1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁለት የባዕድ ቋንቋ ግራ ያጋባት ካሜሮን

ማክሰኞ፣ የካቲት 22 1997

በፈረንሳይና በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስር የነበችዉ ካሜሮን የሁለት ባዕድ ቋንቋ ብሄራዊ መግባቢያነት ለአወዛጋቢ ችግር ዳርጓታል። ከአገሪቱ ህዝብ ቁጥር አንፃር አነስተኛዉን እጅ የሚይዙት የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ዜጎች መብታችን ተገፎ ለብዙሃኑ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ካሜሮናዉያን በሚያደላዉ አሰራር የበይ ተመልካች ሆነናል ይላሉ።

https://p.dw.com/p/E0kF

የአገሪቱ መንግስት ችግሩ የለም ቢልም መፍትሄ ለመፍጠር ማዕከላዊ አሰራሩን እየለወጠ መሆኑን ይገልፃል።
በዘመነ ቅኝ አገዛዝ 80 በመቶ የሚሆነዉን የካሜሮን ግዛት የተቆጣጠረችዉ ፈረንሳይ ስትሆን ቀሪዉ 20 በመቶ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስር ነበር።
የእንግሊዝኛ ቋንቋ አፍ መፍቻቸዉ የሆነዉ 16.7 ሚሊዮን የሚሆኑት በደቡብ ምዕራብና በሰሜን ምዕራብ ክፍላተ ሃገራት የሚኖሩት ካሜሮናዉያን በአካባቢያቸዉ ቁጥራቸዉ ከፍተኛ ነዉ።
ከዛሬ 40 አመት በፊት የተቀረፀዉ የፌዴራል ህገመንግስት ግን የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹን መብት በሚያፍን መልኩ በፈረንሳይኛ ተናጋሪዎቹ ማዕከላዊ አሰራር ተገምዷል ባይናቸዉ በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ጆስሊን ኤኮ።
በያዉንዴ የሚገኝ መንግስታዊ ያልሆነ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሃላፊ የሆኑት ኦዲሊ ጋናንግም ከእ.ኤ.አ. 1972 ወዲህ ስልጣን ላይ የወጡ የካሜሮን መሪዎችም በዘዴ የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹን ማንነት አጥፍተዉታል ይላሉ።
በእሳቸዉ ገለፃ መሰረት ይህ አይነቱ አሰራር ነዉ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹን ካሜሮናዉያን ሁሉም አይነት መድሎ እንዲፈፀምባቸዉ በር የከፈተዉ።
የአገሪቱ የስራ ቋንቋዎች ሁለቱ ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ ሆነዉ ሳለ የሼክስፒር ቋንቋ በመገናኛ ብዙሃንም እንኳን ከሚገባዉ በታች ነዉ ግልጋሎት ላይ የዋለዉ ይላሉ ታዛቢዋ።
በያዉንዴ ከተማ አቅራቢያ በእንግሊዝኛ መምህርነት የሚያገለግሉት ሪቻርድ ማንዳዚም በበኩላቸዉ እንደሚሉት የፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ናቸዉ በአገሪቱ ቁልፍ ቁልፍ የመንግስት ስራዎች ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙት።
እንደ መምህሩ ገለፃ ይህ ዕድል የተሰጣቸዉ ፈረንሳይኛ የሚናገሩት ካሜሮናዉያን እንግሊዘኛ ተናጋሪዎቹን ካሜሮናዉያን አገር የለሽ አድርገዉ ይቆጥሯቸዋል።
በመሆኑም መፍትሄ የሚሉት የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ ካሜሮናዉያን ደቡብ ካሜሮናዉያን ተብለዉ መገንጠሉ ይበጃቸዋል።
የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ በዜግነታቸዉ ያልተጠቀሙበት ሌላዉ የቅሬታ ምንጭ ምጣኔ ሃብትን የተመለከተ ነዉ።
ከጊኒ ባህረ ሰላጤ የሚጎራበተዉ የፔንዚዊላ የፔትሮሊየም ክምችት የጥቅም ተካፋይ አልሆንም የሚለዉ ዋነኛ ጥያቄያቸዉ እንደሆነ በዱዋላ ዩኒቨርስቲ የፓለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት አቦያ ኤንዶንግ ማናሴ ይገልፃሉ።
ከሰላሳ አመታት በፊት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙት ነዳጅ ያለባቸዉ አካባቢዎች ለአንድ የፈረንሳይ ኩባንያ ሲሰጡ በፌደሬሽን የተዋሃዱት አካባቢዎችን በማማከር አልነበረም።
በመጀመሪያ በቅኝ ገዢዎቻቸዉ የሃይል ሚዛን አማካኝነት የወጣዉ መግለጫ አንዷን ካሜሮን የእንግሊዝና የፈረንሳይ ካሜሮን ብሎ ከፋፈለ።
የዛሬ 45አመት በፈረንሳይ ስር የነበረዉ ሰሜናዊ ካሜሮን ነፃ ወጣ። ከአንድ አመት በኋላ በሪፈረንደም በእንግሊዝ ስር የነበረዉ ደቡብ ካሜሮን በፈረንሳይ ስር ከነበረዉ ሰሜን ካሜሮን ጋር በመዋሃድ የካሜሮን ፌደራል ሪፐብሊክን ፈጠረ።
አገሪቱ በዚህ ሁኔታ መኖር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የጋራ መግባቢያ ከማድረግ ይልቅ በሁለት የባዕድ ቋንቋ መስራት የቀጠለችዉ ካሜሮን ዜጎቿን ያለቅሬታ በእኩል የሚያስተናግድ መፍትሄ አጥታለች።
የሊበራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር 40 አመታትን ላስቆጠረዉ የካሜሮን እንግሊዝኛ ተናጋሪ ዜጎች ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ ማዕከላዊ አሰራሩን በመለወጥ ስልጣን ወደ ተለያዩ ክፍለሃገራት እንዲወርድ ለማድረግ እንደሚጥሩ ነዉ ለጋዜጠኞች የገለፁት።
ቦኒፌስ ፎርቢን ይህ ዘዴ የባህል ዉህደትን፤ ነፃነትንና እኩልነትን ለካሜሮናዉያን ሁሉ የማስፈን እድልን ያመጣል ብለዉ ተስፋ ያደርጋሉ።
የካሜሮን መንግስት ግን የእንግሊኛ ተናጋሪዎች ችግር የሚባል ነገር በአገሩ እንደሌለ ነዉ ያስተባበለዉ።
የአገር አስተዳደርና ሚኒስቴር ባለስልጣን የሆኑት ፒየር ኢሶምባ እንደሚሉት በአገሪቱ የሚገኙ 250 ጎሳዎች ሁሉ የየራሳቸዉ ችግር አላቸዉ።
ያንንም በህገመንግስቱ መሰረት ማዕከላዊ አሰራርን በማፍረስ መንግስት ለመፍታት እየጣረ ነዉ። ይህ አሰራርም ለ10 የአገሪቱ ክልሎች የራስ ገዝ አስተዳደር ስልጣን ይሰጣቸዋል።
በአሁኑ ወቅት የካሜሮን መንግስት ከ60 በላይ ከሚሆኑት የካቢኔ አባላት መካከል እንግሊዝኛ ከሚናገሩት ወገን የወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤፍሬም አይኖንን ጨምሮ ሰባት ሚኒስትሮች አሉት።
አይኖን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመረጡት ባለፈዉ ታህሳስ ወር ላይ ሲሆን ሁለት ምክትሎቻቸዉን ጨምሮ ሶስቱ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ባለስልጣናት የተመረጡት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆኑት ፕሬዝዳን ፓዉል ቢያ ነዉ።