1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሶማሊያ መሳሪያ ማዕቀብ መላላቱ

ዓርብ፣ ሐምሌ 19 2005

የተባበሩ መንግስታት ድርጅት የጸጥታዉ ምክር ቤት ከሃያ ዓመታት በላይ ያስቆጠረዉን ሶማሊያ ላይ የተጣለዉ የመሳሪያ ማዕቀብ እንዲላላ ወስኗል። የጸጥታዉ ምክር ቤት የመቅዲሹ መንግስት ራሱን ከጽንፈኛዉ አሸባብ ለመከላከል እንዲችል አቅሙ እንዲጠናከር በሚል ዉሳኔዉን ማሳለፉን አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/19ErB

በጎርጎሪዮሳዊዉ 1990ዓ,ም ሶማሊያ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ በነበረበት ወቅት ነዉ የተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የጣለባት። ከትናንት በስተያ የጸጥታዉ ምክር ቤት በድጋሚ የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ የጦር መሳሪያ ሽግግርን አስመልክቶ ባካሄደዉ ዉይይት ማዕቀብ ወደተጣለባቸዉ ኤርትራና ሶማሊያ መሳሪያ የመላክና በሁለቱ ሃገሮች በኩልም የጦር መሳሪያ የማሸጋገር ድርጊትን አዉግዟል። በ15ቱም የምክር ቤቱ አባላት ድምጽ ረቡዕ ዕለት የተላለፈዉ ዉሳኔ አሁንም በኤርትራም ሆነ ሶማሊያ ላይ የተጣለዉ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንደሚቀጥል አመልክቶ፤ ሶማሊያ ግን ለተወሰኑ ጊዜያት ማዕቀቡ እንዲላላላት ደንግጓል። በዚህ መሠረትም የመቅዲሾ አስተዳደር የጦር ኃይሉን ለማጠናከር የሚስችለዉን የጦር መሳሪያና ወታደራዊ ቁሳዉስ እንዲገዛ ፈቅዷል።

UN Sicherheitsrat Iran No Flash
የተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤትምስል AP

የሶማሊያ መንግስት እስካሁን ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በይፋ የገለጸዉ ነገር እንደሌለ ያመለከቱት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የሶማሊያ ምክር ቤት አባል ሁሴን ባንቱ ዉሳኔዉ ለሶማሊያ ደህንነት የሚታገሉ ወገኖችን እንደሚያስደስት በማመልከት፤ መንግስት ዜጎቹን ከጥቃት ለመከላከል ሌላ አማራጭ እንደማይኖረዉ ነዉ የሚናገሩት፣

«ከመንግስት ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ አልሰማሁም፤ ነገር ግን በእራሴ በኩል ዜናዉን በደስታ እንደተቀበልነዉ ልገልጽ እወዳለሁ። ምክንያቱም እጁ ሙሉ በሙሉ የታሠረ መንግስት በየቀኑ ፍንዳታ በሚደርስበት ሁኔታ ዜጎቹን ለመከላከል ምንም ማድረግ አይችልም። ማለት የምችለዉ ለሶማሊያ ደህንነት የምንታገል ወገኖች ተደስተናል የሚለዉን ነዉ።»

ከዚህም ሌላ በዉሳኔዉ መሠረት የሶማሊያ መንግስት ከሌሎች መንግስታት የቴክኒኒክ እና ስልጠና ድጋፍ ማግኘት ይችላል። የጸጥታዉ ምክር ቤት የረቡዕ ዕለት ዉሳኔ በኋላ የሶማሊያ መንግስት እስከመጪዉ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጋቢት ወር ድረስ የጦር መሳሪያ ማስገባት ይችላል። እንዲያም ሆኖ ግን የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች ከባድ የጦር መሳያዎችን የአየር መቃወሚያ፤ ጸረ ታንክና ለሌሊት የሚሆኑ የጦር መሳሪያዎችን እንዲሁም የረዥም ርቀት አዳፍኔ፣ ጠብመንጃዎች፣ መድፎችና ቀለሃዎችን እንዳያስገቡ ያገደዉ ዉሳኔ እነዚህን መሳሪያዎች ለመግዛት የመቅዲሹ መንግስት ሲዘጋጅ በጸጥታዉ ምክር ቤት የመሳሪያ ማዕቀብን የሚመለከተዉ ኮሚቴን ይሁንታ አስቀድሞ ማግኘት ይኖርበታል። የሶማሊያ መንግስት የምክር ቤት አባል ሁሴን ባንቱ የመንግስት ጦር በቂ መሳሪያ የለዉም ይላሉ፤

«መሳሪያ ከሌለ ፖሊስ G 3 አቶማቲክ ጠብመንጃ ነዉ ያለዉ እንዴት አድርጎ አገራችንን ያድናል? መንግስታችን እንዲጠናከር ታንኮች፣ ተዋጊ ጀቶችእና የጦር ሄሊኮፕተሮች ያስፈልጉናል። መንግስት ከተዳከመ የቦምብ ጥቃቱ ይቀጥላል። አነስተኛ መሳሪያዎች ሶማሊያን ከአሸባሪዎች ሊያድኗት አይችሉም። አሸባሪ እንኳ ቢያጠቃል AK 47 ጠብመንጃህን ይዘህ አፍጥጠህ ከማየት ዉጭ አማራጭ የለህም። ጠብመንጃዉ ሊታደግህ አይችልም።»

Somalia Soldaten
የሶማሊያ ወታደሮችምስል dapd

የጸጥታዉ ምክር ቤት ከዚህ በተጨማሪም ከሶማሊያ የታገደዉ የከሰል ንግድ እንዳልቆመ የሚጠቁም ዘገባ መኖሩን በመግለጽ ሁኔታዉ እንዳሳሰበዉ አመልክቷል። በማዕከላዊና ደቡባዊ ሶማሊያ በርከት ያሉ አካባቢዎች መቆጣጠሩ የሚነገርለት እስላማዊ ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን አሸባብ ራሱን በገንዘብ ለመደገፍ በዚህ ንግድ መሠማራቱ ነዉ የሚነገረዉ። የከሰል ንግዱን ማዕቀብ የሚከታተለዉ ቡድን በዘገባዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም አሸባብ ከከሰል ንግዱ ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱን ጠቁሟል። በዚህ ሁኔታም ከሰል ወደሌላ አገር የመሸጡ ተግባር ከቀጠለም በሁለት ዓመታት ዉስጥ ከአስር ሚሊዮን በላይ ዛፎች እንደሚጨፈጨፉ ዘገባዉ ጨምሮ አስታዉቋል። በሶማሊያ ያለዉ ሁኔታና ኤርትራ መቅዲሾ ላይ የምታሳርፈዉ ተፅዕኖ እንዲሁም በጅቡቱና በኤርትራ መካከል የቀጠለዉ አለመግባባት ለዓለም ዓቀፍ ሰላም እና ጸጥታ ስጋት መሆኑን የጸጥታዉ ምክር ቤት በማመልከትም፤ የማዕቀቡ ተከታታይ ቡድንን የኃላፊነት ጊዜ እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2014ዓ,ም ህዳር ወር ድረስ ማራዘሙን አስታዉቋል። ባለፉት ዓመታት ሶማሊያ ዉስጥ ለዉጥ መታየቱን ያመለከተዉ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታዉ ምክር ቤት የዘፈቀደ ግድያና እስራት እንዲሁም ጾታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸዉ እንደሚያሳስቡት በመግለጽ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና ወንጀል እየፈጸሙ በነፃነት መሄድ እንዲቆምና ጥፋት የፈጸሙ በህግ መጠየቅ እንደሚኖርባቸዉም አሳስቧል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ