1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሃይማኖት፣ ድህነት እና ሙስና

ዓርብ፣ መጋቢት 13 2011

አፍሪቃ ውስጥ በርካታ የክርስትና እና እስልምና ተከታዮች ይገኛሉ። ጸሎት አይለያቸውም፣ ሃይማኖታቸውንም አክብረው ይይዛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በዚች አህጉር ላይ ሙስና እጅጉን ተስፋፍቷል። ሃይማኖት፣ ድህነት እና ሙስና የሚያገናኛቸው ነገር አለ? የኢትዮጵያ ወጣቶችስ ምን ይላሉ?

https://p.dw.com/p/3FTaZ
Symbolbild Wirtschaftskriminalität
ምስል Imago/blickwinkel

ሃይማኖት፣ ድህነት እና ሙስና

ለምንድን ነው በጣም ሃይማኖተኛ የሚባሉት ሃገራት በጣም ደሀ እና ከዓለም በሙስና ቀዳሚ የሆኑት? ሌላው ጥያቄያችን ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 ይፋ የኾነው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የፀረ ሙስና መዘርዝር እንደሚያመላክተው  ከሰሃራ  በታች ያሉ የአፍሪቃ ሃገራት ሙሰኛ የሚባሉ እና በጣም ዝቅተኛ ውጤት ያገኙት ናቸው። ተቋሙ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የ180 ሃገራት ሙስናን የሚያመላክት የዳሰሳ ጥናቶች እና  ግምገማዎች አካሂዷል። በዚህም መዘርዝር ኢትዮጵያ ከ180 ሃገራቱ 114ኛ ደረጃ ላይ ናት። ይህ ማለት በጥናቱ የተካተቱት 66 ሃገራት ከኢትዮጵያ የበለጠ ሙስና ተስፋፍቶባቸዋል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ጭራሽ 144ኛ ስፍራ ላይ ትገኛለች። ከሀገሪቱ 98 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ግን ሃይማኖተኛ ነው። ቦትሱዋና በአንፃሩ በመዘርዝሩ ከ180ዎቹ ሃገራት 34ኛ ስፍራ ላይ ስትገኝ፤ ግማሽ ያህሉ ባህላዊ አምልኮ ነው ያለው። ለመሆኑ ሃይማኖት፣ ድህነት እና ሙስና የሚያገናኛቸው ነገር አለ? ሙስሊም እና ክርስትያን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሚያገናኛቸው ነገር ሊኖር እንደሚችል ቢሆንም ግን ሃይማኖታቸው ሙስናን እንደማይፈቅድ ነው የሚናገሩት።

Infografik Corruption Perceptioin Index 2018 EN

ታድያ ለምንድን ነው እነዚህ ሃይማኖታቸውን የሚያከብሩ እና የሚያምኑ ማህበረሰባት ዘንድ ድህነት እና ሙስና የተስፋፋው? ምንም ቢሆን ትላልቅ የሚባሉት የእስልምና እና ክርስትና እምነቶች የሚሰብኩት በጎ ማሰብና ማድረግን ነው። ዩጋንዳ በሙስና ከ 180 ሀገራት 149ኛ ስፍራ ላይ ትገኛለች።  የዩጋንዳ ወጣቶች «ሰዎች በተዓምራዊ መድህን አጥብቀው ያምናሉ ። ስራቸውን ትተው ቤተክርስትያን ናቸው።  ቤተክርስትያን ሆነው ተዓምር እስኪፈጠር ይጠብቃሉ። ይህ ደግሞ ወደ ስንፍና ነው የሚያመራው።» « ሐይማኖት ሙስናን በመታገል ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ምክንያቱም ሙስና ማህበረሰባችንን እየጎዳ ያለ ነገር ነው። የምናምነው እና የምንከተለውም በየሐይማኖታችን በተሰበክነው ነገር ላይ ነው» ይላሉ።

የሐይማኖት ቡድኖቹ ሙስናን ቢቃወሙም የመቆጣጠር ወይም የማስቆም ኃላፊነት እንደሌላቸው ነው የዩጋንዳ ሙስሊም ማህበረሰብ ሓዲ ሴሬኮ ሙቱምባ የሚያስረዱት።

« እኛ የሐይማኖት መሪዎች ሙስናን እናወግዛለን። ሙስና ክፉ ነው። መቆም አለበት።  እኛ የሐይማኖት መሪዎች ይህንን በመቃወም ነው የምንሰብከው። ከዛ ባለፈ ምንም ማድረግ አንችልም። ሌላ መሣሪያ የለንም። ስልጣኑም የለንም።»

Äthiopien Addis Abeba | Opferfest Eid al Adha
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ቄስ ፔተር ባካም የሚሰብኩትም ፀረ ሙስናን ነው። « ሙስናን መዋጋት ከፈለግን ወጣቱ ላይ ማተኮር ይኖርብናል። እንደ ሒሳብ ፣ የመልከዓ ምድር  ትምህርት ሁሉ ይህንንም ማስተማር ያስፈልጋል። በጎ መስራት በራሱ ሽልማት እንደሆነ እና መልሶ እንደሚከፍል ማስተማር ያስፈልጋል።»

የማህበራዊ ባለሙያዎችስ በዚህ ላይ ምን ይላሉ? ማርቲን ሴምፓ በተሞክሮዋቸው ላይ ተመርኩዘው ይናገራሉ።« ብዙዎቻችን የሚሲዮን ትምህርት ቤት ነው የተማርነው። መሪዎችን የሚያሰለጥኑት ትምህርት ቤቶች በሚሲዮናውያን ነው የተገነቡት ናይጄሪያ ጋና ዮጋንዳ ኬንያ። አሁን ግን ትምህርት ቤቶች የግል መሆን ሲጀምሩ የህይወታችን መሰረት የሆነው ዕምነታችን ርቆናል። አሁን አሁን ትምህርት ቤት ቢዝነስ  ሆኗል።»

ማርቲን ሴምፓ ድህነት ወይም በቂ ክፍያ አለማግኘት ሰውን ወደ ሙስና ሊያመራ እንደሚችል ያብራራሉ። « የአማካይ የሰዎች ደሞዝን ስንመለከት ከፍተኛ የክፍያ ልዩነት እንዳለ እናስተውላለን። ብዙ ይሰራሉ የሚያገኙት ክፍያ ግን ዝቅተኛ ነው። ሰዎች ይበልጥ ሲጨቆኑ  ሌላ አማራጭ  መንገድ መፍጠር እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል።»

 

ሐይማኖት ብቻውን ለሙስና መፍትሄ መሆን እንደማይችል ቀድመው የተናገሩት የሐይማኖት አባቶች እና የማህበረሰብ ባለሙያው ተናግረዋል። ወጣቶችስ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ። « ሐይማኖት ይህንን ባህል የማስቆም አቅም አለው። ሰዎች በእምነታቸው ላይ ካተኮሩ የመቀየር ኃይል ዓለው። »

Äthiopien Orthodoxes Weihnachtsfest in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/abaca/M. W. Hailu

« በሙስና የተዘፈቀው ሰው ራሱ ነው ነገ ቤተ ክርስትያን የሚሄደው ። ስለዚህ አፍሪቃ ውስጥ ማንኛውም ሰው ሙስና ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ይህ አንዱ ምሳሌ ነው።»

ሙስና ከተስፋፋበት ሀገር ዝምባዌ የመጣችው ጆሴፌኒ በዚህ ጉዳይ ላይ ከ DW ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጋለች።  ሐይማኖት ሙስና እና ድህነትን  እንደ ሶስት ማዕዘን ነው የማያቸው ትላለች። « ሶስት ማዕዘኑ ላይ ድህነት ከላይ ይቀመጣል ። ሙስና በስተ ግራ ሐይማኖት ደግሞ በስተ ቀኝ። አፍሪቃ ውስጥ ድህነት ሰውን ወደ እምነት ይመራል። ሐይማኖት የድህነት መደበቂያ መሆን ጀምሯል። አፍሪቃ ውስጥ ሰዎች ለህክምና የሚከፍሉት ይቸገራሉ። ለመድሀኚት የሚከፍሉት የላቸውም። ያኔ ተዓምራዊ መድህን እናገኛለን በሚል ተስፋ  ወደ እምነት ይገባሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ፈዋሽ የሚባሉ የሃይማኖት ሰዎች አሉ ። አንዳንዶቹ ቄሶች ደግሞ ሙሰኞች ናቸው። ስራ ሲያጡ ነገ ተነስተው ሰባኪ ነኝ ይላሉ።»

 

የውሸት ፈዋሾች  ግራ የተጋቡ እና የተቸገሩ ሰዎችን እያታለሉ ትርፋማ ለመሆን ሲሞክሩ በየተደጋጋሚ በየሀገሩ በሚሰራጩ ቪዲዮዎች ይታያሉ። « የደቡብ አፍሪቃውን ቪዲዮ ስንመለከት ሁሉም ነገር ድራማ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በሺዎች የሚቆጠሩ በደስታ ሲጮሁ ይታያል። እነዚህ ሰዎች ጤነኛ ናቸው ያስብላል። ደግሞ የተለያዩ ዜግነት ያላቸው፤ ቻይናውያን፣ ነጮች ታዳሚ ሆነው ይታያሉ። እነዚህ ቼሶች ምን ያህል ከአለም ህዝብ ትርፋማ እንደሆኑ ያሳያል።»

በአንድ በኩል በውሸት ቄስ ነኝ እያሉ የሚያታልሉ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ በሀይማኖት የተደራጁ ሰዎች ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል የመሳሰሉትን ይገነባሉ። እነዚህን በጎ አድራጊዎችንስ በምን ዓይን መመልከት ይኖርብናል።? « እነሱ የቆዩት የካቶሊክ ፣ የወንጌላውያን እምነቶች ናቸው። ከዚህ ሌላ ግን ከሰዎች የሚነጥቁ እንጂ የሚሰጡ እየታጡ ነው። በጣም የሚያሳዝነው እኛ አፍሪቃውያን እነዚህ ሰዎች ይህን ሲሰሩ መቀበላችን ነው።»

ሌላው ተጠያቂ ደግሞ የነዚህ ሀገራት መንግታት ናቸው ትላለች ጆሰፊነ« ሰዎች ሲጠቀሙባቸው እያዩ ምንም አይነት ርምጃ አይወስዱም ። ምክንያቱም እነሱ በህዝባቸው ላይ እየተጠቀሙ ስለሆኑ ነው። ይህን ስል ግን አንድ እጅግ የማመሰግናቸው ፕሬዚዳንት አሉ። የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ። በስነ መለኮት ትምህርት ያልተመረቀ ሰው  ቤተ ክርስትያን እንዲሰብክ አይፈቀድም። ቁጥጥር አለ። ሌሎች የአፍሪቃ መሪዎችም እንደዚህ ቢያደርጉ ምንኛ ጥሩ ነበር።»ትላለች ጆሴፌኒ።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ