1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ፦ ለምን?

ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2011

​​​​​​​የኢትዮጵያ መንግሥት 1.2 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ከ«የዓለም ባንክ» እንደሚያገኝ የተገለጠው በዚሁ በያዝነው ሳምንት ነው። ለኢትዮጵያ የሚሰጠው መጠነ ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ ጠቀሜታው እና ተግዳሮቱ እንዴት ይቃኛል? በከፊል ብድር እና ከፊል ርዳታ የሚሰጠው ገንዘብ ለተባለለት ዓላማ ስለመዋሉስ ምን አይነት ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል?

https://p.dw.com/p/37m8y
NO FLASH Weltbank in Washington
ምስል AP

1.2 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለኢትዮጵያ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም «የዓለም ባንክ» ከ13 ዓመታት ወዲህ ለኢትዮጵያ መንግሥት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ለመጀመሪያ ጊዜ ቃል ገብቷል። ሰሞኑን የዓለም ባንክ ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት የወሰነው በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የታየው ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የለውጥ መንፈስ ብሎም ተነሳሽነትን ለማበረታታት እንደኾነ ዐስታውቋል። 

ኢትዮጵያ  ከ14 ዓመታት በፊት፤ በ1997 ዓም ያከናወነችው ሀገራዊ ምርጫ፤ ደም በማፋሰስ መቋጨቱ የዓለም ባንክን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፊታቸውን ከመንግሥት አዙረው እንዲቆዩ አድርጓል። የፖለቲካ እና የሰብአዊ መብቶች ጭቆና ብሎም በደል፤ እንዲሁም ኢኮኖሚው በዋናነት በመንግሥት ቁጥጥር ስር መውደቁም ተቋማቱን ለማራቁ እንደምክንያትነት ይጠቀሳል። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን መንበሩ ከመጡ ወዲህ ግን በፖለቲካውም ኾነ በኢኮኖሚው ዘርፍ የለውጥ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ዋና ተጠሪ ካሮሊን ቱርክ ለኢትዮጵያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጠው «በሀገሪቱ እየታየ ነው» ያሉትን ለውጥ ለማፋጠን እንደኾነ የዓለም አቀፍ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ላይ ተናግረዋል። የፖሊሲና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም በበኩላቸው የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ባንክ እንደ ርእዮተ-ዓለም ከሚከተለው አመለካከት ጋር የሚሄዱ ነገሮችን ለመፈጸም በመዘጋጀቱ የተነሳ ነው ብለዋል።   

«ሊመጣ ያለውን የለውጥ ርምጃዎች መደገፋቸውን ለማረጋገጥ፤ እንዲሁም ሀገሪቱ እየሄደችበት ወይንም ልትሄድበት የፈለገችበትን አቅጣጫ በአጠቃላይ ለመደገፍ፤ በአንድ በኩል ደግሞ አቅጣጫው እነሱ የሚያምኑበት ስለኾነ ወይንም ደግሞ እነሱ በሚያስቡት መንገድ እየሄደ ያለ ስለኾነ ነው። ያ ማለት በዋናነት የግል ዘርፉን ማበረታታትን፤ ለገበያ በቂ የኾነ ቦታ መስጠትን፤ በተወሰነ ዘርፍ መንግሥት የነበረውን ጠቅላይነት (monopoly) መቀነስን ግምት ውስጥ ያስገባ፤ ግልጽ የኾነ የመንግሥት አሠራርን በመከተል ረገድ፤ የሕግ ተጠያቂነትን ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች[ን በመመልከት ነው።]እንግዲህ እነዚህ አቅጣጫዎች ዓለም ባንክ በአጠቃላይ እንደ ርእዮተ-ዓለም ከሚከተለው አጠቃላይ አመለካከት ጋር የሚሄዱ ስለኾነ እሱንም ለመደገፍ፤ የሚደረግ ጥረት ነው  ብዬ ነው የማስበው እኔ።»

Addi Abeba Straßenbahn
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

በእርግጥም ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማክሰኞ ግንቦት 28 ቀን፤ 2010 ዓም ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች የአቶ ጌታቸው ተክለማርያምን ሐሳብ የሚያጠናክሩ ናቸው።  ከዛሬ አምስት ወራት በፊት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል፦ በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ አንዳንድ ግዙፍ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲዘዋወሩ የሚለው ይገኝበታል። እነዚህ ግዙፍ ተቋማት፦ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የመብራት ኃይል አገልግሎት፣ የባቡር መጓጓዣ አገልግሎት፣ የስኳር ምርት ፋብሪካዎች፣ የኢንዱስትሪ መስኮች፣ ሆቴሎች እና የማምረቻ ድርጅቶችን ያካተቱ ናቸው። አቶ ጌታቸው የዓለም ባንክ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለምን ዓላማ ሊውል እንደሚችል እንዲህ ያብራራሉ።

«ዓላማው እንግዲህ በዋናነት ልንለው በምንችል ኹኔታ በኢኮኖሚው ውስጥ በአጠቃላይ  የግል ዘርፉ ያለውን ተሳታፊነት ማሻሻል ለሚል ዓላማ የሚውል ነው፤ በአጠቃላይ ልንለው በምንችል መልኩ። ግን የግል ዘርፍ ተሳትፎ በምንልበት ሰአት እንግዲህ ከፋይናንሱ ዘርፍ ጀምሮ፤ እስከ መሠረተ-ልማት ጨምሮ፦ ለምሳሌ በአዲስ መልኩ  በተዋቀረው የመንግሥት እና የግል ዘርፎች ጥምረት ወይንም (public-private partnerships)  በምንላቸው ዘርፎችም ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚል ዓላማዎች የያዘ ነው። በጣም ብዙ ዓላማዎችን ነው የያዘው፤ ዘርፎቹ ይለያያሉ ግን ከመሠረተ-ልማት እስከ ፋይናንስ በሚደርሰው የኢኮኖሚው የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ያለውን የግል ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ተሳትፎ ማሻሻል  የሚል ዓላማ የያዘ ነው።»

የዓለም ባንክ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ አነስ ወዳለ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት ተርታ (a lower-middle-income country) ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ለማፋጠን እንደኾነ ገልጧል። ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ላይ ተነስቶ ከሚሰጠው ከአጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ፦ 600 ሚሊዮን ዶላሩ ብድር ቀሪው 600 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ርዳታ ነው ተብሏል። የፖሊሲና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም መሰል የገንዘብ ድጋፎች ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ ይናገራሉ።

«የረዥም ጊዜ ብድር ብዙ ጊዜ በዐሥር ከዐሥር ዓመታት በላይ ባሉ ዓመታት የሚከፈሉ ናቸው። እነዚህ [ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሃገራት በዝቅተኛ ወለድ የሚሰጡ ብድሮች] (concessional loan) የምንላቸው ከዐሥር እስከ ሃያ ዓመታት የሚደርሱ የክፍያ ጊዜ ያላቸው ናቸው። ወለዳቸውም በጣም ትንሽ ሊባል የሚችል ነው። ከ2,5 እስከ 4 በመቶ የሚደርስ ነው። ግን አኹን ትልቁ ችግር ለእንደዚህ አጠቃላይ ሥርዓትን (system) ለማሻሻል፤ አሠራርን ለማዘመን፤ የገበያ ተሳታፊዎችን አቅም ለመገንባት፤ በገበያ ውስጥ ያሉትን ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚመጡ የምንወስዳቸው ብድሮች ለተባለላቸው ዓላማ ጥብቅ በኾነ የአፈጻጸም መከታተያ መንገድ መዋል ካልቻሉ በስተቀር መሠረተ-ልማት ላይ እንደምናውላቸው ብድሮች በቸልተኝነት ብንመለከታቸው የምንላቸውን ውጤት ወይንም በገንዘብ ቋንቋ [የመዋዕለ-ንዋይ ጥቅሙ ከወጪው ጋር ተካፍሎ የሚገኘው ውጤት] (return on investment) ማምጣት የሚችሉ ገንዘቦች አይደሉም።»

Bauboom in Addis Ababa, Äthiopien
ምስል picture alliance/dpa/D. Kurokawa

የዓለም ባንክ ፕሮዤዎች ግብረ-ኃይል ኃላፊ ናታሊያ ማይሌንኮ የገንዘብ ድጋፉ በምን ዘርፎች ላይ ሊውል እንደሚችል በዓለም ባንክ መግለጫ ላይ ዘርዝረዋል። እንዲህ ይነበባል፦ «የእድገት እና ተፎካካሪነት እንቅስቃሴ የመንግሥት መርሐ-ግብርን  እና የለውጥ ዕቅዶችን በሦስት ዋና ዋና መሠረታዊ ጉዳዮች በቀጥታ ይደግፋል። እነሱም ለልማት የገንዘብ አቅርቦትን ማሳደግ፤ የመዋዕለ-ንዋይ አውድን ማሻሻል፤ የገንዘብ ተቋማትን ማሳደግ፤ እንዲሁም ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ማበረታታት ናቸው።»

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ የሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥብቅ ክክትል ለማድረግ የሚያስችሉ መንገዶች በዓለም ባንክ እና በመንግሥት ሊበጁ እንደሚገቡ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

«እስከ ዛሬ ከምናያቸው አንጻር በጣም ብዙ በአፈጻጸም ረገድ የምናያቸው ጎዶሎዎች ለሚኖሩ ገንዘቡ ለተባለለት ዓላማ፤ ከዛ ውጪ ደግሞ አጠቃላይ ምክንያቱም ይኼ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደመኾኑ ዘላቂ የኾነ መዋቅራዊ ለውጥን ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ፤ ርስበራሳቸው የሚፈጸሙ ፕሮዤዎችም ርስበራሳቸው ተሳስረው፣ ተናበው አጠቃላይ በኢኮኖሚ ደረጃ የምንፈልገውን ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መልኩ መኾኑን ማረጋገጥ ከዓለም ባንክም ከመንግሥትም፤ እንደዚሁም ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት [ያስፈልጋል።] መንግሥት በምንልበት ጊዜ ግብር ከፋዩ አለ፤ ዓለም ባንክ በምንልበት ጊዜ ከተለያዩ ርዳታ ሰጪዎች የሚመጣ ገንዘብን የሚያስተዳድር ተቋም እንደመኾኑ መጠን የውስጥም የውጭም የተጠያቂነት መንገዶች ያስፈልጉታል።»

የዓለም ባንክ ከረዥም ጊዜ ወዲህ ለኢትዮጵያ መንግሥት እጆቹን ሲዘረጋ በአንጻሩ መንግሥት የከፋ ድህነትን እንዲያከትም ብሎም የጋራ ብልጽግና ማጎልበቱ ላይ እንዲጠነክር በማሳሰብ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተስፋለም ወልደየስ