1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣት በጎ ፈቃደኞች

ዓርብ፣ ጥር 3 2011

ወጣት በጎ ፈቃደኞቹ የልማት ስራዎችን በመስራት፤ አረጋዊያንን በመንከባከብና ድጋፍ በማድረግ፤ የተቸገሩትን በመርዳት አገልግሎት ይሰጣሉ።

https://p.dw.com/p/3BOTN
Äthiopien Addis Ababa - Freiwillige des Roten Kreuz
ምስል R. Mekuria/B. Negatu

በጎ ፈቃደኞችን ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ለሚያደርጉት ተግባር ግንባር ቀደም ይላቸዋል፤ የኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማህበር።  በጎ ፍቃደኞቹ የሰብአዊና የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ናቸው። አጠቃላይ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃደኞች ቁጥር 47,000 ደርሷል። ወጣት በጎ ፈቃደኞቹ የልማት ስራዎችን በመስራት፤ አረጋዊያንን በመንከባከብና ድጋፍ በማድረግ፤ የተቸገሩትን በመርዳት አገልግሎት ይሰጣሉ። ሰዎችን መርዳት ያስደስተኝ ነበር ይላል ሮቤል መኩሪያ። በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 13 ዓመት ሆኖታል። ሮቤል በተደጋጋሚ ይሰማው የነበረው የአምቡላንስ ጥሪ ድምጽ በውስጡ ጥያቄ ፈጠረበት፤ ጥያቄውም መልስ አግኝቶ ወደ በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ለመግባት ምክንያት እንደኾነው ይናገራል።  "ሰዎችን መርዳት ያስደስተኛል። አምቡላንስ ሲጮህ እሰማ ነበር። ሲጮህ በእኔ ውስጥ የፈጠረው ስሜት አለ። ምን እንደሚሰራ ስጠይቅ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰውን ይረዳል ተባልኩ፤ ገባሁ። ምንም ጥቅም ሳታገኝ ያለሽን ነገር መስጠት ነው። አምቡላንስ ላይ እሰራ ነበር፤ የጽዳት ዘመቻዎች ላይ እሳተፋለሁ። የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ የሚሰጥበት ቦታ ላይ በስፖርት ቦታዎች፣ ኤግዚቢሽን፣ በበአላት ቀን ተሳትፌ እርዳታ ሰጥቻለሁ። በየትምህርት ቤቱ ክበባትን አዋቅረን፤ በተደራጀ መልክ ስራዎችን እየሰራን ነው ያለነው። ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ከሚያሳልፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቢሰጡ መልካም ነው"። ቢኒያም ንጋቱ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአዲስ አበባ በጎ ፈቃደኞች ወጣት ካውንስል ምክትል ፕሬዚደንት ሆኖ ያገለግላል። ለ11 ዓመታት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥቷል። ወደ በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የገባበትን አጋጣሚ እንዲህ ሲል ያስረዳል። "ስራዬ ሙዚቀኛ ነው። ቀይ መስቀል ባንድ አለው። ሙዚቀኛ ሆኜ ነበር የተቀጠርኩት። ምን እየተሰራ እንዳለ ስረዳ ወደ በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ገባሁ፤ በርካታ ስራዎችን እየሰራሁ እገኛለሁ። 24 ሰዓት አምቡላንስ ላይ በርካታ ሰዎችን እርዳታ የመስጠትና የማገዝ ስራ እየሰራን እንገኛለን። ባለን ጊዜ ሰውን ብናግዝና ብንረዳ እንደዚህ አይነት አገልግሎቶች ላይ እንዲሳተፉ ለወጣቱ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።" የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለህብረተሰቡ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ሰፊ እንደሆኑ የሚገልጹት፤ አቶ ሽመልስ ማረኝ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የበጎ ፍቃደኞች አባላትና ቅርንጫፎች መምሪያ ከፍተኛ ባለሞያ ናቸው። በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች የተጎዱትን በመንከባከብና በመደገፍም ትልቁን ሚና እንደሚጫወቱ ይጠቅሳሉ። በየትኛውም የድንገተኛ አደጋ ወቅት ከፍተኛውን ስራ የሚሰሩት የበጎ ፈቃደኞች ናቸውም ይላሉ አቶ ሽመልስ። "ቀይ መስቀል ከተቋቋመ ጀምሮ በጎ ፈቃደኞቹ ለማህበሩ የጀርባ አጥንት ናቸው። ለሚከሰቱ ችግሮቹ ግንባር ቀደም የሚሆኑት በጎ ፈቃደኞቹ ናቸው። በሰው ሰራሽም በተፈጥሮ አደጋ በደረሰ ጊዜ የቀይ መስቀል ወጣቶች ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። የመጀመሪያ የህክምና አገልግሎት በመስጠት የተጎዱ ሰዎችን በመንከባከብና በመደገፍ ትልቅ ሚና አላቸው። በድንገተኛ የህክምና አገልግሎቶች ከፍተኛውን ስራ የሚሰሩት በጎ ፈቃደኞቻችን ናቸው። በጎ ፈቃደኞቹ ከወጣት እስከ አዋቂ ነው፤ 85 በመቶው ወጣቶች ናቸው። ከበፊቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጋር ሲነጻጸር በዚህኛው ትውልድ በጎ ፈቃድ አገልግሎት አልተሰራም ማለት ይቻላል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በመዳከሙ መሰራት ያለበት ነው የሚሆነው።"
እንደ አቶ ሽመልስ ሁሉ ወጣት ቢኒያምና ሮቤል ወጣቱ ወደ በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እንዲመጣ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።

Äthiopien Addis Ababa - Freiwillige des Roten Kreuz
ምስል R. Mekuria/B. Negatu

 
ነጃት ኢብራሂም 
ማንተጋፍቶት ስለሺ