1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኖርማንዲ ዘመቻ እና የኃያላኑ አቋም

ሰኞ፣ ሰኔ 2 2006

ጦር አዛዦች ወደ ፊልድ ማርሻል በርናርድ ሞንትጎመሪ እና ወደ ጄኔራል ኦመር ብራንድልያ ዞር አሉና «እንቀጥላለን» አሉ።ሰኔ ስድስት 1944---የኖርማንዲ ሰማይ ሰዉ እንደ ዶፍ-ይዘንብበት ገባ።ሐምሳ ሺሕ የሚገመተዉ የጀርመን ወታደር በመቶ-ሐምሳ ሺሕ የተባባሪዎቹ ሐገራት ወታደሮች ተጥለቀለቀ።ባሕሩም ምድሩም፤ ሰማዩም አስከሬን ይለብቀዉ ያዘ።

https://p.dw.com/p/1CF4e
ምስል picture-alliance/AP Photo

የኖርማንዲ ዘመቻ ወይም ዲ-ዴይ፤የጀርመን ናትሴን ለመዉጋት ባንድ ያበሩት የሞስኮ፤ ለንደን ዋሽንግተን ተባባሪዎችአሰቃቂዉን ጦርነት በድል የማጠናቀቃቸዉ ጉሉሕ ምልክትነቱ ሲነገር፤ ሲመሰከር፤ ሲዘከር ባለፈዉ አርብ ሰባኛ ዓመቱን ደፈነ።ዘመቻዉና በዘመቻዉ የበረቀዉ ድል የናትሴዎች ፍፃሜ ከመሆኑ እኩል፤ በጦርነቱ ሰበብ የተወዳጁት የቀድሞ ጠላቶች፤የወዳጅነታቸዉ ማብቂያምነበር።ስታሊን፤ሩዘቬልት፤ቸርችልና ደጎልን እኩል ያስፈነደቀዉ የኖርማዲ ዘመቻ፤ ዘንድሮ በሰባኛ ዓመቱምየሚወጋገዙ፤የሚወነጃጀሉ፤ የሚዛዛቱትን የሞስኮ፤ዋሽንግተን፤የለንደን፤ ፓሪስ፤በርሊን መሪዎችን አኩል አሰለፈ።የዘመቻዉዝክር መነሻ፤የጠላቶቹ ወዳጅነት፤ የወዳጆቹ ጠላትነት የድሮ-ዘንድሮ እዉነት ማጣቀሻ፤ ለዐለም የተርፈዉ ዳፋ መድረሻችንነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

« ኖርማንዲ ላይ የዚያን ቀን የሆነዉ እና የፈነጠቀዉ ለኛ እስካሁን ድረስ አንፀባራቂ ብርሐን ነዉ።የዚን ጊዜ 150 ሺሕ የኢንግላንድና የዩናይትድ ስቴትስ ወንዶች እዚሕ አረፉ።እኒያ ወታደሮች እኛን ለማዳን በአዉሮፕላን እና በሔሊኮብተር በርረዉ በጃንጥላ እዚሕ አረፉ።»

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ-ባለፈዉ አርብ።ለድል አድራጊዎቹ ኖርማንዲ ላይ የዚያን ቀን የፈነጠቀዉ ብርሐን ለተቀረዉ ዓለም-እንደ ድል አድራጊዎቹ ሁሉ ብርሐን-ይሁን ወይም በተቃራኒዉ ጨለማ -ብዙ ያነጋግር ይሆናል።የዚያን ዕለቱ-ዘመቻና ዘመቻዉ ያበሠረዉ ድል የእስከዚያ ዘመኑን የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት መለወጡ ግን በርግጥ አያጠያይቅም።

ለዚያች ቀን ያደረሰዉ የኃያላኑ መንግሥታትም ጉዞ አስቸጋሪ፤ዉስብስብ፤ እንዳዴም ግራ አጋቢነቱም ሐቅ ነዉ።ነገሩ እንዲሕ ነበር።በ1930ዎቹ ማብቂያ-(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎአ ነዉ) እስያ የጠበባቸዉ የጃፓን ወታደራዊ ገዢዎች እብጠት ለዩናይትድ ስቴትስም ይተርፍ ይሆናል ብለዉ፤የዋሽንግተን፤ ለንደን ፓሪስ መሪዎች ለመጠንቀቅ፤ ማስተንተን ቀርቶ ለማስብ እንኳን የፈለጉ አይምስሉም።ወይም አልቻሉም።እንዲያዉም የቶኪዮ ገዢዎች «ግዛታችንን ለማስለስ»በሚል ሰበብ መጋቢት 1938 ሶቬት ሕብረትን ሲወርሩ የዋሽግተን፤ለንደንና ፓሪስ መንግሥታት የሞስኮ ኮሚኒስቶችን የሚያዳክምላቸዉ ኃይል ያገኙ ያክል ነበር የተደሰቱት።

Jalta Konferenz 1945
ምስል picture-alliance/dpa

ጦርነቱ በሶቬት ሕብረት አሸናፊት ተጠናቀቀ።ነሐሴ1938።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዲ ሩዘቬልት የኮሚንስቶቹን ድል፤ ጥንካሬና እድምታዉን የማዉጣት ማዉረዳቸዉን ያክል፤የጃፓኖችን ፍላጎት፤ ዕቅድናአላማ ለማስተንተን፤ ማሰልል ሞክረዉ ቢሆን ኖሮ ፕርል ወደብ ላይ ሥለተደገሠላቸዉ ጥፋት ፍንጭ ባገኙ ነበር።

ሩዘቬልት፤ ቶኪዮዎችን ጨርሶ ትተዉ፤ የሞስኮዎችን ቀጣይ እርምጃ በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጠዉ አዉሮጳን ለመስልቀጥ በርሊን ላይ የሚያቅራራዉ ፉሕረር አዶልፍሒትለር ሠላም እንዲያስፍንማግባባቱ ላይ አተኮሩ።በአራት ወር ለሁለተኛ ጊዜ ሒትለርን የሚማፀን ደብዳቤ ላኩ።

እንደ ሩዘቬልት ሁሉ ቶኪዮዎችን ረስተዉ፤ በሞስኮዎች ድል የሚጤስ ንዴታቸዉን አምቀዉ ከሒትለር ለበቅ ለመዳን የሚራወጡት የለንደንናየፓሪስመሪዎችየሮማፋሺቶችን አግባባብተዉ የሒትለርን የእብሪት «ዛር»ለመሶረፍ ገሚስ ቸኮዝሎቫኪያን ጭዳ አደረጉ።እናሰላም ከማያቀዉ፤ ሠላም እንደማያቅ ከሚያዉቁት ሒትለር ጋር«የሠላም»ያሉትን ዉል ሙኒክ-ጀርመንላይ ተፈራረሙ።መስከረም 30 1938።

የፓሪስ እና የለንደን መሪዎች ቸኮዝሎቫኪያን ለበርሊኖች ከመለገሳቸዉ በፊት፤የሮማ ፋሺስቶችን ከበርሊኖች ነጥለዉ ከጎናቸዉ ለማሠለፍ የዚያ ዘመኑ «ቄሳሮች» የኢትዮጵ ሕዝብን-በመርዝ ጋዝ እያንጨረጨሩ ኢትዮጵያን እንዲገዙ ፈቅደዉ ነበር።

አዶልፍ ሒትለር ሐንጋሪን፤ስሎቫክን፤ሩሜንያን እና ሌሎችንም በሐይልም፤በማስፈራራትም፤ በሥምምነትም እያለ ሲጠቀልል ሞሶሊኒ አልባኒያን ዋጠ።በዚሕ ጊዜ ነዉ ሞስኮዎች መጪዉን አደጋ በጋራ እንከላከል የሚል ጥያቄ ለምዕራባዉያኑ ሐያላን ያቀረቡት።

ሚያዚያ 18 1939። ሶቬት ሕብረት የሰወስትዮሽ ወታደራዊ ትብብር እንዲደረግ ለብሪታንያና ለፈረንሳይ ያቀረበችዉን ጥያቄ-ሁለቱ ሐገራት ዉድቅ አደረጉት።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳናት ሩዘቬልትም የንትሴዎቹን ቁንጮ በደብዳቤ ከማባበል አልፈዉ አደጋዉን በጋራ እንከላከል የሚለዉን የነጆሴፍ ስታሊንን ሐሳብ የሚቀበሉት አይነት አልነበሩም።

Bildergalerie D Day Aktuell Feuerwerk
ምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images

የሰወስትዮሹ የትብብር ጥያቄ ዉድቅ የሆነባቸዉ የሞስኮ መሪዎች-እንደ ለንደን-ፓሪሶች ሁሉ ከጀርመን ጋር የትብብር ዉል ለመፈራረም ወሰኑ።ነሐሴ-23 የሞሎቶቭ-ሪብንትሮፕ ተብሎ የሚጠራዉ ስምምነት ለበርሊንም፤ ለሞስኮም ጊዜ ከመግዛት ባለፍ ብዙም እንደማይፈይድ ሁለቱም ያዉቁታል።ግን ፈረሙት። ነሐሴ-23 1939።

በሳምንቱ ጀርመን ፖላንድን ፈጥርቃ ያዘች።ከዚያ በፊት ከኢትዮጵያ እስከ ሊቢያ፤ ከአልባኒያ እስከ ስሎቫኪያ የተደረገዉ ዉጊያ ጦርነት ያልሆነ-ይመስል የዚያን ቀን ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፈነዳ ተባለ።መስከረም 1 1939።

በተከታዮቹ ዓመታት አዉሮጳ ስትጋይ፤ ዩናይትድ ስትቴትስ በጢስ ስትታፈን፤ በተለይ ፕርል-ወደብ ሲወድምባት- በሐያላኑ መግሥታት መካክል የበረዉ-ሁሉ እንዳልነበር ሆነ።ሙኒክ ላይ በፈረሙት ሥምምነት መሠረት «የተወዳጁት» የለንደን- ፓሪስ፤ የበርሊን-ሮም መንግሥታት እሁለት ተገምሱ። ጠመንጃ ተማዘዙ። የሞሎቶቭ-ሪበንትሮፕ ዉልም ፈረሰ።

ፓሪሶች ሐገራቸዉን ተቀምተዉ-ሲሰደዱ፤ የለንደን፤ ዋሽግተን ጥብቅ ወዳጆች-በ1939 እንቢኝ ያሉትን ጥያቄ አፍርሰዉ ከኮሚንታዊቷ ጠላታቸዉ ከሞስኮ ጋራ ተወዳጁ።በርሊኖች-ከሙኒክ ተሻራኪዎቻቸዉ ሮማዎችን አስቀርተዉ፤ ከቶኪዮ ገዢዎች ጋር የብረት (የደምም) ይባል ነበር ዛቢያ (አክሲስ) ባሉት ዉል ተወዳጁ።ሁሉም ለአሰቃቂ ጦርነት።

ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳናት ባራክ ኦባማ የኖርማንዲዉ ዘመቻ ሰባኛ ዓመት ባለፈዉ አርብ ሲከበር እንዳሉት ሚሊዮኖችን የፈጀዉ ጦርነት በዋሽግተን፤ ለንደን ሞስኮዎች ትብብር ድል አድራጊነት ባይጠናቀቅ ኖሮ-የዓለም ፖለቲካዊ-ምጣኔ ሐብታዊ ሥርዓት ሌላ መልክና ባሕሪ በያዘ ነበር።

«በዚያ ጦርነት የተቀዳጀ ነዉ ድል ምዕተ-ዓመቱን የቀረፀ ብቻ ሳይሆን፤ የመላዉ ሰብአዊ ፍጡርን ደሕንነት ያረጋገጠም ነዉ።ያንን መጥፎ ሁኔታ ለማስወገድ በሕብረት ጥረናል።በስተመጨረሻዉ ግንብና የብረት አጥሩ እስኪ ፈርስ ድረስ ታግለናል።ከምዕራብ አዉሮጳ እስከ ምሥራቅ፤ ከደቡብ አሜሪካ እስከ ደቡብ ምሥራቅ እስያ የሰባ ዓመት የዴሞክራሲ ንቅናቄ ተሠራጭቷል።ሕይወታቸዉን መስዋዕት ለማድረግ የቆረጡና የሚመኙትን ያልኖሩት ወገኖች ባይሰዉ ኖሮ-ይሕ ሁሉ በጎ ነገር ባልኖር ነበር።»

የጀርመን፤የኢጣሊያና የጃፓን እብሪተኞችን ለመቅጣት በጋራ ያበሩት ሕይላት በጋራ ለማበር ብዙ ጊዜ እንደፈጁ ሁሉ ኖርማንዲ ላይ የታየዉን የድል-ብሥራት ለመወሰን ብዙ እቅማምተዉ፤ አንግገራግረዉም ነበር።የማቅማማት፤ ማንገራገሩ ሰበብ ደግሞ የመጀመሪያዉ ጠያቂ ኮሚስታዊት ሶቬት ሕብረት መሆኗ ነበር።

ሩብ ያሕል ግዛታቸዉ በጀርመኖች የተያዘባቸዉ የሶቪየት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን የዩናይትድ ስቴትስ፤ የብሪታንያና የሌሎች የምዕራብ ተባባሪ መንግሥታት ጦር በምዕራብ አዉሮጳ በኩል በጀርምን ጦር ላይ ጥቃት እንዲከፍት ደጋግመዉ ጠይቀዉ ነበር።

60 Jahrestag D-Day Frankreich
ምስል AP

የስታሊን ጥያቄ-ጀርመኖችን ከምሥራቅና ምዕራብ ለሁለት አቃርጦ ለመቀጥቀጥ ፤ በሶቬት ሕብረት ላይ ያረፈዉን ወታደራዊ ጫና ለመቀነስ ያለመ ነበር።ሁለት ጠላቶች ን እርስ በርስ ካላተሙ በኋላ አንዱን ጠላት በሌለኛዉ ጠላት አስደፍልቆ-የተዳከመዉን ሁለተኛ ጠላት በቃላሉ በመፈንገል የመጨረሻዉን ድል በመቆናጠጥ ሥልት የተካኑት ምዕራባዉያን በተለይ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችል የሳታሊንን ተደጋጋሚ ጥያቄ በተደጋጋሚ ዉድቅ አደረጉት።

የሞስኮዉ ቆፍጣና አልተበገሩም።ቸርችልን ገሸሽ አድረገዉ ሩዘቬልትን ማግባባት ያዙ።ሰወስቱ መሪዎች ለመጀመሪያ ጉባኤያቸዉ ቴሕራን-ኢራን ላይ ሲሰበሰቡ በጀርመን ላይ በምዕራብ አዉሮጳ በኩል ሌላ የጦር ግንባር ይከፈት የሚለዉን ሐሳብ አፀደቁ።ታሕሳስ 1 1943።

ዝግጅቱ፤ ቦታ መረጣዉ፤ የማሳሳቻ ዉጊያዉ፤ የማደናገሪያ መረጃዉ ይቀለጣጠፍ ያዘ።የጀርመን ጦር አዛዦች በምዕራብ ግንባር ሌላ ጥቃት እንደሚከፈትባቸዉ እርግጠኛ ናቸዉ።መቼ እና የት ለሚለዉ ግን መልስ አላገኙም።ቢሆንም የፈረንሳይን የአትላቲክ ዳርቻ በግንብ፤ በሽቦና ቦምብ ያሳጥሩ ገቡ።

ከለንደን፤ ዋሽግተን እና ሞስኮ የሚንቆረቆርላቸዉን የሐስት መርጃን በየቀጣጫዉ ከሚከፈተዉ የማሳሳቻ ተኩስ ጋር እያቀናጁ ሲያስተነትኑ ደግሞ ጠላቶቻቸዉ ግንቦት ላይ በተለይ ካሌ በተባለዉችዉ የፈረንሳይ ከተማ በኩል ጥቃት ይከፍታሉ ወደሚለዉ ሐሳብ አዘነበሉ።

ፈረሳይ የሰፈረዉ የጀርመን ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል ኤርቪን ሮሜልና የቅርብ አለቃቸዉ የምዕራብ አዉሮጳ ዕዝ ዋና አዛዥ ፊልድ ማርሻል ጌርድ ፎን ሩንድሽታንድ-አትላቲክ ባሕር ጠረፍ ላይ የሚያስገነቡትን መከላከያ ጎብኝተዉ፤የካሌዉ ግንባር እንዲጠናከር አዘዙ።ግንቦት አበቃ።

የተሰነዘረ ጥቃት የለም።«ግንቦት ካበቃ-የባሕር ነዉጥም፤ ነፋስም፤ ዝናብም፤ መቀስቀሱ ሥለማይቀር ለአጥቂ ጦር-አደገኛ ነዉ።» አሰቡ ጀርመኖች።ሐሳቡ በሰሜን አፍሪቃዉ ጦርነት «የበረሐዉ ቀበሮ» የሚል የአድናቆት ቅፅል ያተረፉትን ማርሻል ሮሜልን አሳምኗል።ሰኔ መግቢያ ላይ ቤተሰባቸዉን ሊጠይቁ ወደ ደቡብ ጀርመን ሔዱ።

ካሌ አጠገብ ከሚጀምረዉ ከፈረንሳይ የባሕር ጠረፍ-በወዲያኛዉ ጫፍ ግን የወረራዉ ዕቅድ ተጠናቅቆ-አየሩ ይጠበቃል።ሰኔ አምስ-አየሩ መጥፎ።ዘመቻዉ ተራዘመ።ሰኔ ስድስት 1944። «አየሩ ከትናንቱ ይሻላል፤ ግን ጥሩ አይደለም። «እሺ» አሉ የጦሩ ዋና አዛዥ ጄኔራል ድዋይት ዴቪድ አይዘንአወር የአየር ንብረት ባለሙያዎቻቸዉን ማብራሪያ እንደሰሙ።

D-Day Landung Utah Beach Normandie 1944
ምስል AFP/Getty Images

ወደ ዘማቹ ጦር አዛዦች ወደ ፊልድ ማርሻል በርናርድ ሞንትጎመሪ እና ወደ ጄኔራል ኦመር ብራንድልያ ዞር አሉና «እንቀጥላለን» አሉ።የኖርማንዲ ሰማይ ሰዉ እንደ ዶፍ-ይዘንብበት ገባ።ሐምሳ ሺሕ የሚገመተዉ የጀርመን ወታደር በመቶ-ሐምሳ ሺሕ የተባባሪዎቹ ሐገራት ወታደሮች ተጥለቀለቀ።ባሕሩም ምድሩም፤ ሰማዩም አስከሬን ይለብቀዉ ያዘ።

«የተዘበራረቀ ነገር ነበር።በኛም በጃንጥላ በወረዱት በነሱም በክል ድብልቅልቅ ያለ ነገር ነበር።የት እንዳሉ አያዉቁትም።መጥፎዉ የአየር ጠባይም ለዚሕ አስተዋፅኦ አድድርጓል።መሐላችን ያርፋሉ።አነሱ እኛ መሐል እኛም አነሱ መሐል ነበርን።ሁኔታዉን በግልፅ ለመረዳት ያሁኑን ማወቅ ይገባናል።»

ይላሉ የያኔዉ የጀርመን ወታደር።ካሁኑ በፊት የድሮዉ አለ።የናትሴ ጀርመንን በጋራ ድል ያደረጉት ሐይላት በድል ማግሥት ኮሚንስት ካፒታሊስት በሚል ዓለምን ለሁለት ገምሰዉ ለአርባ አምስት ዓመታት አወዛግበዉ፤ አዋግተዉ፤ አጋድለዉታል።

ፕሬዝዳናት ኦባማ-የግንብና የብረት አጥር ያሉት የበርሊን ግንብ ከተናደ፤ ሶቬት ሕብረትም ከተፈረካከሰች በኋላ የአርባ አምስት ዘመኑ ክፍፍል ያበቃ መስሎ ነበር።ዘንድሮ ግን አንዴ በሶሪያ ሌላ ጊዜ በዩክሬን ሰብብ ዳግም ይወዛገባሉ።የምዕራባዉያን ሐገራትና የሩሲያ መሪዎች የኖርማንዲዉን ዘመቻ ሰባኛ ዓመት ለማክበር ጎን ለጎን መቆማቸዉ፤አብረዉ መመገብ፤ መነጋጋገራቸዉም አልቀረም።መልዕክታቸዉ ግን-ጠብን እንጂ ፍቅርን የሚጋብዝ አይደለም።

«ዛሬ የዓለም ምጣኔ ሐብት በሚያድግበት ወቅት የሩሲያ ምጣኔ ሐብት ባንፃሩ መሪዎቿ በመረጡት (እርምጃ) ምክንያት እዝጋሚ፤ እንዲያዉም ደካማ ነዉ።መንግሥቶቻችን የዩክሬን ሕዝብ ለመደገፍና ለመርዳታ በአንድነት መቆማችንን እንቀጥላለን።»ፕሬዝዳናት ባራክ ኦቦማ፤ የፕሬዝዳናት ቭላድሚር ፑቲን አፃፋ ከረር-መረር ያለ ነበር።

«ጥቅሟን ለማስከበር በመሪዎችዋ ፍቃድና ፍላጎት እጅግ በጣም ጠንካራ ወረራ እና እርምጃ የምትወስደዉ ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ ነች።ይሕ ደግሞ ረጅም ጊዜዋ ነዉ።እኛ ዉጪ ሐገር ያሰፈርነዉ ጦር አለ ማለት አይቻልም።ባንፃሩ የአሜሪካ ጦር በመላዉ ዓለም በየሥፍራዉ አለ።በየደረሱበት ከድንበሮቻቸዉ በሺዎች ኪሎ ሜትሮች የሚኖሩ የሌሎችን ሕዝቦች ዕጣ-ፈንታ የሚወስኑት እነሱ ናቸዉ።»

D-Day Landung Hussars White Beach 06.06.1944 Fallschirmjäger
ምስል Imago

የሩሲያ ኮሚኒስቶች በ1917 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ክሬምሊን ቤተ-መንግሥትን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ጠላት ነበሩ።የጋራ ጠላት ሲነሳ ተወዳጁ።ያወዳጃቸዉ ጠላት ሲጠፋ-ዳግም ጠላት ሆኑ።

ከ1990ዎቹ ጀምሮ ደግሞ ጠላትነታቸዉን አርግበዉ መወዳጀታቸዉን ይነግሩን ነበር።ዛሬ ግን እንደገና ጠላትነታቸዉ ደምቋል።ነገስ?

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ