1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለማርስ ጉዞ የልምምድ ፍጻሜ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 29 2004

ከምድራችን ፣ አንዳንዴ ቀረብ ፤ አንዳንዴም ይበልጥ ፈንጠር ብላ ትገኛለች። ማርስ! እርሷ ቀረብ ስትል፣ ምድርም እንዲሁ ጠጋ ስትል፤ 54,6 ሚሊዮን ኪሎሜትር ብቻ ነው የሚያለያያቸው።

https://p.dw.com/p/RvgJ
ማርስምስል AP

ይህ የሚሆነው፤ ምድራችን ከፀሐይ ፈንጠር ብላ ፣ ማርስም ወደ ፀሐይ ይበልጥ ጠጋ ብላ ምኅዋሯ ላይ ስትገኝ ነው ማለት ነው። እ ጎ አ በ2003 ዓ ም እንደተረጋገጠው መሬትና ማርስ የተራራቁት በ 56 ኪሎሜትር ነበረ። ከዚህ አንጻር ደግሞ በምኅዋር ከሚራራቁባቸው ምኅዋሮች ላይ ሲደርሱ፣ 401 ሚሊዮን ኪሎሜትር አፈንግጠው ሊገኙ ይችላሉ። በአማካይ ግን በሁለቱ መካከል የ 225 ሚሊዮን ኪሎሜትር ርቀት መኖሩ እሙን ነው።

ከፀሐይ ፣ በርቀት፤ 4ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ማርስ፤ (ከሜርኩሪ፤ ቬኑስና መሬት ቀጥላ መሆኑ ነው)ከምድራችን ጋር የምትመሳሰልባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ። የማርስ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 25 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ከፍ ይላል። ማርስ፤ እንደ መሬትም 4 ወቅቶች ነው ያሏት፤ እርግጥ ነው፤ የከባቢ አየሯ ቅዝቃዜ አያድርስ ! ነው የሚያሰኘው። ከዜሮ በታች 125 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ይወርዳል። ደግሞም እንደምድራችን አየር ወጣ ብለው የሚተነፍሱት አየር አይደለም ያላት። አንዱ ትልቅ ልዩነትም ይህ ነው። የማርስ ከባቢ አየር 95 ከመቶው የተቃጠለ አየር (ካርበን ዳይኦክሳይድ) ሲሆን 3% ናይትሮጂን፤ 1,5% ደግሞ አርገን ነው። ውሃ መገኘቱ ተረጋግጧል፣ ኦክስጂን ግን የለም።

ለንጽጽር ያህል ፤ የመሬት ከባቢ አየር፤ 78 ከመቶ ናይትሮጂን፣ 21 ከመቶ ኦክስጂን፤ 1% አርገን፣ እንዲሁም 0,3% ካርበን ዳይኦክሳይድ ነው።

አንድ የማርስ ቀን፣ 24,6 የመሬት ሰዓት ነው።

አንድ የማርስ ዓመት=1,88 የመሬት ዓመት= 687 የመሬት ቀናት= 669 የማርስ ቀናት መሆኑ ነው።

ታዲያ ፤ ወደዝች ፕላኔት ነው የሚተነፈስ አየር ሳይቀር ተሰንቆ የ 520 ቀናት የደርሶ-መልስ ጉዞ እየታሰበ ያለው። ሐሳቡ፤ እውን እንዲሆን ሙከራም ተካሄዷል ። ይኸው ሙከራ ደግሞ ባለፈው ዓርብ በአመርቂ ውጤት መደምደሙ ተነግሯል።

520 ቀናት ተገልለው ፣ በአንድ ልዩ ዝግ ቤት ውስጥ፣ ማለትም ልክ ወደ ኅዋ በመመጥቅ፣ ማርስ ደርሶ እንደተመለሰ በሚታሰብ መንኮራኩር ውስጥ ፤ መሬት ላይ ማለትም ሞስኮ ውስጥ በምርምር ጊዜያቸውን ያሳለፉ 6 ተመራማሪዎች፤ ባለፈው ዓርብ ፤ ከቆዩበት ልስን ልዩ ጊዜያዊ ቤት ውስጥ ሲወጡ ፤ የቅርብ ቤተ-ዘመድና የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪዎች በጋለ ጭብጨባ ተቀብለዋቸዋል። ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችም በሥፍራው ተገኝተው ነበር።፣ እንደመንኮራኩር በታሰበው ልዩ ቤት ውስጥ 520 ቀናት ያሳለፉት ፤ 3 ሩሲያውያን አንድ ፈረንሳዊ ፤ አንድ የኢጣልያና የኮሎምቢያ ተውላጅ እንዲሁን እንድ ቻይናዊ ናቸው። የተልእኮው መሪ አሌክሴይ ሲቲየቭ፤ ሀኪሙ፣ ሱክሮብ ካሞሎቭና የሥነ ልቡና ባለሙያው አሌክሳንድር ሶምሊየቭስኪ (3ቱም ሩሲያውያን ናቸው)

ፈረንሳዊው ኢንጂኔር ፤ ሮማ ሻርል፤ ቻይናዊው የኅዋ በረራ ጉዳይ አስተማሪ ዋንግ ዩ፣ እንዲሁም ኢታሎ- ኮሎምቢያዊው፣ ዲየጎ ዑርቢና ነበሩ፣ እ ጎ አ ከ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ ም አንስቶ በሞስኮው የምርምር ጣቢያ 520 ቀናት አሳልፈው ፣ ተልእኮአቸውን ያጠናቀቁት። --ዲየጎ ዑርቢና --

«የአውሮፓ የኅዋ ድርጅት አባል ለሆንኩት ለእኔ ፣ በሙያቸው እጅግ ከተካኑ 5 ሰዎች ጋር፤ የዚህ አስደናቂ ተግባር ክንውን ተሳታፊ መሆን በመቻሌና ፣ ከእነዚህ የማይበገሩ ግለሰቦች ጋር አብሬ በመሥራቴ ፤ ክብር ይሰማኛል። በዚህ የረጅም ጊዜ ሚሲዮን ከቅርብ ላበረታቱኝ፤ ከጎኔ ለቆሙት ሁሉ ምሥጋናዬ ምንጊዜም አይለያቸውም።»

የኅዋ ምርምር ነክ ጠበብት እንዳሉት፤ ወደ ማርስ አስተማማኝ ተልእኮ ለማከናወን ሥነ ቴክኒኩ ፣ ገና ዐሠርተ-ዓመታት ይቀሩታል። የሩሲያ ጠፈርተኞችና የጠፈር መንኮራኩር መርኀ ግብር ኀላፊ አሌክሴይ ክራስኖቭ፣ እንዳሉት ፣ ይኸው የልምምድ ተልእኮ ፣ ወደ ማርስ የሚደረገው ተጨባጭ ተልእኮ የተሳካ ይሆን ዘንድ ገንቢ መረጃ ለማሰባሰብ ረድቶናል ብለዋል። የማርስ 500 ሙከራ 15 ሚሊዮን ዶላር (10,9) ሚሊዮን ዩውሮ ወጪ ያስወጣ ሲሆን አብዛኛውን የከፈለችው ሩሲያ ስትሆን፤ የአውሮፓው ኅብረት ድርጅት እና ጀርመንም ለፕሮጀክቱ ክፍለዋል።

ወደ ማርስ ለሚደረግ ጉዞ፣ ጠፈርተኞቹ ያሳለፉት ጊዜና ያደረጉት ምርምር በተሣካ ሁኔታ ተደምድሟል። አብዛኛው ቀሪ ሥራ ከእንግዲህ የሳይንቲስቶች ይሆናል። በመቶዎች የሚቆጠሩትን የቤተ ሙከራ ክንውኖች ፣ መመርመርና ወደ ማርስ አንድ ቀን ሰዎች ለሚጓዙበት ተልእኮ ፤ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማሟላት መጣር፣ ሳይንቲስቶችን በእርግጥ የሚፈትን ብርቱ ተግባር ነው የሚሆነው። ወደ ማርስ ለመጓዝ የሚያስችለው ዝግጅት በተጠናቀቀ በ 5 ኛው ቀን ባለፈው ሌሊት ለዛሬ አጥቢያ፤ ሩሲያ ወደ ማርስ ጨረቃ ፣ ፎቦስ መንኮራኩር ያመጠቀች ሲሆን፤ መለስተኛም ሆነ ከባድ እንከን ሳያጋጥማት አልቀረም።

መንኮራኩርዋ፤ እንደታቀደው፤ ከከባቢ አየር ምኅዋር ወጥታ፤ ወደ ማርስ የሚያመጥቃትን አቅጣጫ መያዝ ባለመቻሏ፣ የሩሲያ የጠፈር ሳይንስ ጉዳይ ኢንጂኔሮች፤ ማስተካከል የሚችሉት፣ በሚመጡት 3 ቀናት ውስጥ ብቻ ነው። «ፎቦስ ግራንት» የተሰኘችው የሩሲያ መንኮራኩር፤ በውስጧ ዪንግሁዎ የተባለችውን የቻይና ሳቴላይትም መጫኗ ታውቋል። የሩሲያ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ሮስኮስሞስ ዋና ኃለፊ ቭላዲሚር ፖፖቭኪን ፣ ያጋጠመውን ችግር «ክሽፈት» እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፤የመንኮራኩርዋ ተልእኮ ዐበይት ዓላማዎች ያሉት ሲሆን፤ በማርስ ዙሪያ መሽከርከር ብቻ ሳይሆን፤ ከትልቋ የማርስ ጨረቃ ፎቦስ ላይ አፈርም ሆነ አሸዋ ዝቆ ወደ መሬት ማማጣትንም ያጠቃልላል።

የአሜሪካው NASA ፤ «ማሪነር» እና «ቫይኪንግ » በተሰኙት መንኮራኩሮቹ በኩል ከቅርብ የተነሱ የማርስ ፎተግራፎችን ለዓለም ህዝብ በማቅረብ ፣ አድናቆትን ማግኘቱ የታወቀ ሲሆን፤ የፈረሰችውን ሶቭየት ኅብረት የተካችው ሩሲያ ፤ እስካሁን ድረስ ፈንጠር ወዳለው የኅዋ ክፍል መንኮራኩር ልካ አታውቅም። ይሁንና በዓለም ውስጥ የመጀመሪያው ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪን ለመጀመሪያ ጊዜ ኅዋን ባሰሰበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ፤ ያህ ያሁኑ ዐቢያ ተልእኮ እንዲሳካላት ፤ ጥብቅ ምኞቷ መሆኑ የታወቀ ነው። በሚመጡት 3 ቀናት ውስጥ እቅዱን የማቃናቱ ተግባር ከሠመረ፤ ፎቦስ ግራንትማርስ የምትደርሰው በመጪው 2012 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ሲሆን፤ ፎቦስ ላይ ሳቴላይቷ የምታርፈውና አፈርም ሆነ አሸዋ የምትዝቀው በ 2013 ፤ ወደመሬት የምትመለሰውም እ ጎ አ በነሐሴ ወር 2014 ይሆናል። ፕላኔቶች ካሏቸው ጨረቃዎች ሁሉ እጅግ ጠጋ ብላ ምኅዋርዋን ጠብቃ የምትሽከረከር ፤ የማርስዋ ጨረቃ ፎቦስ ናት። ሳይንቲስቶች ተስፋ እንደሚያደርጉት ከዝች ጨረቃ አፈር ማምጣት፤ ስለፕላኔቶች አፈጣጠር ፤ ምሥጢሩን ለማግኘት ሳይረዳ አይቀርም።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ