1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳሃሮቭ ሽልማት ለሽብርተኛዉ ቡድን ሰለባዎች

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2009

እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ታፍነዉ የነበሩ ሁለት የያዚድ ሃይማኖት ተከታዮች የአዉሮጳ ኅብረት የሚያበረክተዉን የዘንድሮዉን የሳሃሮቭ ሽልማት አገኙ።

https://p.dw.com/p/2UDj1
EU-Parlament Sacharow-Preis Nadia Murad und Lamija Adschi Baschar
ምስል Reuters/V. Kessler

የ 23 ዓመትዋ ናዲን ሙራድና የ 18 ዓመትዋ ላሚያ ሃዱሺ ባሻር በጎርጎረሳዊዉ 2014 ዓ,ም ይኖሩበት በነበረዉ በሰሜናዊ ኢራቅ በሚገኝ አንድ አነስተኛ ገጠር በአሸባሪዉ ቡድን ታፍነዉ ተወስደዉ ለወራቶች የወሰቢ ጥቃት ሲፈፀምባቸዉ ከነበረበት ቦታ አምልጠዉ ጀርመን ለመግባት በቅተዋል። ሁለቱ ወጣቶች ጀርመን ከደረሱ በኋላ አሸባሪዉ ቡድን አፍኖ በወሰዳቸዉ በሽዎች በሚቆጠሩ ሴቶች እና ታዳጊ ልጃገረዶች ላይ የሚፈፅመዉን ጥቃት በማጋለጥ ላይ ይገኛሉ። የሽልማት ሥነ-ስርዓቱ ላይ ዛሬ የ 18 ዓመትዋ ላምያ ባሽር ሽልማቱ ለኔ አለች፤
« ይህ ሽልማት ለኛ ትልቅ ነገር ነዉ። ለኔና ለናድያ ብቻ ሳይሆን ስቃይ ለሚፈፀምባቸዉ ሴቶች በሙሉ ወይም ደግሞ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ለሚለዉ ቡድን ሰለቦች ሁሉ ነዉ ። ዓለም ድምፃችንን፤ ታሪካችንን እየሰማ ነዉ። እናም ዓለም ርምጃዉን በማጠናከር እኛን ይታደጋል።»  ሌላዋ የ 23 ዓመት የ «IS» ቡድን ሰለባና ተሸላሚ ናዲን ሙራድ በበኩላ ስለሽልማቱ እንዲህ ነበር ያለችዉ። 
«የሳሃሮቭ ሽልማት ለኛ ለተጎጅዎች እጅግ ዋናና አስፈላጊ ነዉ። ለያዚዲን ማኅበረስብ ጭምር ከአዉሮጳ ኅብረት ያገኘነዉም ትልቅ ድጋፍ ነዉ። ግን የሳሃሮቭ ሽልማት «IS»ን አይገታም፤ አያስቆምም። የአዉሮጳ ኅብረት  «IS»  መታገል የመብት ጥያቄ መሆኑን በማሰብ «IS» የያዘዉን የጽንፈኛ ርዕዮተ በመግታት ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ይኖርበታል።»  
በአሁኑ ወቅት የ 23 ዓመትዋ ናዲን ሙራድ በሰሜናዊ ኢራቅ ተጨቁነዉ ለሚገኙት የያዚድ ኃይማኖት ተከታይ ማኅበረሰቦች የተመድ ልዩ መልክተኛ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለት። ሁለቱ ወጣት ሴቶች በአሁኑ ወቅት በጀርመንዋ የቫድንቡተንቨርግ ግዛት የተገን ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት አግኝቶ መኖር መጀመራቸዉም ተገልጾአል። ኃሳብን በነጻነት ለመግለፅ በታገሉት በሟቹ ሩስያዊ የፊዚክስ ምሑር ስም የተሰየመዉ የሰሃሮቭ ሽልማት ከጎርጎረሳዊዉ 1988 ዓ,ም ጀምሮ ለሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ለሚታገሉ ሰዎች እንደሚበረከት ይታወቃል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ