1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁለትም አንድም ናቸዉ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2007

ሁለቱ፤ በአንዱ-ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ አንድ የሆኑበት ሰበብ ምክንያት አንድም አጋጣሚ-አለያም «ትንኝም ለሆዷ፤ ዝሆንም ለሆዱ ----» እንዳለዉ ኢትዮጵያዊዉ ባለቅኔ ካልሆነ በስተጠቀር ብዙም ትንታኔ የለዉም።

https://p.dw.com/p/1E5E3
ምስል picture-alliance/epa/C. Poppe

ዕድሜ-የአባት እና የልጅ ያክል የሚያራርቃቸዉ የሁለት ዘመን ዉልዶች ናቸዉ።ተፈጥሮ በወንድና ሴትነት የሚያቃርናቸዉ፤ ሐይማኖት በሒንዱ-እና እስልምና አማኝነት የሚያራርቃቸዉ፤ የተጎራባች-ግን የጠላቶች ሐገር ግኝቶች።ካይላሽ ሳትያርቲ እና ማላላ ዩስፍዛይ።የሕጻናት የልጆች መጨቆን አቀራረባቸዉ፤ አንድ አደረጋቸዉ፤ ኖቤል አጋራቸዉም።

«አንዲት ወጣት ልጃገረድ እና ብዙም ያላረጁ ሰዉዬ፤አንዷ ከፓኪስታን፤ ሌላዉ ከሕንድ፤ አንዷ ሙስሊም ሌላዉ ሒንዱ፤ ሁለቱም እንደ አንድ፤ ዓለም የሚያስፈልገዉን አንድ ነገር አሳዩ።አንድነትን።አልፍሬድ ኖቤል የተናገሩለትን፤ በሐገራት መካከል ሊኖር የሚገባዉን ዉዴታን---»

የኖርዌ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር ቶርብዮርን ያግላንድ።ሁለትም አንድም ሆኑ።አላማ፤ ትግል፤ ጥረት ስኬታቸዉ የዛሬ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ ።

«ድንበሮች በሙሉ የማይገድቡት፤ ሐይማኖት፤ባሕልና ማሕበራዊ እምነት የማይገታዉ አስተሳሰብ አለ።ልጆች የልጅነት መብታቸዉ መከበር አለበት፤ልጆች መማር እንጂ ተገድደዉ መሥራት የለባቸዉም፤ ኑሯቸዉን በባርነት መጀመር የለባቸዉም የሚል አንድ የዓለም አስተሳሰብ አለ።ይሕ ሁለንተናዊ አስተሳሰብ ከካይላሽ ሳትያርቲ እና ከማላላ ዩስፍዛይ ምግባር ሌላ የተሻለ መገለጫ የለዉም።»

ሁለቱ፤ በአንዱ-ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ አንድ የሆኑበት ሰበብ ምክንያት አንድም አጋጣሚ-አለያም «ትንኝም ለሆዷ፤ ዝሆንም ለሆዱ ----» እንዳለዉ ኢትዮጵያዊዉ ባለቅኔ ካልሆነ በስተጠቀር ብዙም ትንታኔ የለዉም።

Friedensnobelpreis Verleihung Rede Malala 10.12.2014 Oslo
ምስል Reuters/S. Plunkett

እሳቸዉ-ቅምጥል ሐብታሞችን፤ ከጎስቋላ ቧጋቾች ጋር አዛንቃ በማኖር በዓለም የተመሠከረላት ሐገር ዉጤት ናቸዉ።የሕንድ።ካይላሽ ሳይትራቲ።የትዉልድ ግዛታቸዉ ስም-የግዛቲቱን መልከዓ-ምድራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ማሕበራዊ አቋም ገለጭ ነዉ።ማድያ ፕራዴሽ «በሕንዲኛ ማዕከላዊ ግዛት» እንደማለት ነዉ።ቅፅል ሥሟ ደግሞ-የበለጠ ይገልጣታል።የሕንድ-ልብ።

በ1954 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከሕንድ ልብ ግዛት ተወደ።እዚያዉ ግዛት ሲያድግ የሒንዱዎቹ «ሳንታና ዳርማ»-ምድርን «ገነት-ያደረገላቸዉን-ጥቂቶች ወይም ገሐነብ ያደረገበትን አብዛሐ ሕንዳዊ ተቃራኒ ኑሮን አለመያት በርግጥ አይችሉም ነበር።

አስተናዳደግ፤ ትምሕርት አዉቀት ችሎታቸዉ ከሐብት ማማ የሚያደላድለዉን መሠላል በቀላሉ ለመንጠላጠል አመቺ ነበር።ጎበዙ ተማሪ በኤልክትሪክ ምሕንድስና የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዉን ለመያዝ ያነቀፈዉ አልነበረም።የዩኒቨርስቲ ዉጤቱ ከሕንድ «ልቢቱ» ትልቅ ከተማ ባሆፖል በሚገኘዉ ለዩኒቨርስቲ መምሕርነት (ፕሮፌሰርነት) አበቃዉ።

ከእንግዲሕ አንቱ ናቸዉ።በሙያቸዉ ጥቂት ቢገፉበት ሚሊዮንን-መቁጠሩ፤ ሚሊዮኖችን መቅጠሩ ምናልባትም እንደ ብዙ ጌቶች ሺዎ ዶሆችን እየመዘበሩ መንደላቀቁ ባልገደዳቸዉ ነበር።ግን አላ ደረጉትም።እያዩ ያደጉትን የሕዝቦች የተዛነቀ-ኑሮን በበሰለ እድሜ-አዕምሮ ማስተዋል-ማስተንተን ሲጀምሮ አዕምሯቸዉ ሸፈተ።

ሻርማ-የሚለዉን ሁለተኛ ስማቸዉን ሳትያርቲ ወደ ሚለዉ የለወጡበትን ምክንያት ብዙም አይናገሩም።ሕሊናቸዉን ያሸፈተዉን ጥያቄ ለማስተናገድ ግን ሙያ፤ ጥሩ ገቢ፤ የቱጃርነት ተስፋን አርግፍ አድረገዉ የተዉበት ምክንያት ግን ግልፅ ነዉ።ክፉ-ደጉን ያለዩ ልጆች መከራን መታገል።

«የልጆቻችን ሕልም ከመንፈግ የበለጠ በደል የለም።ሥለዚሕ ምኩራቦች፤ መሳጂዶች፤ አብያተ-ክርስቲያናት እና ቤተ-እምነቶች በሙሉ ለልጆቻችን ሕልም ሥፍራ ማጣታቸዉን አልቀበልም።የአንድ ሳምንት ወታደራዊ ወጪ ብቻዉን በመላዉ ዓለም የሚገኙ ልጆችን ትምሕርት ቤት ማስገባት እየቻለ ዓለም ደሐ ናት መባሉን መቀበል እንቢኝ አልኩ።»

እንቢኝ አሉ እና በድሕነት የሚማቅቁ፤ ያለፍላጎት፤ እድሜ-አካላቸዉ ብቃት ለከባድ ሥራ የሚገደዱ ልጆችን ሕይወት ለመለወጥ ሊታገሉ ወሰኑ።1980 ያኔ ማላላ ዩስፍዛይ ልትወለድ ቀርቶ አልታሰበችም።

Friedensnobelpreis Verleihung Rede Satyarthi 10.12.2014 Oslo
ምስል Reuters/S. Plunkett

የሷ እና የሳትያርቲ ሐገራት ግን ሁለቱም በሌሉበት ዘመን የጀመሩትን ዉዝግብ፤ ጠብ፤ግጭት ጦርነት በከፋ ጦር መሳሪያ ለመቀጠል የኑክሌር ቦምብ ለመሥራት ይራወጡ ነበር።ያኔ፤ ዓለምን ለሁለት የተቀራመቱት ሐያላን እንደ አብዛኛዉ ዓለም ሁሉ የሁለቱ የጥንት አንዶች፤ የኋላ ተጎራባች ጠበኞች መንግሥታትን የኑክሌር ግንባታን በመደገፍ የእልቂት-ዝግጅታቸዉን ያጋግሙት ነበር።

ያኔ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንኳ የሕፃናት ወይም የልጆች ለመሥራት እንዳይገደዱ የሚደነግግ ግልፅ ደንብ አልነበረዉም።ሳትያርቲ በተለይ ለልጆች መብት መከበር፤ ያኔ ያልነበረዉ እንዲኖር ሁለት ድርጅቶችን መሥርተዉ ከዓላማ ተጋሪዎቻቸዉ ጋር አብረዉ የገጠሙት ትግል በሁለተኛ ዓመቱ ቢያንስ በሕግ ደረጃ ዓለም አቀፍ ዉጤት አሳየ።

የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ድርጅት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ለመስራት እንዳይገደዱ የሚደነግግዉን ደንብ ቁጥር 82 አፀደቀ።ሳትያርቲና ባልደረቦቻቸዉ ባደረጉት ትግልና ጥረት ከሰማንያ ሺሕ የሚበልጡ ልጆችን ከባርነት ባልተናነሰ ሥራ-ከተጠመዱበት ነፃ አዉጥተዋል።ትግሉ ከባድ ዋጋ-የጠየቀ፤ የሁለት ባልደረቦቻቸዉን ሕይወት ጭምር የተከፈለበት ነበር።

«ሰማንያ ሺሕ ያሕል ልጆችን ነጻ አዉጥተዋል።ልጆቹን ማስለቀቁ አንዳዴ እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ የተከናወነ ነበር።ሳትያርቲ ራሳቸዉ ብዙ ጊዜ ከባድ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል።እሳቸዉና ባልደረቦቻቸዉ ሕንድ ዉስጥ ከምድር በታች በሚገኙ ፋብሪካዎች ተገደዉ የሚሠሩ ልጆችን ለማስለቅቅ ሲሞክሩ የገጠማቸዉ ተቃዉሞ ከባድ ነበር።የልጆቹን ጉልበት በመበዝበዝ የከበሩ ወገኖች በቀላሉ እጅ አልሰጡም።»

GMF 2014 Thorbjørn Jagland
ምስል DW/K. Danetzki

ማላላ ዩስፍዛይ የተወለደችዉ ሳቲያርቲና ባልደረቦቻቸዉ ያደረጉት ትግል፤ ጥረት እና የከፈሉት መስዋዕትነት ለልጆች ደሕንነት የተሻለ መደላድል በፈጠረበት ዘመን ነበር።ሐምሌ 1997።የኮሚንስት ካፒታሊስቶች ፍጥጫ በቀዘቀዘበት፤የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በታወጀበት፤ኢንተርኔት፤ ተንቀሳቃሽ ስልክ ዓለምን በለወጡበት ዘመን ነበር።

በርካታ ትምሕር ቤቶችን ከሚያስተዳድር፤ከተማረና ከከበረ ቤተሰብ የተወለደችዉ ማላላ የቤተሰቦችዋ ሐብት፤ እዉቀት፤ የተለወጠችዉ ዓለም ዕድገትም፤ ኑሮ፤ እድገት ፍላጎትዋን የሚያስተናግዱ ዓይነት አልነበሩም።ዓለም በርግጥ ተለዉጣለች።ሚሊዮኞች ግን ዓለም ከመለወጥዋ በፊት ከነበረዉ በከፋ ሁኔታ ይሰቃዩ፤ ይራቡ፤ መልኩን በለወጠዉ ብዝብዛ ይማቅቃሉ።

ሚሊዮኖች በተለይም ሴት ልጆች የመማር-መመራመር ዓይደለም በልቶ የማደር መብት እንኳን የላቸዉም።የአዲሲቱ ዓለም ብቸኛ ገዢዎች ባንድ በኩል፤ አዲስ ጠላቶቻቸዉ ሆነዉ ብቅ ያሉት ሙስሊም ፅንፈኞች በሌላ በክል የገጠሙት ግጭት ጦርነት እንደ ብዙዎቹ የኢራቅ፤ የአፍቃኒስታን፤የፍልስጤም፤ ልጆች ሁሉ የፓኪስታናዊቷን ታዳጊ ወጣት ሕይወትንም ያናጋዉ ገባ።የፓኪስታን ታሊባኖች የስዋት ሸለቆ የተባለዉን የማላላን የትዉልድ ግዛት በተቆጣጠሩበት ወቅት አንዳድ ሥፍራ ሴት ልጆች እንዳይማሩ አግደዉ ነበር።የታሊባኖቹ እርምጃ አስፈርቷቸዉ ትምሕርት ያቋረጡ፤ ያል እድሜ ፍላጎታቸዉ የተዳሩ፤ እርምጃዉን በመቃወማቸዉ የተሰቃዩትን ሴቶች ስንትነት፤ የስቃያቸዉን መጠን በትክክል ያሳወቀ ወገን የለም።

በታሊባኖች ቦምብ፤ ታሊባኖች ላይ በዘመተዉ የፓኪስታን መንግሥት ጦር ጥይትና መድፍ፤ በአሜሪካኖች ድሮን የተገደሉትን ሰዎች፤ በየትምሕርት ቤቱ የተጨፈለቁትን ሕፃናት ሥንትነት ለማወቅ ዘመን እንደ ማላላ-እስኪያነሳቸዉ ድረስ መጠበቅ ግድ ይለናል።ታሊባኖች የስዋት ሸለቆን ሲቆጣጠሩ የጣሉት ገድብ ግን ለዚያች ታዳጊ ወጣት ለዛሬ ያደረሳትን ጎዳና ቀየሰላት።

ማላላ የሴት ልጆች የመማር መብት እንዲከበር የሚያሳስቡ መልዕክቶችን በአባቷ ድጋፍና እርዳታ እየፃፈች ቢቢሲን ለመሳሰሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ዘዴዎች መላክ ጀመረች።ካላየቻቸዉ፤ ከማታቃቸዉ ሳትያርቲ ጋርም በማታቀዉ መንገድ ላአንድ ዓለማ ከአንዱ ትግል ተቀየጠች።የልጆች በተለይም የሴት ልጆች የመማር መብት-ትግል።

«በ11 ዓመቷ ታሊባን በሚቆጣጠረዉ በሰሜን ምዕራብ ፓኪስታን ግዛት በስዋት ሸለቆ የነበረዉን ከባድ ኑሮ ለቢቢሲ አምደ መረብ መፃፍ ጀመረች።በፓኪስታን መንግሥት ባለሥልጣናት ትብብር ታሊባኖች የሚደርሱትን በደልና ጫና ተቋቁማ መታገል ያዘች።»በእሷ እድሜና ዕዉቀት መፃፉ የሚያጠራጥረዉ መልዕክት በዓለም ሲናኝ ከታሊባኖች ጆሮ መድረሱ አልቀረም።አፀፋዉም ቀላል አልነበረም።ጥቅምት ዘጠኝ 2012።ሰዉዬዉ ማላላና ባልደረቦችዋ ከተሳፈሩበት አዉቶብስ ገባ፤ ማላላ የትኛዋ እንደሆነች ጠየቀ።አወቃት።ሽጉጡን መዝዘ። ተኮሰ፤ደገመ፤አሰለሰ።ሰወስተኛዋ ጥይት በግራ-በኩል ግንባሯን በርቅሳ ገባች።ተዝለፍልፋ ወደቀች።አልሞተችም።ኢንግላንድ ብሪታንያ መጥታ ታከመች።ዳነችም።

«በሰወስት ጥይቶች ደበደባት።ክፉኛ አቆሰላትም።ግን ዳነች።ታሊባን ነብሷን ለማጥፋት ዳግም መሞከሩ እንደማይቀር ባይሸሽግም ልጃገረዶች የተምሕርት እድል እንዲያገኙ የምታደርገዉን ትግል እንደምትቀጥል አረጋገጠች።»

Medaille Alfred Nobel
ምስል picture-alliance/dpa/Kay Nietfeld

ቀጠለች።በኖቤል የሠላም ሽልማት ታሪክ የመጀመሪያ ወጣት ተሸላሚ ሆነችም።«ይሕ ሽልማት የኔ ብቻ አይደለም።የእኒያ ትምሕርት የሚፈልጉ ግን የተረሱ፤ የእኒያ ሠላም የሚሹ ግን የሚሸማቀቁ፤የእኒያ መብታቸዉ እንዲከበር የሚሹ ግን ድምፃቸዉ የማይሰማ ልጆች ጭምር እንጂ።እዚሕ የቆምኩት መብታቸዉ እንዲከበር፤ ድምፃቸዉ እንዲሰማ ነዉ።»

ሁለቱም ለሽልማት አዲስ አይደሉም።ካይላሽ ሳትያርቲ ከዚሕ በፊት አስራ-ሁለት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን፤ በርካታ እዉቅናዎችን አግኝተዋል።ማላላ ከሃያ በላይ ሽልማትና አዉቅና አግኝታለች።ባለፈዉ ሰምንት ግን እንደ ሥራ-ዓላማቸዉ ሁሉ ኖቤል የሠላም ሽልማትም ሁለትም-አንድም አደረጋቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ