1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር መግለጫ

ዓርብ፣ ጥር 3 2011

የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርኃኑ ጁላ በሃገሪቱ አጠቃላይ የጸጥታ ሁኔታ ሁሪያ መግለጫ ሰጡ፡፡ ጄኔራሉ በምዕራብ ኦሮሚያ ተስፋ ሰንቆ ከውጭ የቆዩ የተለያዩ አካላትን የተቀበለው ህዝብ መልሶ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስበት ተደርጓል፡ ለከፋ ችግርም ተጋልጧል ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3BQEX
Äthiopien General Berhanu Jula PK
ምስል DW/S. Muchie

ይሁንና አሁን እየተወሰደ ባለው ጠንካራ እርምጃ የተዘጉ መንገዶችና አደጋ ላይ የወደቁ የመንግስት የመዋቅር ስፍራዎች ተከፍተዋል፡ ከተማዎችን እየዞሩ የሚያተራምሱ «አባ ቶርቤ» የተባሉ ኃይሎችም በመንግስት ቅጥጥር ስር ወድቀዋል ብለዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን በተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ መከላከያ ሰው አልገደለም ያሉት ጄኔራሉ ክስተቱ እንዲጣራ ተወስኗል፡ መከላከያ የሰው ህይወት አጥፍቶ ከሆነ ግን ይቅርታ ይጠይቃል ካሳም ይከፍላል ብለዋል። ይሁንና የደፈጣ ውግያ ተከፍቶብን ስለነበር የአጸፋ እርምጃ ወስደናል በዚህም የተጎዳ ሰው አለ ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ቆስለዋል ብለዋል፡፡ በትግራይክልል የተፈጠረው የመከላከያ ሰራዊትን ጉዞ የማደናቀፍ ተግባር ስህተት እንደሆነና የፖለቲካ ቁማርተኞች የፈጠሩት ነበር ብለዋል፡ በድርጊቱ የተሳተፉትም ይቅርታ መጠየቃቸውን አብራርተው ይህ ማለት ግን በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች እንዲወጡ በእቅድ የተያዘላቸው የጦር ሰራዊት አባላት አይወጡም ማለት አይደለም ብለዋል፡፡ ጄኔራሉ በሁሉም አካባቢዎች ስለደረሰው ጉዳት ምንም አይነት አሃዛዊ መረጃ መስጠት እንደማይፈልጉም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡ የአዲስ አበባዉ ወኪላችን መግለጫዉን ተከታትሎ ዘገባ ልኮልናል። 

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ