1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬይን፤ የተደናቀፈዉ የአይሮፕላን አደጋ ምርመራ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 12 2006

ምሥራቅ ዩክሬይን ተመቶ የወደቀው የማሌዢያዉ የመንገደኞች ማመላለሻ አይሮፕላንን ተከትሎ፤ የዮክሬይን መንግሥት መፍቀሬ ሩሲያንን ወነጀለ። እንደ ዮክሬይን መንግስት፤ መፍቀሬ ሩስያ ተገንጣዮቹ ከአይሮፕላኑ የተገኙ የምስክር ማስረጃዎችን እያሸሹ እና እያጠፉ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/1Cfak
MH17 Flugzeugabsturz Absturzstelle Ukraine 18.7.2014
ምስል picture-alliance/dpa

አማፂዎቹ 38 አስክሬኖችን ወደ ዳኔስክ ከተማ ወስደዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ የአይሮፕላኑን ስብርባሪዎች ወደ ሩሲያ እያሸሹ ነው፤ ይላል የዮክሬይን መንግሥት ይፋዊ መግለጫ። ምክትል ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ግሮኢስማን ከኪየቭ እንደተናገሩት የዮክሬይን ምሁራን ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ በአማፂያኑ ተከበው ለግማሽ ሰዓት ያህል ብቻ ነው ስለ አደጋው ሊታዘቡ የቻሉት። እንዲሁ የአዉሮጳ የፀጥታ እና የትብብር ድርጅት ታዛቢዎችም ነፃ ሆነው አደጋው የደረሰበት ቦታ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ተናግረዋል። በዛሬው ዕለት የማሌዢያ እና የብሪታንያ መርማሪ ቡድን እንዲሁ እስፍራው ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ዮናይትድ ስቴትስ ከሆነ 300 ገደማ ሰዎችን ያሳፈረው አይሮፕላን ተመቶ የወደቀው በመፍቀሬ ሩሲያ ተገንጣዮች ነው። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሩሲያ በቀጥታም ባይሆን ለደረሰው ጥቃት አብራ ኃላፊነት ወሳጅ ናት ሲሉ ተናግረዋል። የሩሲያ መንግሥት በበኩሉ ወቀሳውን አጣጥሏል።

MH17 Flugzeugabsturz Absturzstelle Ukraine Separatist 19.7.2014
የአዉሮጳ የፀጥታ እና የትብብር ድርጅት ታዛቢዎችምስል imago/Itar-Tass

ዩናይትድ ስቴትስ፤ ጀርመን ፤ የአውሮፓው ሕብረትና የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ድርጅት (NATO)፣ የማሌሺያው የሕዝብ ማመላለሻ አይሮፕላን ዩክሬይን ላይ የወደቀበትን ሁኔታ ዓለም አቀፍ ጠበብት እንዲመረምሩ መጠየቃቸዉ ይታወቃል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ፤ ከዩክሬይኑ አቻቸው ፔትሮ ፖሮሼንኮ ጋር ትናንት በስልክ ባደረጉት የሐሳብ ልውውጥ፤ ዓለም አቀፍ ጠበብት በቦታው ተገኝተው እስኪመረምሩ ድረስ ፣ አይሮፕላኑ በወደቀበት ቦታ አንዳች ለውጥ እንዳይደረግ ከማሳሰባቸውም ፤ አሜሪካውያን ጠበብትን ባስቸኳይ ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። መርማሪዎች አደጋው ወደ አጋጠመበት ቦታ ይገቡ ዘንድ ተኩስ አቁም ይደረግ ሲሉም የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጠይቀዉ ነበር።

መፍቀሬ -ሩሲያ የሚሰኙት የምሥራቅ ዩክሬይን ታጣቂ ኃይሎች ወደሚቆጣጠሩት የዳኔስክ አካባቢ ግዛት መርማሪዎች እንዲገቡ ሳይፈቅዱ እንዳልቀሩ ተነግሮ ነበር። ከኪቭ፣ ሞስኮና ከአውሮፓ የትብብና ፀጥታ ድርጅት የተወከሉ መፍትኄ አፈላላጊ ቡድን አባላት ዋስትና እንዲኖር ተስማምተዉ ነበር። የተ መ ድ የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤትም ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በጉዳዩ ላይ መምከሩ ይታወቃል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፤ ለደረሰው አደጋ፣ በእጅ አዙር የኪቭ መንግሥት ተጠያቂ ነው ማለታቸው ተነግሮም ነበር። ፑቲን፤ በምሥራቅ ዩክሬይን ጦርነት ባይካሄድ ኖሮ ፣የደረሰው አሠቃቂ አደጋ ሊያጋጥም ባልቻለ ነበር ማለታቸዉ ይታወቃል።

MH17 Flugzeugabsturz Absturzstelle Ukraine 18.7.2014
ምስል Reuters

የማሌሺያው የህዝብ ማመላለሻ አይሮፕላን ፣ በምሥራቅ ዩክሬይን ሐሙስ ዕለት መውደቁን ተከትሎ ሜክሲኮ ጉብኝት ላይ የነበሩት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍርንክ-ቫልተር ሽታይንማየር፣ በበኩላቸዉ ፤ «መዘዙ ምን ሊሆን እንደሚችል ከመመከሩ በፊት፤ በአርግጥ ምን እንደሆነ በጥሞና ማወቅ ይኖርብናል። በመጀመሪያ አደጋውን ሲያስቡት አይሮፓላኑ፤ እንዲሁ በቀላሉ ወድቆ ነው የተከሰከሰው ብሎ ለማመን ያስቸግራል፤ ምናልባት ሳይተኮስበት አልቀረምና!» ሲሉ ተናግረዉ ነበር።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ