1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ሀሰተኛ መድሃኒቶችን የሚለየው መተግበሪያ

ረቡዕ፣ ኅዳር 2 2013

የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎች ከሚሰጧቸው የተለያዩ ጠቀሜታዎች አንፃር ተወዳጅነታቸውና ጠቀሜታቸው እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለ ሥልጣንም በቅርቡ «አይቬሪፋይ» የተባለ መተግበሪያ በማበልፀግ ሥራ ላይ አውሏል።

https://p.dw.com/p/3l9wj
Symbolbild Handy Notruf | What3Words application
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Locher

ሀሰተኛ መድሃኒቶችን የሚለየው መተግበሪያ

የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎች መረጃ በመስጠት ጤናማ አኗኗርንና የሰዎች መስተጋብርን በማሻሻል ብሎም  የዕለት ተዕለት ህይወትን በማቃለል  የሚሰጡት ጠቀሜታ ቀላል አይደለም። ከዚህ ባሻገር በህክምናው ዘርፍም የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው።በኢትዮጵያም ጊዜ ያለፈባቸው እንዲሁም ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶች ሽያጭ በህብረተሰቡ ጤና ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመግታት የኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዲጅታል መፍትሄ ይዞ ብቅ ብሏል።
መስሪያ ቤቱ  «አይቬሪፋይ» የተባለ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ በማበልፀግ ጥቅም ላይ ያዋለ ሲሆን፤ ይህ መተግበሪያ ሀሰተኛ መድሃኒቶችን ከትክክለኞቹ ለመለየት እንደሚያገለግል የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄራን ገርባ ይገልፃሉ።
«በአጠቃላይ የቁጥጥር ዘርፉን በቴክኖሎጅ ለማስደገፍ ብዙ ስራ ስንሰራ ቆይተናል።እንግዲህ በቅርቡ ይፋ ያደረግነውን «አይቬሪፋይ»የተባለ መተግበሪያም ስራ አስጀምረናል።» ካሉ በኋላ «ከማምረቻ እስከ ተጠቃሚ  ድረስ ባለው የመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ህጋዊ ያልሆኑ ምርቶች ህጋዊ  እንዳይገቡ ከገቡም ቶሎ የሚታወቁበትን መንገድና ለዚያ ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ ለመፍጠር ነው። በተደጋጋሚ ህብረተሰቡ ሲያነሳ ነበር።ለዚህ ምላሽ ይሰጣል ብለን እናስባለን። ይህንን በቀጣይ እያሳደግን ነው የምንሄደው።አሁን በተለያዬ መንገድ ይህ «አፕሊኬሽን»እየተዋወቀ ነው ።»በማለት ገልፀዋል።
የመድሃኒቶችን ክትትልና ቁጥጥር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም  በባለሙያዎች ብቻ ያከናውን የነበረ ሲሆን  በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን መተግበሪያ በአጋዥነት በመጠቀም የተሻለ ስራ መስራት እንደሚቻል  ሃላፊዋ ገልፀዋል።ይህም በህገወጥ መንገድ የሚገቡና ፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው ያልተጠበቁ መድሃኒቶች ወደ ገበያ እንዳይገቡ ያደርጋል።ህብረተሰቡም ስለሚገዛው መድሃኒት መረጃ እንዲያገኝና የቁጥጥር ስርዓቱ አንድ አካል  እንዲሆን ያስችለዋል።
«የቁጥጥር ስራው የሚቀጥል ነው።ይህ ያንን የሚደግፍ ነው።ህብረተሰቡ የሚገዛዉን መድሃኒት ራሱ በራሱ እንዲያረጋግጥ የሚያደርግ አቅም የሚፈጥር ነው።ህብረተሰቡ የቁጥጥሩ ባለቤት እንዲሆን የሚያደርግ ነው።የሚገዛውን መድሃኒት ህጋዊነቱን አረጋግጦ እንዲገዛ የሚያደርግ «አፕሊኬሽን» ነው።ብለዋል።

China Peking Internet-Zensur
ምስል Getty Images/AFP/G. Baker

መተግበሪያውን ከጎግል ፕሌይ በማውረድ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በነፃ የሚጫን ሲሆን  ተጠቃሚዎች ከመድሃኒት ቤቶች የሚገዟቸውን መድሃኒቶች ስም በመስጠት ወይም መለያ ቁጥሩን «ስካን» በማድረግ በመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ከተመዘገቡ መረጃዎች ጋር በማመሳከር  የመስሪያ ቤቱን የጥራት ቁጥጥር አልፎ የገባ መሆኑንና ትክክለኛነቱን ያረጋግጣል።በዚህም መድሃኒቱ መቼና የት እንደተመረተ፣ የአገልግሎት ጊዜው የሚያበቃበትና የምዝገባ ፈቃዱ  ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎና ተገቢውን የጥራት ቁጥጥር አልፎ ገብቷል ወይ? ስለሚለው ዝርዝር መረጃ ይሰጣል።ህገወጥ ምርት ወደ ተጠቃሚ እንዳይደርስም ያደርጋል።
«ወደ ፊት የሚያመጣዉ ለውጥ የምናየው የምንገመግመዉ ነው።ነገር ግን እኛ ያመጣል ብለን ያሰብነው ለውጥ የህገ-ወጥ ስራውን ይቀንሰዋል ነው።»ነው ያሉት ሀላፊዋ።
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተዘጋጀው የ«አይቬሪፋይ» መተግበሪያ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰራ  ሲሆን በበይነ-መረብ ግንኙነት የሚሰራ ነው።ለወደፊቱ ግን ተደራሽነቱን ለማስፋት ያለ በይነ- መረብ ግንኙነት ለማዘጋጀት ታስቧል።
«ይህንን አፕሊኬሽን ማንኛውም አሁን ባለው ሁኔታ«ስማርት ፎን» ያለው ኢንተርኔት መጠቀም የሚችል ሊጠቀምበት የሚችል ነው።ትልቁ ጥያቄ የኢንተርኔት ተደራሽነት ካልሆነ በስተቀር በአብዛኛው ስልኮቻችን ወደ «ስማርት ፎን» እየተቀየሩ ነው።ቢያንስ በዋና ዋና ከተሞች በክልል ከተሞች መጠቀም የሚያስችል ነው።እኛ ግን የምናስበው «ስማርት ፎን»ያልሆነ እና  «ኦፍ ላይን»የሆነ «ሲስተም» በቀጣይ በሁለተኛውና በሶስተኛው «ቨርዥን» ይህንን እያደረግን ለመሄድ ነው።»በማለት አብራርተዋል።
በሌላ በኩል አብዛናዎቹ መድሃኒቶች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው የምርቱ ዝርዝር መረጃም እንደ ሀላፊዋ በእንግሊዝኛ ነው።በዚህ የተነሳ መተግበሪያው  የተዘጋጀው በዋናነት በእንግሊዝኛ ሲሆን በአማርኛ ቋንቋም በተወሰነ ደረጃ መጠቀም ይቻላል። ለወደፊቱ ግን አጠቃቀሙን ቀላል ለማድረግ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ለማዘጋጀት መታቀዱን አስረድተዋል።
ለመድሃኒት ቤቶች ፈቃድ መስጠት የክልል ተቆጣጣሪዎች ሀላፊነት መሆኑን የሚናገሩት ሃላፊዋ፤ መተግበሪያው  እነርሱ ዘንድም መረጃ በቀላሉ እንዲደርስ  የሚያደርግ በመሆኑ ተገቢውን ቁጥጥር  እንዲያደርጉ ያግዛል።በአጠቃላይ እነዚህን የመሳሰሉ ዲጂታል መፍትሄዎች ተደራሽነትን ለማስፋት፣ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም ስራን ለማሳለጥ ይረዳሉ።እንደ ወይዘሮ ሄራን የመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን ከህገ ወጥ ምርቶች ለመጠበቅም ያግዛሉ። ይህም በሀሰተኛና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ባለፈባቸው መድሃኒቶች ሳቢያ የሚመጣውን የበሽታዎች መድሃኒት የመለማመድ ችግር እንዲሁም  አላስፈላጊ የገንዘብና የሰው ህይወት ጥፋት በመታደግ  ይህ መተግበሪያ በጤናው ዘርፍ  መሻሻልን ሊፈጥር ይችላል። ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያደምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ