1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተተኪ ወጣቶች ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ 

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ መስከረም 25 2011

ከላይ የሰማችሁት ባለፈዉ ረቡዕ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በ11ኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር «ኢህአዴግ» ድርጅታዊ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደዉን ነበር።

https://p.dw.com/p/360NI
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Demonstration mit Anhängern
ምስል Reuters

ወጣቶችና ፖለቲካ 

ወጣት ላሊሳ ባጫ የባቱ « ዝዋይ» ነዋሪ ሲሆን ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም ሥራ አላገኘም እስካሁንም ሥራ አጥ እንደሆነ ይናገራል። ላሊሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ደስ እንዳሰኘዉ ገልፆአል ግን ንግግሩ በተግባር ሲተረጎም ማየትን እንደሚፈልግ ነዉ የተናገረዉ።

ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ስልጣን እንደ ርዕስት ይታያል የሚለዉ የቡታጅራ ነዋሪ  ሬዱዋን ከድር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ስልጣን ማለት ህዝቡን ካገለገሉ በኋላ ለወጣቶች አሰረክቦ መሄድ እንዳለበት ከፍተኛ ትምህርት የሰጡበትም አጋጣም መሆኑን አክሎአል። ሬዱዋን ከድር  እንደሚለዉ አሁን ያለዉ ሽግግር ያለወጣቱ ተሳትፎ አይሳካም ባይ ነዉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ የሚታየዉ የፖለቲካ መቃወስ ሰብዓዊና ዲሞክራስያዊ መብቶች መጣሳቸዉ የአንበሳዉን ድርሻ ቢወስዱም የወጣቶች ሥራ አጥነት እንደ ሌላ ምክንያት ሲጠቀስ እንደነበርም ይታወሳል። የወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱና ይህን ተከትሎ አብዛኛዉ ወጣት ሥራ አጥ መሆኑን ይስማማበታል። ወጣት ለሊሳ ባጫ በበኩሉ  አገሪቱ የነበረችበትን ሁኔታ አስታዉሶ ወጣቶች ለአዲሱ አመራር ግዜ መስጠት አለባቸዉም ብሎአል።

Anhänger von Ministerpräsident Abiy Ahmed demonstrieren in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Gebregziabher

አሁን አገሪቱ ያለችበት ሽግግር ወደ ሚፈለገዉ ቦታ ለማድረስ «የበሬዉን ብልሃትና የወይፋኑን ጉልበት» ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በበጉባኤዉ መክፈቻ ንግግራቸዉ ላይ ጠቅሰዋል።

መንግስት የህግ የበላይነት የማስከበር ግዴታዉን ሊወጣ እንደሚገባም ያሳሰበዉ ወጣት ለሊሳ ግን ይህ ማለት ወደ ቀድሞ ሁኔታ ተመልሶ ማሰርና መግደል መሆን የለበትም ሲል ተናግሮአል። ህዝብ የማይፈልጋቸዉን  አመራሮች የስልጣን ሹመት መስጠት ሳይሆን ወደ ህግ ፊት አቅርቦ ቀርቦ ዋጋቸዉን ማግኘት አለባቸዉም ብለዋል።

የቀደመዉ ትዉልድ ያካበተዉን ልምድና ጥበብ በመጠቀም መካር መሆን እንዳለበት የተናገሩት ዶከትር ዐብይ «እዉቀትና ጉልበት ደግሞ አዲሱ ትዉልድ ዘንድ ይገኛልም» ብለዋል። የአዲሱ ትዉልድ ተተኪ መርሆዎችም ያለፈዉን ነገር ሁሉ ማማረርና ባለፈዉ ትዉልድ ላይ ማሳበብ አይገባቸዉም ሲሉም አሳስበዋል። አገሪቱን ለፖለቲካ ቀዉስ የዳረጋት «መተካካት መበላላት» በመሆኑ ነዉ ብለዋል።

«አንድ መሪ የሚመዘነዉ ባፈራዉ ተተኪ ነዉ» ባሉት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የሚስማማዉ  ወጣት ለሊሳ ዶክተር ዐብይ ተተኪ የማፍራትም ብቃት እንዳላቸዉ፤ በዝያም እንደሚያምን ገልፀዋል።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ