1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማርኛ ትምህርት በሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ መቶ ዓመት አስቆጠረ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 10 2011

በጀርመን ሀገር ከሚገኙ በርካታ ዩንቨርስቲዎች አንዱ የሆነዉ የሀምቡርግ ዩንበርሲቲ የተመሰረተበትን  መቶኛ ዓመት በማክበር ላይ ይገኛል።በዩንቨርሲቲዉ የአማርኛ ቋንቋ  ትምህርት ሲሰጥም  መቶ ዓመቱን ይዟል።

https://p.dw.com/p/3IcE3
amharisch alphabet
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

የአማርኛ ትምህርት በሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ መቶ ዓመት አስቆጠረ

 

amharisch alphabet
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

ከዓንድ ምዕተ አመት በፊት የሀምቡርግ ፓርላማ፤ ዩንቨርሲቲ ለመሥራት መከረ። እናም  እዚያዉ ሀምቡርግ በግዛቲቱ  ስም ዩንቨርሲቲዉን ለመሥራት ወሰነ። በጎርጎሮሳዊዉ 1919 ዓ/ም የተመሠረተዉ የሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ የተመሠረተበትን መቶኛ ዓመት እያከበረ ነዉ። በዩንቨርሲቲዉ የአማርኛ ቋንቋ  ትምህርትም መቶ ዓመቶኛ ዓመቱን ይዟል። በዩንቨርስቲዉ የአፍሪቃ ጥናት ተቋም ስር የአፍሪቃና የኢትዮጵያ ጥናት ትምህርት ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መምህርና የአፍሪቃ ሥነ-ቃል ተመራማሪ  ዶክተር ጌቴ ገላዬ እንደነገሩን የዩንቨርሲቲዉ የምስረታ በዓሉን ዓመቱን ሙሉ የሚያከብር ቢሆንም በጎርጎሮሳዊዉ  ግንቦት 10 ቀን ግን በተለዬ ሁኔታ የጀርመን የፓርላማ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ከዓንድ ሺህ በላይ እንግዶች በተገኙበት የ100 ዓመቱን ጉዞ የሚዘክርና የወደፊቱን አቅጣጫ በሚያመላክቱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። በዩንቨርሲቲዉ የአማርኛ ትምህርት ክፍልም የመቶ ዓመት ጉዞዉን በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ይገኛል።

ዩንቨርሲቲዉ በተፈጥሮ ሳይንስ ፣ በፍልስፍና ፣ በታሪክ፣ በማኅበረሰብ ሳይንስ በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሚያስተምሩ ክፍሎች አሉት። የእስያና የአፍሪቃ ጥናት ክፍልም ከእነዚህ ትምህርት ክፍሎች ዉስጥ አንዱ ነዉ። ትምህርት ክፍሉ በተለያዩ ጊዚያት ስሙ ተለዋዉጧል። ከመቶ ዓመት በፊት ይህ ተቋም «የቅኝ ግዛት ተቋም» ይባል የነበረ ሲሆን በቅኝ ግዛት የነበሩ ህዝቦችን ባህልና ቋንቋ ለማስተዋወቅ ከእነዚህ ሀገሮች መምህራን እየመጡ ያስተምሩ ነበር። ትንሽ ቆይቶ ግን ጥንታዊ ታሪክ ፣ባህል፣ ቋንቋና ሥነ-ፅሁፍ ያላት እንዲሁም በቅኝ ግዛት ያልነበረች አፍሪቃዊት ሀገር መምህር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ተቋሙ ገቡ። ኢትዮጵያዊዉ መምህር ወልደ ማርያም ደስታ።

«እንደ ጎርሳዊው አቆጣጠር በ1918 ዓ.ም. የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲጠናቀቅ ጀርመን በጦርነቱ ተሸንፋ ስለነበር፤ ከዚህ በኋላ ነዉ እንደገና አዲስ የጀመሩት። እና የኛ ከኢትዮጵያ የመጡት ወልደ ማርያም ደስታ ይባላሉ። በ1919 ነዉ የመጡት። በዚያን ጌዜ የአማርኛ ቋንቋ ፣የኢትዮጵያ ታሪክ ፣ግዕዝ በደንብ ይታወቁ ነበር። ቀደም ብሎም በ1905 እስከ 1907  አለቃ ታዬ ገብረ ማርያም በበርሊን ዩንቨርሲቲ የምሥራቃዊ ቋንቋዎች ክፍል ዉስጥ አማርኛ ያስተምሩ ነበር። በአፄ ሚኒሊክ ተልከዉ። ጀርመናዉያን ምሁራን ከግዕዝ በተጨማሪ ስለ አማርኛ ሰዋሰዉ ስለ መዝገበ ቃላት ስለ አማርኛ ማስተማሪያ መጻሕፍት ብዙ አሳትመዋል። ስለዚህ  የኢትዮጵያ ጥንታዊ ባህል የታወቀ ስለነበር። አማርኛ ክብር ተሰጥቶት በዚያን ጊዜ ትምህርት እንዲሰጥ ከኢትዮጵያ መምህር እንዲመጣ ተደርጓል ማለት ነዉ።»

አማርኛ ቋንቋ በጀርመን ዩንቨርሲቲዎች በ1919 ዓ/ም መሰጠት ይጀምር እንጅ ቀደም ሲልም ቢሆን ኢትዮጵያ ለጀርመኖች ትልቅ የምርምርናጥናት ሀገር ሆና የቆየችዉ። ኢትዮጵያ የራሳቸዉ ፅህፈት፣ ታሪክ ፣ነፃ የመንግሥት አወቃቀር፣ ጥንታዊ የስልጣኔ ካላቸዉና ነፃነታቸዉን ጠብቀዉ ከቆዩ ጥቂት ሃገራት መካከል አንዷ በመሆኗ ጀርመናዉያኑ ምሁራን  ከ17ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነበር በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማድረግ የጀመሩት።

«ከ17ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ  የኢትዮጵያ ባህል፣ ታሪክ፣ ሥነ-ፅሁፍና የጥንት ስልጣኔ በጀርመናዉያን ይጠናል። እና በዚያን ጊዜ ሉዶልፍን አማርኛ ያስተማሩት አባ ጎርጎርዮስ የሚባሉ ከመካነ-ሥላሴ ወይም ከቤተ-አምሃራ ከወሎ ላሊበላ አካባቢ የመጡ ሊቅ ናቸዉ። የግዕዝ የአማርኛና የቤተ ክርስቲያን የፍትሃ ነገስት ሊቅ ናቸዉ ያስተማሩት። ስለዚህ የኢትዮጵያን ባህል የታሪክ ሥነ-ጽሑፍ በጣም አጓጊና ታዋቂ ስለሆነ ቋንቋዉን በደንብ ሲመራመሩ፣ ሲጠብቁትና ሲያጠኑት ነዉ የኖሩት ጀርመናዉያን። ብቻቸዉን ሳይሆን ከኢትዮጵያዉያን ጋር በመሆን»

Fortsetzung des 830. Hamburger Hafengeburtstags
የሀምቡርግ ከተማ በከፊልምስል picture-alliance/dpa/A. Heimken

የጀርመን ተመራማሪዎች በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ የብራና መጻሕፍት፣ ገድላት፣ ዜና መዋዕላትና የታሪክ መፃህፍት ላይ ሀተታና ትርጉም እንዲሁም ንፅፅራዊ ጥናት ያደርጉ የነበረ ሲሆን በአማርኛ ቋንቋም ሂዎብ ሉዶልፍ የተባለ ጀርመናዊ የአማርኛ ሰዋሰዉ ለመጀመሪያ ጌዜ ማሳተሙን ዶክተር ጌቴ ያስረዳሉ።

በሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ የአንኮበሩ መምህር ወልደ ማርያም ደስታ ከጎርጎሮሳዊዉ ከ1919 እስከ 1925 ዓ/ም የአማርኛ ቋንቋን ሰዋሰዉ፣ሥነ-ጽሑፍና ንግግር ኦጉስት ክሊንገን ሄቨን ከተባሉ ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ጋር በመሆን ካስተማሩ ወዲህ በዩንቨርሲቲዉ ባለፉት መቶ ዓመታት በርካታ ምሁራን ቋንቋዉን አስተምረዋል።

በአፍሪቃ ጥናት ተቋም ከአፍሪቃ ቋንቋዎች ሃዉሳ እና ኪስዋሂሊ ቋንቋዎች የሚሰጡ ሲሆን በጀርመናዊዉ ተመራማሪ ሒዮብ ሉዶልፍ ስም የተሰየመዉ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋምም ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ አልፍ አልፎም ቢሆን የኦሮምኛ ፣የትግርኛ እና የሶማልኛ ቋንቋዎችን ያስተምራል።

በመሆኑም ጀርመን ተወልደዉ ያደጉ ኢትዮጵያዉያን እና ኤርትራዉያን ተማሪዎች አሁን አሁን ቋንቋ ለመማር በብዛት ወደ ተቋሙ እየመጡ መሆኑንም ዶክተር ጌቴ ገልፀዋል።

ተቋሙ በመቶ ዓመት ቆይታዉ ከኢትዮጵያዉያን እና ከጀርመናዉያን በተጨማሪ ከተለያዩ ዓለም ሃገራት የመጡ  በባህል፣ በሥነ-ልሳን፣ በታሪክ፣ በአንትሮፖሎጅ ፣ በቋንቋ በተለይም በግዕዝ ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች ላይ ምርምር የሚያደርጉ በርካታ ተመራማሪዎችን አፍርቷል። የሒዮብ ሉዶልፍ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች በተጨማሪ የሀገሪቱን ፊደል ፣ ታሪክ፣ ጥንታዊ ስልጣኔ ፣ ባህል፣ አመጋገብ ፣ ሙዚቃ ፣ እምነት እና የበዓላት  አከባበርና ኅብረ-ብሄራዊነት ጭምር ያስተምራል። ተቋሙ ከጥንታዊ  ንግግር እና ሰዋሰዉ፣ እንዲሁም መዝገበ ቃላት  በተጨማሪ ዘመናዊ የአማርኛ ሥነ-ጽሑፍም በትምህርቱ ተካቶ እንደሚሰጥ ተመራማሪዉ ዶክተር ጌቴ ገላዬ ያስረዳሉ።

በጀርመን ሀገር በበርሊን፣ በማይንዝ ፣በላይፕሲግ ዩንቨርሲቲዎች ጭምር የአማርኛ ቋንቋን  የኢትዮጵያ ጥናት  ባለሙያዎች  ሲያስተምሩ እና ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። የአማርኛ ቋንቋ ከጀርመን ዉጭም ፈረንሳይ ፣ጣሊያን እና እንግሊዝን በመሳሰሉ የአዉሮፓ ዩንቨርስቲዎች ይሰጥ ነበረ። በአሁኑ ወቅት ግን ቋንቋዉ በጀርመን በሃምቡርግ ዩንቨርስቲ ብቻ የሚሰጥ ሲሆን በሌሎች የአዉሮፓ ዩንቨርስቲዎችም ድሮ የነበረዉን ያህል ትኩረት እያገኜ እንዳልሆነ ነዉ ፤ተመራማሪዉ ዶክተር ጌቴ ገላዬ የሚናገሩት። ምክንያቱን በሀገር ዉስጥ ለቋንቋዉ  የተሰጠዉ ትኩረት ከመቀነሱ ጋር ያያይዙታል።

በመሆኑም አማርኛንም ይሁን ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ከባሕር ማዶ ሰዎች ይልቅ እኛዉ ባለቤቶቹ ልንከባከባቸዉ እንዲሁም ለትዉልድ ልናስተላልፍ ይገባል ሲሉም ዶክተር ጌቴ ያሳስባሉ። በዚህ ረገድ መንግሥት ፣ ወላጆች ፣ ትምህርት ቤቶች እና የምርምር ተቋማት በርትተዉ ሊሠሩ ይገባልም ብለዋል። በሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ የአፍሪቃ ጥናት ተቋም ስር የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናት ትምህርት ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መምህር እና የአፍሪቃ ሥነ-ቃል ተመራማሪ  ዶክተር ጌቴ ገላዬ።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ