1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁለተኛ ቀኑን የያዘዉ የነቀምት ከተማ ተቃዉሞ 

ማክሰኞ፣ የካቲት 20 2010

በኦሮሚያ ክልል በነቀምት ከተማ በትናንትናዉ እለት በተቀሰቀሰዉ ግጭት አንድ ሰዉ መገደሉና 11 ሰዎች መቁሰላቸዉ ተገለፀ።  በዛሬዉ እለትም በከተማዋ ዉጥረት መንገሱንና መደበኛ አገልግሎቶች መቋረጣቸዉን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/2tQIX
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

Protest in Wolega Town. - MP3-Stereo


የኦሮሞ ፌዴራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ከእስር የተፈቱ የፓርቲዉ አመራሮች ከነቀምት ከተማ ህዝብ በተደረገላቸዉ «የእንኳን ደስ ያላችሁ» ጥሪ መሰረት ባለፈዉ እሁድ ወደ ቦታዉ አምርተዉ ነበር።  ይሁን እንጅ ከቦታዉ ሊደርሱ ጥቂት ኪሎሜትሮች ሲቀራቸዉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ወደ ከተማዉ እንዳይገቡ  በጸጥታ ሀይሎች መከልከላቸዉን የፓርቲዉ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ይህንን ተከትሎም  ለመቀበል በዝግጅት ላይ የነበረዉ የከተማዋ ነዋሪ ህዝብ በትናትናዉ እለት ከጸጥታ ሀይሎች ጋር ወደ ግጭት መግባቱን ገልጸዋል።አቶ ሙላቱ ዛሬ ደረሰኝ ባሉት መረጃ መሰረትም በርካታ ሰወች መጎዳታቸዉንና በዚህ የተነሳም ህዝቡ መንገዶች ዘግቶ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
«እኔም አብሬ ሄጀ ነበር እዚያዉ አድረን ነዉ አብረን የተመለስነዉ።እሁድ ዕለት ከትናናት ወዲያ ማታ እዚያዉ ታግተን ነዉ ያደርነዉ።ከትናንት ጀምሮ በነቀምት በኩል ጊምቢ፣ደምቢደሎ፣አሶሳ የሚወስዱ የየብስ መንገድ የለም።አዉቶብስም አይደርስም ህዝብ አግዶታል።መንገድ ተዘግቷል።ዛሬ ደግሞ ወደ 11 ሰወች በጥይት እንደተመቱ ነዉ።አሁን ሆስፒታል ገብተዋል። አንድ ሰዉ እንደሞተ ነዉ የተነገረኝ።ዛሬ የደረሰኝ ሪፖርት ይህ ነዉ።»
ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የነቀምት ከተማ ነዋሪ በበኩላቸዉ በዛሬዉ እለት በከተማዋ  ከፍተኛ ዉጥረት መንገሱንና መደበኛ አገልግሎቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከትናንት ጀምሮ መዘጋታቸዉንም ገልጸዋል።  በተቃዉሞ ሳቢያ የተዘጉ መንገዶችን  ለማስከፈትም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ የፀጥታ ሀይሎች በአካባቢዉ  እየተዘዋወሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በከተማዋ የሚገኘዉ የወለጋ ዩንቨርሲቲ በትናንትናዉ እለት የተማሪወች ምዝገባ እያከሄደ ነበረ ያሉት ነዋሪዉ ፤በዛሬዉ ዕለት ግን በዩንቨርሲቲዉ ዉጥረት መንገሱንና  በርከት ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢዉ ሰፍረዉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ድምፅ የደረሰዉ ጉዳት እንዳሳዘናቸዉ የሚናገሩት  የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ፤ ሁኔታዉን አቤት ለማለት እንኳ መደበኛ አስተዳደር ባለመኖሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሁኔታዉን የበለጠ አስቸጋሪ አድርጎታል ይላሉ።

Dr. Merera Gudina Addis Abeba Äthiopien Oromo Pressekonferenz PK
ምስል DW/Y.Egziabhare
Äthiopien Oromo Federalist Congress
ምስል DW/Y.G. Egziabhare

በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ከታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ወዲህ በዉልቂጤ፣በጎንደር፣በባህርዳር ከትናንትናዉ ዕለት  ጀምሮ ደግሞ በነቀምትና በደሚቢዶሎ ከተሞች ተቃዉሞዎች ተካሂደዋል።ይህንን በተመለከተም  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቋቋመዉ የኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት በዛሬዉ እለት መግለጫ አዉጥቷል። በኦሮሚያ ክልል በተለይም በነቀምትና በደምቢዶሎ አካባቢወች በእነዚህ ሁለትና ሶስት ቀናት፤ ፅሕፈት ቤቱ፤ «ህገ ወጥ አካላት» ያላቸዉ ወገኖች  የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት እያወኩ መሆናቸዉን  አመልክቶ  እነዚህ አካላት ከድርጊታቸዉ የማይቆጠቡ ከሆነ  የፀጥታ ሀይሎች አስፈላጊዉን እርምጃ እንዲወስዱ መታዘዛቸዉን ፅ/ቤቱ  ገልጿል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ