1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕወሃት ሹሙ አቶ ዛዲግ አብርሃ የአባልነት ስንብት

ሰኞ፣ የካቲት 4 2011

የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በሕገመንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት እንዲፈታ ተጠየቀ ። ሕወሃት ህጋዊ የማንነት ጥያቄ ባነሳው የራያ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን ግድያ እና አፈና በመቃወም በቅርቡ ከድርጅቱ አባልነት መልቀቃቸውን በደብዳቤ ያሳወቁት አቶ ዛዲግ አብርሃ በተለይ ለ«DW» እንደገለጹት የራያ የማንነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ሊፈታ ይገባዋል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3D9wY
Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

የማዕከላዊ እስር ቤት እንዲዘጋ በመታገሌ ከሕወሃት ጋር ትልቅ ቅራኔ ገብቻለሁ

የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት እንዲፈታ ተጠየቀ ። ሕወሃት ህጋዊ የማንነት ጥያቄ ባነሳው የራያ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን ግድያ እና አፈና በመቃወም በቅርቡ ከድርጅቱ አባልነት መልቀቃቸውን በደብዳቤ ያሳወቁት አቶ ዛዲግ አብርሃ በተለይ ለ«DW» እንደገለጹት የራያ የማንነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ሊፈታ ይገባዋል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ በአገሪቱ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን በመግለጽቸው እና ከሌሎች የለውጡ ኃይሎች ጋር የዜጎች ግፍ እና ሰቆቃ መፈጸሚያ ነው የሚባለው የማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት እንዲዘጋ ትግል በማድረጋቸው ከሕወሃት ጋር ትልቅ ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውን የሚናገሩት አቶ ዛዲግ ከዲሞክራሲ ለውጡ በተቃራኒው ተሰልፈዋል ያሏቸውንም የድርጅቱ አመራሮች ድርጊት ኮንነዋል። በተመሳሳይ ዜና  በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሱዳን ዴስክ ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት እና ለአራት ዓመታት በኬንያ በዲፕሎማትነት ያገለገሉት የራያ አካባቢ ተወላጅና የሕወሃት አባል አቶ አንዳርጉ ኢያሱ በርሄ ሕወሃት በራያ ሕዝብ ላይ ይፈጽመዋል ያሉትን ኢሰብአዊ ድርጊት በመቃወም ራሳቸውን ከሕወሃት አባልነት ማግለላቸው ታውቋል። 
የራያ አካባቢ ተወላጅና የሕወሃት አባል የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ ከ 2001 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱን ተቀላቅለው በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ቀደል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ድኤታ እንዲሁም በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዲሞክራታይዜሽን አስተባባሪ የነበሩ ሲሆን የፍትህና የህግ ስርዓት ዋና ዳይሬክተር በመሆንም በፌደራል መንግሥት ውስጥ በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ አገልግለዋል ። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አመራር ምክትል ዳይሬክተርም ነበሩ ። አቶ ዛዲግ ገና  በአፍላ ወጣትነት የእድሜ ዘመናቸው ሕወሃትን በአባልነት ከተቀላቀሉ ጀምሮ ከራያ ህዝብ ውስጥ በመውጣታቸው ምክንያት በጥርጣሬ መታየት እና ማግለልን ጨምሮ ነጻ የውጭ የትምህርት ዕድሎች ክልከላ ልዩ ልዩ አድልዖ እና ተጽዕኖ በከፍተኛ የድርጅቱ አመራር በኩል ይፈጸምባቸው እንደነበር ነው በተለይ ለ DW የገለጹት ። ያም ቢሆን ከሕወሃት አመራሮች ይልቅ የሌሎች የግንባር ፓርቲው አባላት ድጋፍ እና እገዛ ስላልተለያቸው በልዩ ልዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሹመቶች እየታጩ አገራቸውን ማገልገላቸውንም ይናገራሉ። በፖሊስ እና ደህንነት መዋቅሩ ውስጥ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም ያወቁት በእስር ላይ የነበረ የቅርብ ጓደኛቸው ሲፈታ የአካል ጉዳት ደርሶበት በማየታቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዛዲግ ከዛን  ጊዜ ጀምሮ በተለይም በርካታ ዜጎች ለስቃይ ሰቆቃ እና አካል ጉዳት ተዳርገውበታል የሚባለው የማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት እንዲዘጋ በተደረገው ጥረት  ለውጡን ከሚደግፉ ወገኖች ጋር የበኩላቸውን ሚና ማበርከታቸውን ይናገራሉ። በነበረው የለውጥ ጅማሮም በወቅቱ የፖለቲካ እስረኞች በአገሪቱ መኖራቸውን እውቅና በመስጠት እንዲፈቱ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  ጽሕፈት ቤት ድሕረ ገጽ ላይ ይኸው ጉዳይ ይፋ መደረጉም ከሕወሃት የበላይ አመራሮች ጋር የነበራቸውን ቅራኔ ይበልጥ እንዳካረረውና ዘለፋ እና ዛቻውም ተባብሶ መቀጠሉን አቶ ዛዲግ ያስታውሳሉ።
 የሕወሃት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት አቶ ዛዲግ በአገሪቱ " የፖለቲካ እስረኞች አሉ " የሚል ዕውቅና መስጠታቸው ከድርጅቱ ጋር ይበልጥ ሆድ እና ጀርባ ቢያደርጋቸውም በሂደት የሕሊና እስረኞች የመፈታታቸው ጉዳይ ግን የማይቀር ሆኗል ይላሉ።ለውጡ የትግራይ ሕዝብንም ሆነ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ የሚጠቅም ቢሆንም አንዳንድ የሕወሃት አባላት ለውጡን ለማሳካት የተካሄደውን የእስረኞችን ፍቺ በበጎ ጎኑ ሲመለከቱት መላው አገሪቱን ወደ ትልቅ እስር ቤት እየቀየሯት የነበሩ ጥቅማቸው የተነካባቸው አብዛኛዎቹ ከፍተኛ አመራሮች ግን ቁጭት እና ብስጭት ውስጥ ገብተው እንደነበርም ነው የገለጹልን ። ፀረ ሕዝብ እና ፀረ ለውጥ ሲሊ የገለጹት ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በመላው ኢትዮጵያ ከመጣው ለውጥ ጋር አብሮ ለመሄድ አለመፍቀዱ ይልቁንም ለውጡን ለማደናቀፍ በተቃራኒ አቅጣጫ በጥፋት ጎዳና መጓዙ ድርጅቱን ለመሰናበት ቀዳሚው ምክንያት እንደሆናቸውም ተናግረዋልዋል።
 የራያን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በተመለከተም ያለ ፈቃዱ ወደ ትግራይ በመካለሉ ምክንያት በሚያቀርበው ሕጋዊ እና ሰላማዊ ተቃውሞ እስካሁን የሚሰጠው ምላሽ ጥይት ነው ያሉት አቶ ዛዲግ ከሕወሃት ለመልቀቅ ሌላው ምክንያታቸው ይኸው በማሕበረሰቡ ላይ የሚፈጸመው መቆሚያ ያጣው ግድያ እስር አፈናን እንግልት እና ሰቆቃ መሆኑንም ገልጸውልናል። የትግራይ ክልል መስተዳድር የራያ ችግር ለዓመታት ምላሽ ያጣ የመልካም አስተዳደር እጦት እንጂ የማንነት ጥያቄ አይደለም ሲል በተደጋጋሚ የሚሰጠውን ምላሽም ሃሰት ነው በማለት አጣጥለውታል ። 
በተመሳሳይ ዜና  በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሱዳን ዴስክ ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት እና ለአራት ዓመታት በኬንያ በዲፕሎማትነት ያገለገሉት የራያ አካባቢ ተወላጅና የሕወሃት አባል አቶ አንዳርጉ ኢያሱ በርሄ ሕወሃት በራያ ሕዝብ ላይ ይፈጽመዋል ያሉትን ኢሰብአዊ ድርጊት በመቃወም ራሳቸውን ከሕወሃት አባልነት ማግለላቸው ታውቋል። አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት እሳቸውን ጨምሮ ከ 7 የሚበልጡ የራያ አካባቢ ተወላጅ የሕወሃት አባላት በድርጅቱ ውስጥ በሚፈጸምባቸው መድሎ እና መገለል በራያ ሕዝብ ላይ ይፈጸማል ባሉት ግፍ እና አፈና እንዲሁም ሕወሃት አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ይጥራል በሚል ተቃውሞ ከድርጅቱ አባልነት በፈቃደኝነት የለቀቁ መሆናቸውን ከተለያዩ መረጃዎች ለማረጋገጥ ችያለሁ ነው ያሉት። ኢትዮጵያዊነትን በጭቆና ቀንበር ውስጥ ከሚገኘው የትግራይ ሕዝብ ልብ ላይ መፋቅ አይቻልም ያሉት አቶ ዛዲግ ይሁን እንጂ ለውጥ አደናቃፊው የሕወሃት ከፍተኛው አመራር በውስጡ መሽጎ የእኩይ ዓላማው ሰለባ አድርጎታል ሲሉም ወቅሰዋል።  ከ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከእንግሊዝ መንግሥት ባገኙት ነፃ የትምህርት ዕድል በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ ዛዲግ በቀጣይም ሊያታግላቸው ከሚችል ድርጅት ጋር በመቀላቀል ለራያም ሆነ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ የሚጠቅም ተግባር በመከወን አገራዊ ለውጡን ለማገዝ እንደሚተጉም ነው የተናገሩት።

እንዳልካቸዉ ፈቃደ 


አዜብ ታደሰ 
ነጋሽ መሐመድ