1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተሠረዘው የቴዲ አፍሮ አልበም ምረቃና መስቀል ያሰረው ቢራ

ዓርብ፣ ጳጉሜን 3 2009

ከረዥም ውጣ ውረድ በኋላ በሒልተን ሆቴል ሊመረቅ ነበር የተባለለት የቴዲ አፍሮ «ኢትዮጵያ» አልበም ምረቃ መሰረዝ መነጋገሪያ ሆኗል። አንገቱ ላይ መስቀል ታስሮለት በቪዲዮ የማንቀሳቀስ ስልት የሚውረገረገው የራያ ቢራ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ በበኩሉ ከቁጣ አልፎ ብዙዎችን በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች እጅግ አነታርኳል።

https://p.dw.com/p/2jXtv
Artist Thewodros Kasahun
ምስል CD Album Foto Via Mantegaftot Sileshi

በተደጋጋሚ ጊዜያት አንዴ በመንግሥት ሌላ ጊዜ ደግሞ አርቲስቱን በሚቃወሙ ወገኖች አስተባባሪነት ያቀዳቸው የሙዚቃ ድግሶች ተሰርዘውበታል፤ አሁን ደግሞ የሙዚቃ አልበሙ ምረቃ። አርቲስት ቴዲ አፍሮ፤ ባሳለፍነው እሁድ በሂልተን ሆቴል ሊያኪያሂድ የነበረው «ኢትዮጵያ» የተሰኘው የአልበም ምርቃት መሰረዙ በርካታ ደጋፊዎቹን አስቆጥቷል። ራያ ቢራ በቴሌቪዥን ያቀረበው ማስታወቂያ አንገታቸው ላይ መስቀል የተንጠለጠለባቸው ሦስት የቢራ ጠርሙሶች በምስል ቅንብር ሲወዛወዙ ይታያል። የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች አብይ መነጋገሪያ ሆኗል። በበርማ የሰላማዊ ሰዎች ጭፍጨፋ እና ግፍ ሰሚ አላገኘም የሚሉ አስተያየቶችም ተበራክተዋል። ጣና ሐይቅን የወረረው እምቦጭ አረምን ለማጥፋት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ያሳዩት እልህና ርብርብ ብዙዎችን አስደምሟል። 

ነሐሴ 28 ቀን፤ 2009 ዓ.ም. አንድ ሺህ ግድም አድናቂዎች ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በጉጉት የሚጥብቁት አንዳች ነገር ነበር። አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ለአድናቂዎቹ ያቀረበውና ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈለት፤ በዓለም የአልበም ሽያጭ በአንድ ዘርፍም ለሳምንታት አንደኛ ሆኖ የዘለቀለት «ኢትዮጵያ» የተሰኘው የሙዚቃ ዓልበሙ የሚመረቅበት ቀን ነበር። አርቲስቱ እሁድ ከሰአት 11 ሰአት ከሩብ አካባቢ በፌስቡክ ይፋዊ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ «በደመቀ ሁኔታ» ሊካሂድ የነበረው የ«ኢትዮጵያ» አልበም ምርቃት መሰረዙን የገለጠው በ«ከፍተኛ ሀዘን» ነበር። 

ቴዲ የሙዚቃ አልበም ምርቃት ዝግጅቱ ሳይጀመር የተቋረጠው በጸጥታ ኃይላት ትእዛዝ መሆኑን ጽፏል። «ይህን ዝግጅት ለማካሄድ ፍቃድ መጠየቅ ማለት አንድ ዜጋ የሠርግ ወይም የልደት በዓሉን ለማክበር ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ከመንግሥት ፍቃድ የመጠየቅን ያህል ሥራ ላይ ውሎ የማያውቅ አሠራር» ነው ሲልም ገልጧል። ቀጠል አድርጎም «ከአገሪቱ የሕግ አካሄድ ጋር የሚጣረስ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለጊዜውም ቢሆን ሁኔታውን ለማስቀጠል ባደረግነው ሙከራ ምንም አይነት የሙዚቃ መሣሪያና ለዝግጅቱ አስፈላጊው የሆኑ ግብዕቶች በሙሉ ወደ ሆቴሉ እንዳይገቡና ከመኪና እንዳይወርዱ መለዮ በለበሱ የመንግስት ታጣቂዎች በመከልከላችን ያለውን ሁኔታ ለመቀበል ተገደናል» ሲልም ማን እንደከለከላቸው ይፋ አድርጓል።

Tewodros Kassahun Musik Äthiopien
ምስል DW/L.Abebe

ጥሪ የተደረገላቸው አድናቂዎቹንም ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ ጠይቋል። «ክቡራን እንግዶቻችን እና ለመላው ውድ አድናቂዎቻችን ይህን ይቅርታ ያዘለ መልዕክታችንን ስናስተላልፍ መጪው አዲስ አመት የሰላምና የፍቅር ከምንም በላይ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ልጆች በዕኩል ዓይን የሚታዩበት የፍትሕ ዘመን እንዲሆን በመመኝት ነው» ያለው ቴዲ አፍሮ ጽሑፉን የቋጨው «ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፤ ፍቅር ያሸንፋል» በሚል ማሰሪያ ነው።

ጋዜጠኛ ነቢዩ ሲራክ በፌስቡክ ገጹ «የተወዳጁ ቴዲ አፍሮ ጥፋቱ ምንድን ነው ?» ሲል ጠይቋል።  «አስራ ሰባት መርፌ ብሎ በመዝፈኑ፣ አስራ ሰባት አመት ሊቀጡት ወሰኑ። ግና እሱ ሆነ እንጅ አስራ ሰባት ፅኑ። ቴዲ አፍሮ» ሲል በትዊተር ገጹ የጻፈው ደግሞ ዘመናት ነው። ዓሚር ቢን ያስር «ቴዲ አፍሮ ዝግጅቱን እንዳያቀርብ በሚያደርጉ ኃይሎች እና በእነ ጎሳይ ላይ Boycott በሚጠሩ ኃይሎች መካከል ያለውን ልዩነት የሚያስረዳኝ ይኖር ይሆን?» ብሏል።

«ቴዲ አፍሮ ብቻ አይደለም ሙዚቃውን እንዳያቀርብ የተከለከለው።  ሌሎችም በጣም ብዙ አሉ" የሚባል መጃጃል ምንድነው? በሱ ብቻ የመጣ አይደለም ስለዚህ ችግር የለውም ነው?» ሲል አውራሪስ በትዊተር ገጹ ጠይቋል።  አሉላ ሰለሞን ደግሞ፦ «ኢትዮጵያን ስለምወድ በደል ደረሰብኝ" የምትል አዲስ ከረሜላ ገበያ ላይ ውላለች» ሲል በፌስ ቡክ ጽፏል። 

አቤል ሺፈራው፦ «ቴዲ አፍሮ በሁለት ዘረኞች መከራውን የሚያየው ኢትዮጵያን ስላለ ነው። ቴዲ አፍሮን መጠበቅ የኢትዮጵያዊነት ግዴታችን ነው» ብሏል። ደረጀ ምንዳዬ፦ «የፍቅር ቀን መቼ ነበር? የፍቅር ቀን ፍቅር ያሸንፋል!ኢትዮጵያዊነት ያበራል!ቴዲ አፍሮ ከማማው፣ ከሰገነቱ ከከፍታው ተሰይሞ ኢትዮጵያዊነትን ይዘምራል። ይብላኝ ለበቀለኞች ይብላኝላቸው ለክፉዎች!» የሚል ጽሑፉን አስነብቧል። የሁለቱም ጽሑፍ በፌስቡክ ነው የቀረበው። ዮና ብር በትዊተር ገጹ፦ «ተራ ካድሬ ከሕገ መንግሥት በላይ በሚያዝባት አገር ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ብቻውን ታግሎ አሸነፏል» ብሏል። ጋዜጠኛ ቆንጂት ተሾመ፦ «ከፍታው የአንተ ነው ቴዲ አፍሮ! ቢሰረዝ ባይሰረዝ...በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ንግስናህ ጽኑ ነው! ምንም የሚሰበር መንፈስ የለም!» ስትል ቴዲ አፍሮ እና ኢትዮጵያ በሚሉ ቃላት አስተያየቷን ቋጭታለች።
ሌላው የሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር አቢይ መነጋገሪያ ሆኖ የቆየው የራያ ቢራ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ነበር። «ርሑስ በዓል አሸንዳ» በሚል በትግሪኛ ቋንቋ የቀረበው የቴሌቪዥን ማስታወቂያ በርካቶችን ያበሳጨው መስቀል የተንጠለጠለባቸው ሦስት የቢራ ጠርሙሶችን በማስታወቂያነት በመጠቀሙ ነበር። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ኢንትዮጵያን ዲጄ የተሰኘው በርካታ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ፦ «ምነው ራያ ቢራ? መስቀል በቢራ ማንጠልጠል ምን አይነት ንቀት ነው?»  በሚል አጠር ያለ ዐረፍተ ነገር ከተንቀሳቃሽ ምስል ጋር አያይዟል። 

ተንቀሳቃሽ ምስሉ እንደ ሰው አንገታቸውን የሚያረገርጉ ሦስት ቢራዎች ይታዩበታል። ቢራዎቹ የፎቶግራፍ ምስልን በማንቀሳቀስ ስልት ማለትም (animation) የተሠሩ ናቸው። ወገባቸው ላይ የተረዘረዘ የቅጠል ዝንጣፊ በአጭሩ አገልድመዋል። ሲወዛወዙ ብትን ዘርጋ የሚል ዝንጣፊ። የቢራዎቹ አናት ላይ ከቆርኪው በቀለማት የተገመደ ቀጭን ሻሽ መሳይ ነገር አስረዋል። አወዛጋቢው የሆነዉ ነገር -እንደ ሰው አንገት በሚቅለሰለሰው የቢራው አንገት ላይ የታሰረው መስቀል ነው። 

«ቢራ ላይ መስቀል አጥልቆ ፕሮሞሽን የመስራቱ ሐሳብ ስንት ቢራ ቀምቅመው ነው የመጣላቻው?» ሲል የጻፈው አዲስ አብነት ነው። አየለ አዲስ እዛው ፌስቡክ ላይ፦ «ራያ ቢራ ላይ መስቀል መኖሩ ምንም አይገርምም፤ ቢራ ሃይማኖትን መሰረት አድርጎ አልተጠመቀም፤ ቢጠመቅም እየጠጣ ያለው ክርስቲያኑ ነው» ብሏል።

ሳባዊ ደሳለኝ በበኩሉ፦ «ከ90 ዓመት በላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚል ስያሜ ያለው ቢራ ያለምንም ጥያቄ ሲጠጣ ኖሮ ምንም ያላለው ሰው( እኔን ጨምሮ) አንድ የማስታወቅያ ስህተት ሲያይ ዓይኑ ቀልቶ ራያ ቢራ ላይ ይዘምታል!» ሲል ተችቷል። «ራያ ቢራ መስቀል በቢራ መጠቀሙ ተሳስተዋል ብየ አምናለው!» ያለው ሳባዊ «የራያ ቢራ ስህተት በአንድ ደቂቃ በማይሞላ ማስታወቂያ የሚስተካከል ነው!» ሲልም አክሏል። 

ቴዲ ማይጨው፦ «ራያ ቢራ ውስጤ ነው» ሲል ፌስቡክ ላይ ጽፏል በአጭሩ። «የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ሲገርመን አሁን ደግሞ ራያ ቢራ የፈጣሪ ያለኽ» ያለችው ሚጣ ናት። የራያ ቢራ ቁጣ ለቀሰቀሰው ማስታወቂያ ማስተባበያ አልተሰጠም የሚሉ ሰዎች አሁንም እንደተቆጡ ነው። በአንጻሩ የራያ ቢራን «አትጠጡ» የሚል ዘመቻም መጀመሩ ተሰምቷል።

Bangladesch Massenflucht der Rohingyas
ምስል picture-alliance/dpa/B. Armangue

የጣና ሐይቅን ያሰጋዋል የተባለው የእምቦጭ አረም ወረርሽ ድንገተኛ ዜና ብዙዎችን ማስደንገጡ ብዙም ውሎ ሳያድር ወጣቶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተጠራርተው በዘመቻ መልክ አረሙን ሲነቃቅሉ ታይተዋል። ወኔ በተቀላቀለበት መንፈስ ጭቃና አረንቋውን ሳይጠየፉ የከተማ ወጣቶች ከገጠር ነዋሪዎች ጋር በመተባበር በዜማ ታጅበው አረሙን ከሐይቁ እየነቀሉ ሲከምሩ የሚያሳዩ የፎቶግራፍ እና የቪዲዮ ምስሎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ተሰራጭተው ታይተዋል።

ሌላው በሳምንቱ መነጋገሪያ ከሆኑ ርእሶች መካከል በበርማ የተባባሰው ጭፍጨፋ ይገኝበታል። በበርማ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰዉ ግፍ እና ጭፍጨፋ ተገቢውን ሽፋን አላገኘም የሚሉ ተደጋጋሚ አስተያየቶች በተለይ በዋትስአፕ ገጻችን ደርሶናል።  

ጪቅሳው ወርቁ፦ «ፍትህ በርማ ውስጥ ለሚገኙ ሙስሊሞች» ሲል ጽፏል።  ሙስሊም ለሙስሊም በፌስ ቡክ ገጹ፦ «በርማ የሩሃኒንግ ሙስሊሞች ስቃይ በሰው አይደለም በእንስሳትም ላይ ሊፈፀም የማይገባ እና ይህንን ለመቃወም ደግሞ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው» ብሏል። «ሙስሊም አይደለሁም። ሆኖም ግን በርማ በሚባል አገር የሰው ልጅ የመጨረሻውን የጭካኔ ጣራ በነካ አገዳደል ሲገደል እያየሁ ዝም አልልም» ያለው ደግሞ የቅዱሳን ኅብረት ነው።

ብዙኃን የቡድሒዝም እምነት ተከታዮች በሚኖሩባት ሚያንማር ወይንም በርማ፤ በመንግስት ጦር የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ሕጻናትን ጨምሮ የሚታይባቸው ምስሎች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተሰራጭተዋል። በሚያንማሩ ኹከት ከሮሂንግያ ሙስሊሞች በተጨማሪ የሒንዱ እና የቡድሂዝም እምነት ተከታዮችም መገደላቸው ተዘግቧል። የበርማ መንግሥት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 430 ግድም ይደርሳል ሲል ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር። ቁጥሩ በሌላ ወገን አልተጣራም። ግድያው አሁንም አልተቋረጠም። የበርማ መንግሥት ጦርን ግፍና በደል በመፍራት ደግሞ ወደ ባንግላዴሽ የተሰደዱት የሮሒንግያ ሙስሊሞች ቁጥር ከ164ሺ መብለጡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። ይኽም ዜና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሠራጭቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ