1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጆን ኬሪ የአፍሪቃ ጉብኝት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 22 2006

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል። የስድስት ቀናት የአፍሪቃ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ የሚጀምሩት የኬሪ ትኩረት የሰብአዊ መብቶች ቀውስ በተከሠተባቸው አካባቢዎች የሚሰጥ እርዳታ እንዲሁም የኤኮኖሚ ትብብር እንደሚሆን ተገልጿል ።

https://p.dw.com/p/1BrIw
Paris Treffen Außenminister Ukraine 5.3.2014 John Kerry
ምስል Reuters

ኬሪ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ አንጎላንና ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎን የሚጎበኙ ሲሆን ደቡብ ሱዳንም ሊሄዱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል ። የዶቼቬለው ፊሊፕ ዛንድነር እንደዘገበው፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ በዝግጅት ላይ እያሉ የኢትዮጵያ ፖሊስ ስድስት የኢንተርኔት አምደኞችንና ሶስት ጋዜጠኞችን ማሰሩ የዋሽንግተንን አስተዳደር ቅር የሚያሰኝ እርምጃ ነው ። የኢትዮጵያ መንግስት ለወሰደው ለዚህ እርምጃ የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ወዲያውኑ ነበር እንዲህ ሲሉ ነበር በፅሁፍ አስተያየታቸውን የሰጡት።

«የኢትዮጵያ መንግሥት የታሰሩትን ሰዎች ጉዳይ በቅጡ ተመልክቶ በአስቸኳይ እንዲፈታቸው እንጠይቃለን ። እነዚህን ስጋቶቻችንን ለኢትዮጵያ መንግስት በቀጥታ አንስተናል ። በኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት እና ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ላይ ስላለው ማነቆ ስጋታችንን በተደጋጋሚ አስታውቀናል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለህገ መንግሥታዊ ዋስትና መሉ በሙሉ ተገዥ እንዲሆን እጠይቃለን ። »

Demonstration der Blue Party in Addis Abeba, Äthiopien
ምስል DW

የአሜሪካ መንግሥት በየጊዜው በሚያቀርበው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉን ነገር በኃይል ይቆጣጠራል በማለት ከመንቀፍ የቦዘነበት ጊዜ የለም ። አሁን ጆን ኬሪ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኩራሉ ተብሎ አይታሰብም ። የጉብኝታቸው ዓላማ በሌሎች ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነውና ። ቻተም ሃውስ የተባለው የለንደኑ የምሁራን ቡድን ባልደረባ አሌክስ ቫይንስ እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስ በቀውስ ላይ ለሚገኙት ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን መላ በመሻት ረገድ ኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ ተጓዳኟ ናት ።

«ኢትዮጵያ በተለይ በአፍሪቃ ቀንድ አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚወሰዱ እርምጃዎች ለዩናይትድ ስቴትስ አገናኝ ድልድይ እና ስልታዊ አጋር የሆነች አገር ናት ። ስለዚህ ይሄ ጠንካራ ግንኙነትና ታሪካዊም ነው ። ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ልማት ብቻ ሳይሆን በአቅም ግንባታና በተቋማት ግንባታም ብዙ ገንዘብ አውጥታለች ።»

Angola Ölförderung vor der Küste
ምስል MARTIN BUREAU/AFP/Getty Images

በደቡብ ሱዳን መንግሥትና በአማፅያን መካከል የሚካሄደው ግጭትም በኬሪ አጀንዳ ውስጥ የተያዘ ሌላው ጉዳይ ነው ። ኬሪ ምናልባት በደቡብ ሱዳን አጭር ቆይታ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል ። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት አደራዳሪነት የልተሳካው የደቡብ ሱዳን የሰላም ንግግር የተካሄደባት ከተማ ናት ። በታዛቢዎች እምነት ኬሪ አዲስ ዙር የሰላም ንግግር እንዲጀመር ይፈልጋሉ ። በቫይንስ አስተያየት እጎአ በ2011 ደቡብ ሱዳናውያን ነጻነታቸውን የመረጡበት ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ። ለኬንያው ታዛቢ ባራክ ሙሉኩ ደግሞ የኬሪ የአፍሪቃ ጉብኝት የሚያመለክተው በምዕራቡ ዓለምና በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉት ቻይናንና ብራዚልን በመሳሰሉት የኤኮኖሚ ኃያላን መካከል ያለውን ፉክክር ነው ።

«ምዕራባውያን ሃገራትና አሜሪካ በአፍሪቃ ላይ ያላቸው ተእፅኖ እየቀነሰ ነው ።ወደፊት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ወደ አፍሪቃ የሚያደርጉት መሰል ጉዞ እየጨመረ ነው የሚሄደው ። ይህ በክፍለ ዓለሙ ኤኮኖሚያዊ ተፅእኖ ለማድረግ የሚካሄድ ትግል ነው ።»

ሙሉኩ እንዳሉት ምዕራባውያን ሃገራት በአንድ ጉዳይ ተሳታፊ የሚሆኑት ከራሳቸው ጥቅም ጋር የተያያዘ ከሆነ ነው ። ለዚህም ሙሉኩ ብዙ የነዳጅ ዘይት ሃብት ያላቸውን ደቡብ ሱዳንና አንጎላ በምሳሌነት ያነሳሉ ። አንጎላ ኬሪ በመጨረሻ የሚጎበኟት አገር ናት ።ከዚህ በተጨማሪ ኬሪ በኮንጎ ጉብኝታቸው የምሥራቅ ኮንጎ ግጭትና መፍትሄውም ላይ ይነጋገራሉ ።

ፊሊፕ ዛንድነር

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ