1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሩዋንዳ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ

ሐሙስ፣ ኅዳር 15 2009

ሩዋንዳ የምትገኘዉ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በጎርጎሪዮሳዊዉ 1994ዓ,ም በሀገሪቱ በተካሄደዉ የዘር ማጥፋት ድርጊት ለነበራት ሚና ይቅርታ ጠየቀች። ቤተ ክርስቲያኒቱ በወቅቱ በድርጊቱ የተሳተፉት ተግባር የሚፀፅት መሆኑን ገልጻለች።

https://p.dw.com/p/2TBlf
Ruanda Erinnerung an Völkermord, Kirche
ምስል Getty Images/C. Somodevilla

Ruandas Kirche entschuldigt sich für Völkermord - MP3-Stereo

ቤተ ክርስቲያኒቱ ያወጣችዉ ይህን የተመለከተዉ መግለጫም የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት አንድ ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች የተገደሉበትን የዘር ማጥፋት በማቀድ፣ በመርዳት እና በተግባር መፈጸማቸዉን ማመኗም ተመልክቷል። ርምጃዋም በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በሩዋንዳ መንግሥት መካከል ለአስርት ዓመታት ያህል የነበረዉን ዉጥረት ሊያረግበዉ እንደሚችል ተገልጿል። በሩዋንዳዉ የዘር ፍጅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እጇ አለበት በሚል ስትከሰስ ቆይታለች።

በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ዕለት ይፋ የሆነዉ መግለጫ በዘጠኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፊርማ ፀፀት እና ኑዛዜ የታጀበ ነዉ። ዓላማዉም በጎርጎሪዮሳዊዉ 1994ዓ,ም ሩዋንዳ ዉስጥ በተፈፀመዉ የዘር ማጥፋት ወንጀል የነበረዉን ተሳትፎ አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ነዉ። የጳጳሳቱ ምክር ቤት በደብዳቤዉ በወቅቱ ኃላፊዎቹ የተሳተፉበትን የጅምላ ግድያ በመጥቀስ ይቅርታ ለምኗል። ጳጳሱ ፊሊፕ ሩካምባ የጳጳሳቱ ምክር ቤት እና የጳጳስ ቡተሬ ሀገረ ስብከት ቃል አቀባይ ናቸዉ።

«ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያን ጉዳት እንዲያደርስ ማንንም ባትልክም፤ እኛ የካቶሊክ ጳጳሳት በዘር ማጥፋቱ ድርጊት ሚና በነበራቸዉ በቄሶች፣ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች እና ክርስቲያኖች ቦታ ሆነን ይቅርታ እንጠይቃለን። በሰብዓዊነት ላይ ከባድ ኃጢያት ፈጽመዋል። ፈጣሪ ልባቸዉን እንዲለዉጥ እንጠይቃለን፤ ንስሀ እንዲገቡም ፤ በእነዚያ በካዷቸዉ ወገኖች ዘንድም ትክክለኛዉን ነገር በማድረግ እርቅ እንዲያወርዱ እንዲረዳቸዉም እንለምናለን። የፈጣሪን ይቅርታ መፈለግ ይኖርባቸዋል፤ ይም ደግሞ ለመላዉ ሩዋንዳ ይቅርታን የሚያወርድ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ጸጸትም እዉነቱን እንዲናገሩ ይርዳቸዉ፤ በዚህም በፈጣሪ እና በሀገሪቱ ላይ በፈፀሙት ከከፋዉ ኃጢያታቸዉ ልባቸዉ መዳን እንዲችል እንለምናለን።»

የጳጳሳቱ ቡድን አክሎም ሕዝቡም ራሱ ለጥቃትና አመፅ መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን እንዲዋጋም ጥሪ አድርገዋል። የዘር ማጥፋትን የሚያስከትልና የመከፋፈል መንፈስንም እንዲዋጋ ሕዝቡን አሳስበዋል።

Ruanda Erinnerung an Völkermord, Kirche
ምስል picture-alliance/dpa/J. Johannsen

 

«እንደ ጳጳሳት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስም በሀገራችን፤ በዚህ ይቅርታችን ሌሎች መዘዞችን እና በ1994 በቱትሲዎች ላይ የተፈፀመዉን ግድያ እናወግዛለን፤ በጎሳዎች መካከል የተፈጠረዉን ልዩነትም ከቱትሲዎች የዘር ፍጅት በኋላ ዳግም እንዲያመረቅዝ የሚያደርገዉን ቀጣይ ልዩነትም እናወግዛለን።»

ከዘር ማጥፋቱ የተረፉ ወገኖች የመሠረቱት ማኅበር ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ዣን ፒየር ዱሲንግዚሙንጉ፤ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት የመጣዉን የይቅርታ መግለጫ በደስታ ተቀብለዋል። ይህ ይቅርታም ወደ ፍትህ የሚወስድ እና የዘር ማጥፋትን የሚያስከትሉ አስተሳሰቦችን በመዋጋት ሀገርን ለመገንባት የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል።

«ድርጅታችን ይህን ዜና በከፍተኛ ደስታ ነዉ የተቀበለዉ። ሲጓተት የቆየ ነገር ነበር። ይቅርታዉን ለመጠየቅ ረዥም ጊዜ ቢወሰድም ይቅርታዉ በራሱ ትልቅ ነገር ነዉ። ቀደም ብለዉ ይህን አድርገዉ ቢሆን ኖሮ በርካታ ችግሮችን ይፈታ ነበር ብለን እናስባለን። ሆኖም ግን ወደ ሌላና መላዉ ሩዋንዳዉያን ይቅር እንዲባባሉ ወደ ማድረጉ ደረጃ ስለሚያሸጋግረን ርምጃዉን እናደንቃለን።»

በተቃራኒዉ አንዳንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ይህን መልዕክት በተደባለቀ ስሜት ነዉ የተቀበሉት። ግሩስ ኦሲምቢ ከዘር ማጥፋቱ የተረፈች ሲሆን ይህን መግለጫ በቅርበት ተከታትላዋለች።  

«ጥሩ ርምጃ ነዉ፤ አዎንታዊ ዉሳኔም ነዉ። ነገር ግን ሁልጊዜም ለ22ዓመታት መጠበቅ ነበረብን ወይ ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ። በዘር ማጥፋቱ ድርጊት የነበራቸዉን ሚና ሲክዱ ነበር። በመቀጠልም በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሁሉ መነበብ የሚገባዉ ይህ መግለጫ አልተነበበም። በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መግለጫዉ አለመነበቡ ግራ አጋብቶኛል።»

Ruanda Erinnerung an Völkermord, Kirche
ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

ስለዘር ማጥፋት በርከት ያሉ መጽሐፍትን የጻፉት ጳጳስ ጆን ንዶሊማ ቤተ ክርስቲያኗ ገጽታዋን ለማፅዳት ከዚህም የበለጠ ርቃ መጓዝ ይገባታል ነዉ የሚሉት።

«በእነዚያ ዓመታት በሙሉ ሲፈፅሙ ለቆዩት ነገር ይቅርታ መጠየቅ አለባቸዉ። ወደፊት ተራምዶ እዉነቱን ለመናገር እንቅፋቶች ነበሩ። በዘር ማጥፋቱ የሚጠረጠሩት የቤተ ክርስቲያኗ ቄሶች ሁሉ ወደፍርድ ካልቀረቡ ይቅርታ አንጠይቅም ሲሉ ነበር። እንዲያም ሆኖ አሁንም የተባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ኃላፊዎች በመላዉ ዓለም እየተንቀሳቀሱ መሆናቸዉን በሚገባ እየተረዱ ነዉ ይህን ያሉት።»

ሆኖም አብዛኛዎቹ ዋና ከተማ ኪጋሊ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት በጳጳሳቱ የተዘጋጀዉን የይቅርታ መግለጫ እንደታቀደዉ ለማንበብ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ እየተነገረ ነዉ። የቤተ ክርስቲያኒቱን ገፅታ ከማደሱ ርምጃ ጀርባም የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ መኖራቸዉ ይገመታል።

ሸዋዬ ለገሠ /ሲልቫኑስ ካረሜራ

አዜብ ታደሰ