1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህገ ወጥ ስደት ጀርመን እና አፍሪቃ

ማክሰኞ፣ የካቲት 5 2011

እስካሁን በመሰጠት ላይ ካሉት እገዛዎች መካከል ለድንበር ጥበቃ የሚውሉ ቁሳቁሶች እርዳታ፣የፖሊሶች ስልጠና እና ባዮሜትሪክ ለሚባለው መታወቂያ ሥራ የሚሰጠው ድጋፍ ይገኙበታል። ይህ ግን የታለመለትን ዓላማ ከግብ የሚያደርስ አይደለም ሲሉ ፖለቲከኞች ይከራከራሉ። ይልቁንም ህዝቡ እንዳይሰደድ የሚያደርጉ ሌሎች ተግባራት ላይ ነው መተኮር ያለበት ይላሉ።

https://p.dw.com/p/3DEgr
Kamerun Polizisten in Buea
ምስል Getty Images/AFP/M. Longari

ሕገ ወጥ ስደት ጀርመንና አፍሪቃ

የጀርመን መንግሥት ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ ለመከላከል የስደተኞች መነሻና መተላለፊያ ለሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት ባለፉት ሁለት ዓመታት በብዙ ሚሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ አድርጓል። ጨቋኝ የሚባሉ መንግሥታትንም የሚያካትተው ይህ እርዳታ ጀርመን ውስጥ ከሚያወዛግቡ አከራካሪ ጉዳዮች አንዱ ነው። የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ጀርመን «ህገ ወጥ» የሚባለውን ስደት ለመከላከል ለአፍሪቃ ሀገራት የድንበር ቁጥጥር የምታደርገውን ድጋፍ እና ትችቶችን ይመለከታል።
ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ህገ ወጥ የሚባለውን ስደት ለመከላከል ለአፍሪቃ መንግሥታት ድጋፍ ከሚሰጡ የአውሮጳ ሀገራት አንዷ ጀርመን ናት። የጀርመን መንግሥት በቀጥታም ይሁን በአውሮጳ ህብረት በኩል በተለይ በአፍሪቃ ለተሻለ የድንበር ቁጥጥር የሚውል ድጋፍ መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል። በዚሁ ወቅት ማለትም ከጎርጎሮሳዊው 2016 እስከ 2018 የጀርመን ፌደራል መንግሥት ለዚሁ ዓላማ 15 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ አድርጓል። የድጋፉ ትኩረትም ህገ ወጥ ስደትን እና ከዚሁ ጋር የሚያያዙትን ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ የማዘዋወር ወንጀልን እንዲሁም በዓለም አቀፍ አቭየሽን ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን መከላከል  መሆኑን የፌደራል ጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር እና ልማት ከዚህ ቀደም በጀርመን ፓርላማ ከግራዎቹ ፓርቲ ቡድን በኩል ለቀረበ ጥያቄ በሰጠው መልስ አስታውቋል። እስካሁን በመሰጠት ላይ ካሉት እገዛዎች መካከል ለድንበር ጥበቃ የሚውሉ ቁሳቁሶች እርዳታ፣የፖሊሶች ስልጠና እና ባዮሜትሪክ ለሚባለው መታወቂያ ሥራ የሚሰጠው ድጋፍ ይገኙበታል። ይህ ግን የታለመለትን ዓላማ ከግብ የሚያደርስ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩ የጀርመን ፖለቲከኞች አሉ። ከመካከላቸው በጀርመን ምክር ቤት የግራዎቹ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ኡላ የልፕከ አንዷ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት የጀርመን መንግሥት ችግሩን ይከላከላል ብሎ በተለይ የስደት መነሻ እና መተላለፊያ በሆኑ ሀገራት ከሚሰጠው ድጋፍ ይልቅ ህዝቡ ሀገሩን ለቆ እንዳይሄድ ሊያደርጉ የሚችሉ ሌሎች ተግባራት ላይ ነው መተኮር ያለበት።
«የድንበር ቁጥጥርን ማጥበቅ ሰዎች ከሀገራቸው ጭርሱኑ እንዳይሰደዱ አያግድም።ይልቁንም ሰዎች በሀገራቸው ዴሞክራሲ ካለ ሥራም ማግኘት ከቻሉ ሀገራቸውን ጥለው አይሄዱም። እናም የጀርመን ፌደራል መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ያሳስቡኛል።»
የጀርመን መንግሥት በቁሳቁስ ከሚደግፋቸው መካከል ግብጽ አንዷ ናት። ለድንበር ቁጥጥር የሚያገለግል ባትሪ ከድጋፎቹ ውስጥ የሚጠቀስ ነው። ለካሜሩን ፖሊሶች የሚሰጠው ሥልጠና እንዲሁም የናይጀሪያ መንግሥት መታወቂያዎችን ባዮሜትሪክ እንዲያደርግ የተሰጠው የገንዘብ ድጋፍ የድንበር ቁጥጥርን ለማጠናከር ታስበው ከተሰጡት ድጋፎች ውስጥ ይገኙበታል። እነዚህ እገዛዎችም ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመሩ ነው የሄዱት። እገዛው ሲጀመር በጎርጎሮሳዊው 2016 በአፍሪቃ ለሚካሄዱ መሰል ፕሮጀክቶች ወጪ የተደረገው 1.2ሚሊዮን ዩሮ ነበር። ባለፈው ዓመት ደግሞ ወደ 5.7 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ብሏል። ይህም የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነው። እነዚህን ለመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ይህን ያህል ገንዘብ መውጣቱም ማነጋገሩ አልቀረም። ጁዲት ፎራዝ በጀርመኑ የፖለቲካ ጉዳዮች ጥናት ተቋም የስደት ጉዳዮች ምሁር ናቸው። ፎራዝ ለነዚህ መሰል ፕሮጀክት የሚመደበው ገንዘብ መጠን ከፍ ማለት የጀመረው ስደተኞች በብዛት ወደ አውሮጳ ከገቡበት ከ 2015 በኋላ መሆኑን ያስታውሳሉ። ስደተኞች በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ ለመግባት የመረጡት መንገድ እጅግ አደገኛ በመሆኑ የበርካታ ወጣት ስደተኞች ህይወት ጠፍቷል። አሁንም ባልቆመው በዚህን መሰሉ አስከፊ ስደት የሚደርሰው ሞት የአካል ጉዳት እና እንግልት ቀጥሏል። ተሳክቶላቸው እንደ እድል ተርፈው አውሮጳ መድረስ ከቻሉት መካከልም ያለሙትን ህይወት ሳያገኙ ለተለያዩ ስነ ልቦናዊ ችግሮች የተዳረጉ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። እናም የስደት ጉዳዮች ምሁሯ ፎራዝ እነዚህን ከመሳሰሉ ሁኔታዎች በመነሳት ህገ ወጥ የሚባለውን ስደት ለመከላከል እርምጃዎች መወሰዳቸው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
«በአንዳንድ ምክንያቶች ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ያለ ምንም ተስፋ እንዳይሰደዱ መከላከል ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በአብዛኛው አውሮጳ የመግባት እድላቸው ዝቅተኛ ሆኖ ፣በአደገኛ ጉዞ  ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ብዙ ገንዘብም አጥፍተው ነው የሚሰደዱት።»
በሚሊዮኖች ዩሮ የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ የሚካሄዱት በጀርመኑ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት በእንግሊዘኛ ምህጻሩ GIZ አማካይነት ነው። ቴክኒካዊ ድጋፎችን በተመለከተ ብዙውን ጊዜ ሃላፊነቱ የሚሰጠው ደግሞ ለጀርመን ፌደራል ፖሊስ ነው። ይህን መሰሉን ድጋፍ ከሚያገኙት ሀገራት መካከል የዴሞክራሲ ተምሳሌት አይደሉም የተባሉ መኖራቸው ማነጋገሩ አልቀረም። በዚህ ጉዳይ ስማቸው ከሚነሳው ሀገራት አንዷ ግብጽ ናት። ጨቋኝ በሚባሉት በፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የምትመራው ግብጽ ጀርመን በአፍሪቃ የግል ውረታን ለማበረታት ይረዳል በሚል ዓላማ ከአንድ ዓመት በፊት በጀመረችው ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ በተባለው መርሃ ግብር ከተካተቱት 12 አገራት አንዷ ናት። በዚህ መርሃ ግብር ውስጥ ቤኒን ፣ ቡርኪናፋሶ፣ኮት ዲቯር ኢትዮጲያ ጋና ጊኒ፣ሞሮኮ ሩዋንዳ ሴኔጋል ቶጎ እና ቱኒዝያም ታቅፈዋል። ግብጽ ከጀርመን ባትሪዎችን ብቻ ሳይሆን የአቅጣጫ መጠቆሚያ መሣሪያ ቴክኖሎጂ እና ለፀጥታ ፍተሻ የሚውሉ መሣሪያዎች እርዳታ ታገኛለች። በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በመብት ጥሰት ለምትወቀሰው በኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ላልተካተተችው ለቻድም እንዲሁ ጀርመን ድጋፍ ትሰጣለች። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ሥልጣን ከያዙ 30 ዓመታት ተቆጥረዋል። ዴቢ የሰላ ትችት የሚያቀርቡባቸውን ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ያዋክባሉ። ሆኖም የሀገራቸው ፖሊስ ከጀርመን የድንበር ቁጥጥር ስልጠና ያገኛል። በካሜሩንም የፖለቲካ ሁኔታው እንዲሁ አሳሳቢ ነው። ካሜሩንን ከ35 ዓመታት በላይ በመሩት በፕሬዝዳንቱ በፖል ቢያ ላይ ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎች ይካሄዳሉ። ቢያ ጫናውን ከቁብም የቆጠሩት አይመስልም። የካሜሩን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ከጥቂት ቀናት በፊት ታስረዋል። ከጎርጎሮሳዊው 2017 አንስቶ ማዕከላዊው መንግሥት ረስቶናል የሚሉ እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች በሚኖሩበት የሀገሪቱ ክፍል በተቃዋሚ ሰልፈኞች እና በፖሊስ መካከል ደም የሚያፋስሱ ግጭቶች ደርሰዋል። እናም ይሄ ሁሉ ሲታይ ድጋፍ የሚሰጣቸው ሀገራት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ከግምት ውስጥ አይገባም ወይ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። የግራ መስመር ፖለቲካ የሚያራምደው የጀርመኑ የግራዎቹ ፓርቲ ፖለቲከኛ ኡላ የልፕከ በነዚህን መሰል ፕሮጀክቶች የጀርመን መንግሥት የሀገራቱን የሰብዓዊ መብት ይዞታ መፈተሹን እጠራጠራለሁ ይላሉ።
«የፖሊስ ድንበር ጥበቃን የተመለከቱት ሁሉም ፕሮጀክቶች የሁለትዮሽ ስምምነቶች አሠራር እና የቴክኖሎጂ አያያዝ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ሆኖም በሥልጠናዎቹ ሂደት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ምንም ዓይነት ሚና የሚጫወት አይመስልም። የጀርመን ፌደራል መንግሥት እንደ አውሮጳ ህብረት ወይም እንደ ተባበሩት መንግሥታት ፕሮጀክቶች የሰብዓዊ መብት መስፈርቶችን ማካተቱ ያጠራጥረኛል።» 
ጀርመን ከዚህ በተጨማሪም በአውሮጳ ህብረት አማካይነት የሚካሄዱ የድንበር መቆጣጠሪያ መርሃ ግብሮችንም ትደግፋለች።  የአውሮጳ ህብረት ከምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት የሚመጡ ህገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ለማስቆም የቀረጸው የአንድ ሚሊዮን ዩሮ መርሃ ግብር ትችት ከሚቀርብባቸው መካከል አንዱ ነው። በተለይ አምባገነን የሚባሉት የሱዳን እና የኤርትራ መንግሥታት የዚህ መርሃ ግብር የትብብር አካል መሆናቸው ይተቻል። በነዚህ ሀገራት የሚካሄዱ መርሀ ግብሮችን የሚያስተባብረው የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት GIZ ነው። እነዚህን በመሳሰሉ የተለያዩ መንገዶች ለድንበር ቁጥጥር የሚሰጠው ድጋፍ መጠናከር ከአፍሪቃ በህገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ ለመሰደድ ይሞክራሉ የሚባሉ ስደተኞችን ቁጥር በመቀነስ በኩል አዎንታዊ ለውጦች ሊያመጣ ይችላል የሚል እምነት አለ ። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ጥረት አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል የስደት ጉዳዮች ምሁርዋ ጁዲዝ ፎራዝ ያስረዳሉ።
«በአውሮጳ ህብረት ፕሮጀክቶች አማካይነት ባዮሜትሪክ የሚባለው ፓስፖርት ስራ ላይ ከዋለ እና የተሻለ ቁጥጥር ማድረግ ከተጀመረ በኋላ፣የምዕራብ አፍሪቃ አውሮፕላን ማረፊያዎች ህገ ወጥ ለሚባሉት ስደተኞች አስቸጋሪ ሆነውባቸዋል። ለዚህም ነው የናይጀሪያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ብዙዎቹ በየብስ የሚሰደዱት። እናም እነዚህ ለሀገራቱ በተሰጠ ድጋፍ የሚወሰዱ እርምጃዎች በጎ ለውጦች አምጥተዋል። ሆኖም ቀደም ሲል በዐዕምሮአችን ያልመጡልን ሌሎች ተጽእኖዎችንም እያስከተለሉ ነው። »
የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2018 በሜዴትራንያን ባህር በኩል ከ139 ሺህ በላይ ስደተኞች አውሮጳ ገብተዋል። በ2015 በዚህ መስመር የተሰደዱት ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነበር። 

Ulla Jelpke
ምስል Deutscher Bundestag / Lichtblick/Achim Melde
Afrikanischer Reisepass
ምስል picture-alliance/Godong
Symbolbild | Flüchtlinge im Mittelmeer
ምስል picture-alliance/dpa/AP/S. Palacios


ዳንኤል ፔልዝ/ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ