉ የኅብረቱ አባል ሃገራት ውኃ መሸጫ የፕላስቲክ መያዣዎችን ተጠቃሚው መልሶ እንዲሰጣቸው ተጨማሪ ሳንቲም ደምረው እንዲያስከፍሉ በቅርቡ መመሪያ ተሰጥቷል። ጀርመን ይህን የፕላስቲክ ምርት ዳግም ሥራ ላይ ከሚያውሉ ሃገራት ግንባር ቀደሟ ናት። አብዛኛዉ የምግብ ሸቀጥም ሆነ የተለያዩ ገበያ አዳራሾች ዕቃ መያዣ ላስቲክ የሚሻ ዳጎስ ያለ ሳንቲም እንዲከፍል ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ ብዙዎች የየራሳቸውን ዕቃ መያዣ ከቤታቸው ይዘው እንዲወጡ እያደረገ ነው። ፕላስቲክ መጠቀም ጥንቃቄ ይደረግበት የሚለው ግፊት በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በማገናዘብ ነው። አቶ ያለምሰው ጥቂቱን ያነሳሉ፤

« ፕላስቲኮች እንግዲህ አሁን ምንድነው ያላቸው አደጋ በብዙ መልኩ ከፍተኛ ነው። አካባቢን ከማቆሸሽ ባለፈምእነዚህ ፕላስቲኮች  እየተመገቡ ብዙ ከብቶች በዓለም ላይ እንደሚሞቱ መረጃዎች አሉ።»

ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ደረጃ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ የሚመረቱት አይነት በግልፅ የተቀመጠ ነው። ይህንን ከኅብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ልማድ ጋር በማዋሐድ በየቦታዉ የሚጣለውን የፕላስቲክ ውጋጅ ብዛት ለመቀነስ ይረዳል ያሉትንም እንዲህ ይዘረዝራሉ አቶ ያለምሰው።

Indien Plastikverschmutzung
ሕንድን ያጥለቀለቃት ፕላስቲክምስል picture-alliance/AP Photo/A. Qadri

የጤና ቀበና  ግንፍሌን እናፅዳ ማህበር እንዲህ ያለው የባህሪ ለውጥ ከልጅነት እንዲመጣ ተማሪዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ገልጾልናል። ባለፈው ሳምንትም ይህንኑ ለማጠናከር ሞክረዋል። በአሁኑ ጊዜም አንዳንድ የፕላስቲክ ዕቃዎችን እየሰበሰቡ ዳግም ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሞክሩ ድርጅቶች መኖራቸዉንም ሳይገልፅ አላለፈም።

ፕላስቲክን ተጠቅሞ የማስወገዱ ጉዳይ ጥንቃቄ እንዲረግበት አበክሮ መምከሩ እንዳለ ሆኖ  አቶ ያለምሰው አደላ ዘመኑ ፕላስቲክን ይበልጥ መጠቀምን የሚጋብዝ መሆኑን ያስገነዝባሉ። የእሳቸው መስሪያ ቤት የምርምር ዘርፍም ፕላስቲክን ወደሌላ ጥቅም ማዋል የሚያስችል ምርምሩን እያገባደደ መሆኑን እና በቅርቡም ይፋ እንደሚደረግም ጠቁመዋል። የተመድ ዘገባ እንደሚያሳየው በዓለም ከሚመረተው 9 ቢሊየን ቶን ፕላስቲክ ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውል የተደረገው ዘጠኝ በመቶው ብቻ ነው። በመላው ዓለም በየደቂቃው 10 ሚሊየን ፕላስቲክ ጥቅም እንደሚውል የሚያመለክተው ጥናት ፕላስቲኮቹ ተቀጣጥለው ቢያያዙ ዓለምን ሰባት ጊዜ ሊጠቀልሉት እንደሚችሉ አመልክቷል።

 ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ