1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የክፍለ ሃገር ምርጫ አሸናፊና እንደምታዉ

ሰኞ፣ ግንቦት 7 2009

ባለፈዉ እሁድ የክፍለ ሃገር ምርጫን ያካሄደዉ በጀርመን ከፍተኛ ሕዝብ የሚኖርበት የኖርዝራይን ዊስ ፋልያ ግዛት የክርስትያን ዴሞክራቶቹ «CDU» ፓርቲ 34,5 በመቶ አብላጫ ድምፅን በማግኘት አሸንፏል። ግዛቲቱን በጣምራ ሲያስተዳደሩ የነበሩት አረንጓዴዎቹና የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ቦታዉን ለ ክርስትያ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አስረክበዋል።

https://p.dw.com/p/2d0RQ
Deutschland Nach der Landtagswahl in Nordrhein-Westfalen - CDU
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

mmt Q&A (NRW _CDU gewinnt Wahl) - MP3-Stereo

የጀርመኑ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠንካራ ይዞታዉ ነዉ ተብሎ በሚነገርለት የሀገሪቱ ምዕራባዊ ፌደራላዊ  ግዛት ያጋጠመዉ የምርጫ ሽንፈት የፓርቲዉን ቀጣይ ጉዞ አዳጋች እንደሚያደርገዉ ሊቀመንበሩ አመለከቱ። በጀርመንኛ ምህጻረ ቃሉ SPD በመባል የሚታወቀዉ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ትናንት በተካሄደዉ ምርጫ በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ማለትም CDU መበለጡ ደጋፊዎቹንም ታዛቢዎችንም አስደምሟል። የSPD ሊቀመንበር ማርቲን ሹልስ ዛሬ አስቸጋሪ ያሉት የትናንቱ ዉጤት ፓርቲያቸዉ በመስከረም በብሄራዊ ደረጃ በሚካሄደዉ ምርጫ የሚኖረዉን ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ አድርጎታል። በተቃራኒዉ ስደተኞችን በተመለከተዉ መርሃቸዉ ምክንያት ድጋፍ እያጡ መሄዳቸዉ ለሚነገርላቸዉ ለአንጌላ ሜርክል ፓርቲ የዚህ ግዛት የምርጫ ዉጤት ብርታት እንደሆነዉ ተገልጿል። በትናንቱ ምርጫ CDU 33 በመቶ ሲያገኝ፤ SPD የመራጩን 31,2 በመቶ ድምጽ ብቻ ነዉ ያገኘዉ። ዉጤቱ ይፋ ሲሆንም ሹልስ የተሰማቸዉን እንዲህ ነበር የገለጹት።

«ይሄ ለSPD በጣም አስቸጋሪ ቀን ነዉ፤ ለእኔም በግሌ በጣም ከባድ ቀን ነዉ የሆነብኝ። እኔ በዛሬ ዕለት ክፉኛ ከተሸነፍንበት አካባቢ ነዉ የተገኘሁት።»

የኖርድራይን ቬስትፋለን ፌደራል ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሶሻል ዲሞክራቷ አናሎረ ክራፍት ፓርቲያቸዉ መሸነፉ እንደተነገረ ከስልጣናቸዉ ለቀዋል። የግዛቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት መፍጠር የሚችሉበትን መንገድ ለመፈለግ በዛሬዉ ዕለት እየመከሩ ነዉ።

Düsseldorf Hannelore Kraft nach Landtagswahl
ስልጣን የለቀቁት ሶሻል ዴሞክራት አናሎረ ክራፍትምስል Imago/DeFodi

ሶሻል ዴሞክራት ለ 50 ዓመታት በቀዳሚነት ሲያስተዳድር የነበረዉን ቦታ መልቀቅ መገደዱ ለፓርቲዉ ታሪካዊ ሽንፈት የታየበት ምርጫ መሆኑ ተገልፆአል። ባለፈዉ በተካሄደዉ ምርጫ በግዛቱ ፓርላማ ለመግባት የሚያስችል ነጥብን ያላገኙት የነፃ ዲሞክራቶች ፓርቲ «FDP» 12 በመቶ ድምጽን በማግኘት በምርጫዉ ሦስተኝነትን አግኝተዋል። በዚህ ምርጫ ደካማ ሆኖ የወጣዉ የአረንጓዴዉ ፓርቲ  6 በመቶ ድምፅን ሲያገኝ በግዛቱ ፓርላማ መግባት ያልቻሉት የግራዎቹ  ፓርቲ ሆነዋል። «AfD» በመባል የሚጠራዉ ቀኝ ዘመሙ ለጀርመን አማራጭ ፓርቲ 7 በመቶ  ድምፅን በማግኘት ያልታሰበ ከፍተኛ ዉጤት ማምጣቱ ተመክቶአል።  የፊታችን ሰኔ 14 በሚካሄደዉ የጀርመን ሸንጎ ምርጫ ማለት የጠቅላላ ምርጫ ወሳኝ ስለነበረዉ ስለትናንቱ የክፍለ ሃገር ምርጫ ዉጤትና የፖለቲከኞች አስተያየትን በተመለከተ የበርሊኑን ወኪላችንን አነጋግረነዋል።

ይልማ ኃይለሚካኤል

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ