1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የቀድሞዎቹ እንጨት ተሸካሚዎች 

ረቡዕ፣ ነሐሴ 17 2009

ትክክለኛ ቁጥራቸው አይታወቅ እንጂ በአዲስ አበባ እንጨት እና ቅጠል ለቅመው በመሸጥ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ብዙ ሴቶች አሉ። ሥራቸው እስከ አስገድዶ መድፈር የሚያደርስ ለድብደባም የሚያጋልጥ እንደሆነ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/2iijJ
Women collecting firewood in the forest – Nepal
ምስል Rob Goodier / Engineering for Change / CC BY-SA 2.0

የቀድሞዎቹ እንጨት ተሸካሚዎች

ወ/ሮ አማረች አሜ ለብዙ ዓመታት ኑሯቸውን የገፉት ከእንጦጦ ጫካ እንጨት ለቅመው በሽሮ ሜዳ ገበያ እየቸረቸሩ ነበር። ሥራው ጀርባ ይሰብራል፤ የጥበቃ ዱላ እና ጥቃትም አያጣውም። አምስት አባላት ያሉትን ቤተሰብ ለማኖር ወ/ሮዋ በሳምንት ሶስት ቀናት ከሽሮ ሜዳ ተነስተው የእንጦጦ ጫካዎችን ሲያካልሉ ኖረዋል።"እንጦጦ ተራራ ወጥቼ ነው የምለቅመው። ከዛ ከላይ ንፋስ ያራገፈውን ቅጠል ሰብስቤ በመሸጥ ነበር የምተዳደር የነበረው። በሳምንት ሶስት ጊዜ እሔዳለሁ። ገበያ ላይ ግን ዋጋው በጣም ርካሽ ነበር።" ወጣቷ ፍቅርተ ጀቤሳም ለሁለት አመታት የእናቷን ዱካዎች እየተከተለች እንጨት ለቅማ ትሸጥ ነበር። ፈታኙን ሥራ ተጋፍጠው ቤተሰባቸውን የመመገብ ጫናው የወደቀው ግን ዛሬ ህመም በተጫናቸው የእናቷ ጫንቃ ላይ ነበር።እንጨት ለቀማው ሁሌ አይሳካም።አንዳንዴ ደግሞ የጥበቃዎች ዱላም አለ። ለዚህ ደግሞ ወ/ሮ አማረች ምሥክር ናቸው። ጀርባ የሚያጎብጠው እንጨት ለቀማ እስከ ሁለት ሰዓት ያስጉዛል። ጫካ ለጫካ የሚያኳትነው ሥራ አስከ አስገድዶ መደፈር የሚያደርስ አደጋ አለው። ፍቅርተ ዘርዘር አድርጋ ልትናገረው አትፈልግ እንጂ እሷን ጨምሮ በርካቶች ይኸው መጥፎ አጋጣሞ ደርሶባቸዋል። 
96 በመቶ ገደማ ኢትዮጵያውያን የዕለት ከዕለት ምግባቸውን ለማብሰል የባህላዊ ኃይል ምንጭ ጥገኛ ናቸው። ማገዶ፤ከሰል፤ ከሰብል የተረፉ ምርቶች፤እና የእንስሳት አይነ ምድር ለኢትዮጵያውያን የምግብ ማብሰያ ሆነው ያገለግላሉ። አዲስ አበባ ታዲያ ባህላዊውን የኃይል ምንጭ እንድታገኝ እንደ ወ/ሮ አማረች እና ፍቅርተ ያሉ እንጨት ለቃሚዎች ያስፈልጓታል። አሏትም።  በእንጨት ለቀማ የተሰማሩ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር፤በሥራቸው የሚያገኙት አማካይ ገቢም ይሁን ፈተናዎቹን የሚዳስስ ጥልቀት ያለው ሰነድ ማግኘት አልቻልንም። የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ-ክርስቲያን የልማት ድርጅት በሰራው የዳሰሳ ጥናት ግን ቢያንስ እስከ 800 ሰዎች በዚህ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው እንደሚገኙ ይገምታል። አቶ አልዩ ሸረዲ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል የልማት ድርጅት  መካከለኛ ቀጠና ፕሮግራም ኦፊሰር ናቸው። 
ወ/ሮ አማረች አሜ እና ፍቅርተ ጀቤሳን ከቀድሞ የእንጨት ለቀማ ሥራቸው ያላቀቃቸው የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ-ክርስቲያን የልማት ድርጅት የሰጣቸው ሥልጠና እና ያቀረበላቸው ተዘዋዋሪ የብድር አቅርቦት ነው። ለስድስት አመታት በሶስት ዙሮች ለማገዶ ለቃሚዎች ስልጠና እና የመነሻ ገንዘብ በመስጠት አማራጭ ሥራ እንዲያገኙ ሲያደርግ ቆይቷል። ወደ 42 ከሚደርሱት የድርጅቱ የሥራ ዘርፎች መካከል የሕጻናት፤አረጋውያን እገዛ እና የሴቶች አቅም ግንባታ ይገኙበታል። ድርጅቱ በሚሰራቸው የልማት ሥራዎች እንጨት ለቃሚዎችን፤ 12ኛክፍል አጠናቀው ስራ ያጡ እንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ የሚፈልጉ ሰዎች ያግዛል። 

Ghana Frauen Internationaler Frauentag
ምስል Geoffrey Buta

ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ማዕቀፉ ያድምጡ።

እሸቴ በቀለ 

ነጋሽ መሐመድ