1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የተጀመረው ዕርቅ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግብይት ምን ይፈይዳል?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 4 2010

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን እስኪመጡ በድንበር ይገባኛል ውዝግብ የተቃወሰው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወዳጅነት የመቃናት ምልክት አላሳየም። ጦርነቱና የተከተለው ወታደራዊ ፍጥጫ ከተሞች የነበራቸውን ማኅበረ-ኤኮሚያዊ እንቅስቃሴ ቀምቶ ምድረ-በዳ አድርጓቸዋል። የተጀመረው ዕርቅ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግብይት ምን ይፈይዳል?

https://p.dw.com/p/31IGs
Eritrea Soldaten auf dem Weg zur Front
ምስል picture-alliance/dpa/S. Forrest

የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ስምምነት ኤኮኖሚው

በስተመጨረሻ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰላም አወረዱ።ሁለቱ አገራት ለ20 አመታት ገደማ ተቋርጦ የነበረው የስልክ ግንኙነታቸው እንደገና ተጀምሮ የተነጣጠሉ ቤተሰቦች ይነጋገሩ ጀምረዋል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈረሙበት ሰነድ እንደታቀደለት ገቢራዊ ከሆነ አሁን ሰላም ወርዷል። አገራቱም የሕዝቦቻቸውን ጥቅም የሚያስጠብቅ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና የጸጥታ ግንኙነት ይኖራቸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ አስመራ በረራ ይጀምራል።

ከወደ አፍሪቃ ቀንድ የነፈሰው የለውጥ ነፋስ በርካቶች በጉጉት የጠበቁት ቢሆንም ፍጥነቱ ግን አስገራሚ መሆኑ አልቀረም። ለሉዋም ዲራር ነገሩ ሁሉ እንዲያ ሆኖባታል።ሉዋም ዲራር የአስመራ እና የኮርኔል ዩኒቨርሲቲዎች የሕግ ምሩቅ ነች።  በተለይ ትኩረቷን በንግድ፣ የልማት እና የአፍሪቃ ጉዳዮች ላይ አድርጋ በአማካሪነት የምትሰራው ዲራር "እንዴት ልገልጸው እንደምችል አላውቅም። ፈፅሞ የሚታመን አይደለም። ሰላም እጅግ ሩቅ ያለ ይመስል ነበር። ረዥም ጊዜ የሚወስድ ይመስል ነበር። ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ለውጥ የነበረ ቢሆንም በዚህ ፍጥነት ይሆናል ብዬ ግን አላሰብኩም ነበር" ስትል ስሜቷን ታስረዳለች።

በእርግጥ ሰላም እጅግ ሩቅ ሆኖ ቆይቷል። በአሰቃቂው ጦርነት ከሁለቱም ወገን እስከ 80,000 የሚደርስ ሰው አልቋል። ጦርነቱ በተካሔደባቸው አካባቢዎች የነበረው የተፈጥሮ ሐብት ወድሟል። ገበያ ተበትኗል፤ እንቅስቃሴም ቆሟል። ለዚህ በትግራይ ክልል ኢሮብ ወረዳ ተወልዶ ያደገው ዚያደ አብርሐ ካህሳይ ምስክር ነው። ዚያደ በቦን ዩኒቨርሲቲ የፒ.ኤች.ዲ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል። ከጦርነቱ መቀስቀስ በፊት በልጅነቱ ለኢሮብ ሰዎች የኤርትራዋ ሰንዓፈ የቅርብ ገበያ እንደነበረች ዚያደ ያስታውሳል። እርሱም የ13 አመት አዳጊ ሳለ ሰንዓፈ ገበያን ያውቃትል። ዛሬ ግን ያ ሁሉ የለም።

"የኤርትራ ጦር ሲገባ የነበረው የተፈጥሮ ሐብት በማይመለስ መልኩ ነው የጠፋው" የሚለው ዚያደ የንብ ቀፎዎች እና የእንስሳት ሐብት ጭምር መውደማቸውን ያስታውሳል። "ግብይት ጭራሽ የለም። አሁን ምንም ወደማይመለስ ደረጃ ላይ ነው የወረደው። ምክንያቱም ውጊያ ከተካሔደ በኋላ ወታደር ሰፍሮበታል። ለ20 አመታት ያህል ወታደር እየኖረበት ነው ያለው" ሲል ያክላል።

President Isaias Afwerki &  Prime Minister Abiy Ahmed in Asmera
ምስል Yemane G. Meskel

የጦርነቱ ዳፋ ግን በኢሮብ ወረዳ ብቻ አልተወሰነም። በቦን ዩኒቨርሲቲ የድኅረ-ዶክትሬት የምርምር ባለሙያው ሳሙኤል ገብረ መድኅን ኢታይ ዛላምበሳ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እና ጦርነቱን የተከተለው ውጥረት ተፅዕኖ ተሸካሚ መሆኗን አስተውሏል። ሳሙኤል "ዛላምበሳ ከጦርነቱ በፊት የንግድ እንቅስቃሴው በጣም የደራ፤ እጅግ የደመቀ የድንበር፤ መኪና ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ፤ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚሔዱበት፤ ከመቀሌ ወደ አስመራ ያለው መስመር የሆቴል ንግዱ የተጧጧፈበት፤ የሰው እንቅስቃሴ በጣም የበዛበት፤ ሰራተኞች ከትግራይ ወደ ኤርትራ የሚሔዱበት እንዲሁም ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት" እንደነበር ይናገራል። ከጦርነቱ በኋላ ግን ዛላምበሳ ለሳሙኤል "ሞት ያንዣበበት ከተማ" መስላ ታይታዋለች። ሳሙኤል ከተማዋን በጎበኘበት ወቅት የመኖሪያ ቤቶቿ መፍረሳቸውን ታዝቧል። "ከድንበሩ ወደ መሐል ትግራይ ወደ 50 ኪ.ሜ. እና ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ በሙሉ ከኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ነፃ ነው። የመዋዕለ ንዋይ እንቅስቃሴም የለውም። የአካባቢው ማኅበረሰብም ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን አይሰራም። የአካባቢው ሚሊሺያም ካለው የመከላከያ ሰራዊት ጋር ተጣምሮ ነው ድንበር የሚጠብቀው" የሚለው ሳሙኤል አካባቢው እንቅስቃሴው ተገድቦ መቆየቱን አስረድቷል።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት በባድመ አካባቢ በነበረ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ተቀሰቀሰ ይባል እንጂ ዳፋው ሁለቱ አገሮች የሚዋሰኑበትን አካባቢ ሁሉ አዳርሷል። በጦርነቱ ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የንግድ፣ ቱሪዝም እና መዋዕለ-ንዋይ እንቅስቃሴዎች ቆመዋል። የሕግ የበላይነት እና የተቋማት ሚና ተዳክሟል። የግልም ሆነ የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ የሚሹትን ደኅንነት በማጣታቸው ምክንያት እርግጠኝነት ማጣት እንዲሰፍንም አድርጓል።

ጉዳዩን ውስብስብ የሚያደርገው በአገራቱ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው መቃቃር ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ እንኳ መፍትሔ ሳይገኝለት ቀርቶ ለሁለት አስርት አመታት በተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ መዝለቁ ነው። "ከጦርነቱ በፊት ሁለቱ አገሮች በርካታ የሁለትዮሽ የንግድ ሥምምነቶች ነበሯቸው። ሁለቱም አገሮች የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ ) አባላት ነበሩ። ኤርትራ የኢጋድ አባል አገር ነበረች። እርስ በርስ ለመገበያየት እና ለመረዳዳት ጥረት ያደርጉ ነበር።" የምትለው ሉዋም ከጦርነቱ በኋላ ግን መስተጓጎሉን ጠቁማለች።  ሉዋም "እርስ በርስ መገበያየት አንዱ ጥቅሙ ለዜጎች አማራጭ ምርቶች እና የዋጋ ተመን ማቅረቡ ነው። ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በርከት ያሉ የምርቶች አማራጮች ይኖሯቸዋል። ጤፍን በምሳሌነት እንውሰድ። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የሚመረት በመሆኑ በገበያው ላይ ውድድር ይኖራል። በዚህም ለሸማቹ ውዋጋውን ዝቅ ያደርገዋል። ይኸ አንዱ አዎንታዊ ተፅዕኖው ነው። ሌላው የተለያየ አይነት ጤፍ በገበያው ላይ እንዲያገኙ ይረዳል። ከጦርነቱ በኋላ ግብይት የነበረ ቢሆንም በሶስተኛ አገር በኩል መሔድ ነበረበት። የኢትዮጵያ ጤፍ ለኤርትራ ገበያ የሚደርሰው በሱዳን ወይም በየመን በኩል በመሆኑ በጤፍ ዋጋ ላይ ጭማሪ ፈጥሯል። ይኸ ደግሞ በኤርትራ ላለው ሸማች ውድ እንዲሆን ያደርገዋል። ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚላኩ ምርቶች በተመሳሳይ በሶስተኛ አገር በኩል እንዲሆን በመገደዱ በኢትዮጵያ ላለው ሸማች ውድ ሆኖኗል" ስትል በዜጎች ላይ ያለውን ጫና አክላለች።

የአፍሪቃ አገሮችን የርስ በርስ የንግድ ግንኙነት የምትከታተለው ሉዋም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግብይት በጦርነት ባይደፈርስ ኖር ሁለቱንም የተሻለ ተጠቃሚ ባደረገ ነበር የሚል ዕምነት አላት።

"የጦርነቱ ሌላ ኤኮኖሚያዊ ጫና የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ላይ ያሳደረው ነው። በጦርነቱም ወቅት ሆነ ከጦርነቱ በኋላ ከውጭ የሚመጣው የውጭ መዋዕለ ንዋይ በሁለቱም አገሮች ጫና ላይ ወድቋል። ለ25 አመታት ገደማ ወደ ኤርትራም ሆነ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ የውጭ መዋዕለ-ንዋይ የነበረ ቢሆንም ሁለቱ አገሮች ሰላም ቢኖራቸው ኖሮ ሊሆን የሚገባውን ያክል አይደለም።  አሁን በደረሱበት የሰላም ስምምነት የውጭ መዋዕለ ንዋይ ይጨምራል ብዬ አስባለሁ። በሁለቱ አገራት ዜጎች መካከል የሚኖረው የንግድ ግንኙነት ይጨምራል። በዚህም የሥራ ዕድል ይፈጠራል። የካፒታል፣ ሸቀጦች ፣አገልግሎቶች እና የሰዎች እንቅስቃሴም ያድጋል። የንግድ ሥምምነቱ ምን ዓይነት እንደሚሆን ለጊዜው የማውቀው ነገር የለም። በቅርብ ጊዜ እናውቃለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን ይፋ የሆነው እጅግ በጣም መሠረታዊ የሚባል ነው"

Karte Äthiopien Eritrea Grenze Amharisch

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት የዕርቅ ሙከራ ግን እንዲህ ቀላል አይመስልም። የድንበር ማካለል ጉዳይ እና የአልጀርስ ስምምነት ተግባራዊነት ሁነኛው ፈተና ነው። አገራቱ መቼ እንዴት እና በማን ድንበር ይካለላሉ? የሚታወቅ ነገር የለም። የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊነት ሥጋት ከሚያጭርባቸው የአሁኑን የሰላም ማውረድ ሙከራ በግማሽ ልብ ከተቀበሉት መካከል ዚያደ አንዱ ነው። ሰላም የማውረድ ጥረቱ እንደ ኢትዮጵያዊ "በጣም ትልቅ ተስፋ ነው" የሚለው ዚያደ እንደ ኢሮብ ግን ሥጋት የሚያጭር ሆኖበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርስ ውልን ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ አደርጋለሁ ማለቱን የሚያስታውሰው ዚያደ "ይኼ የአልጀርስ ስምምነት 30 ሺህ ከሚሆነው የኢሮብ ሕዝብ አንድ ሶስተኛ ያህል ወደ ኤርትራ ሌላው ደግሞ ኤርትራ ላይ ነው የሚቀረው። ይኼ በጣም ትልቅ ጥያቄ ሆኖ እየቀረበ ያለ ስለሆነ ይኼ ነገር ደግሞ ካልተፈታ በዘላቂነት ያ ሕዝብ በዘላቂነት በሰላም ይኖራል ወይ? የሚል ጥያቄ ይመጣብኛል" ሲል ያክላል።

በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት እና ጦርነቱን ተከትሎ አገራቱ በገቡበት ፍጥጫ የትግራይ ሕዝብ የከፋ ኤኮኖሚያዊ ጫና ደርሶበታል የሚለው ሳሙኤል በበኩሉ የክልሉ ነዋሪዎች እና ልሒቃን ልዩነቱ እንዲፈታ ጥረት ሲያደርፉ ቆይተዋል ሲል ይናገራል። ሳሙኤልንም የሚያሳስበው የድንበር አከላለል ጉዳይ ነው።

Äthiopien Proteste gegen die EEBC-Entscheidung
ምስል DW/A. Desta

ሳሙኤል "የድንበሩ ጉዳይ አፈታቱ ሕዝባዊ መሠረት መያዝ አለበት። ከፖለቲካ ውሳኔ ውጭ ሆኖ ለሕዝቡ መሠጠት አለበት። ሕዝቡ የት እንደሆነ ድንበሩ ጠንቅቆ ያውቃል" ሲል ተናግሯል።

ሉዋም የጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሁለትዮሽ መግለጫ እንዴት ወደ ተግባራዊ ኤኮኖሚያዊ ስምምነት ይቀየራል የሚለው ጉዳይ ወደ ፊት የሚታይ እንደሆነ ብታውቅም ተስፈኛ ናት። "በጣም ተስፈኛ ነኝ። ምክንያቱም ይኸ በመንግሥታት መካከል ብቻ የሚፈጠር ሰላም አይደለም። በሁለቱም አገሮች የሚፈልጉት ነው። አፍሪካ እያደገች ነው። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኤኮኖሚም እያደገ ነው። ቻይና የሁለቱም አገሮች የንግድ አጋር ሆና ቆይታለች። በመላው አፍሪቃ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት ዝቅተኛ ነው። ይሁንና ካላቸው የተለየ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ቁርኝት አኳያ ያን ችግር መፍታት እና በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የቀጣና  የንግድ ግንኙነት ያድጋል ብዬ አስባለሁ"

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ