1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩ ኤስ አሜሪካ ወጣት ተሟጋቾች

ዓርብ፣ ኅዳር 15 2010

ምንም እንኳን የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በከባቢ አየር ለውጥ ባያምኑም በርካታ ወጣት አሜሪካውያን የአየር ንብረት ለውጡ እንደሚያሳስባቸው ይናገራሉ።ባለፉት ሁለት ሳምንታት ቦን ከተማ በተካሄደው የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ሶስት ወጣቶች ለዶይቸ ቬለ እንደገለፁት ሀገራቸው ከፓሪሱ ስምምነት ራሷን ማግለል የለባትም።

https://p.dw.com/p/2oCCG
Deutschland Das COP 23 Gelände der UN-Klimakonferenz in Bonn
ምስል picture alliance/Geisler-Fotopress/J. Zumbusc

ከ197  ሃገራት የመጡ  23 000  ተሳታፊዎችን ባስተናገደው የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ ላይ ከተሰበሰቡ ወጣቶች አንዷ ዳይና ጄይ ትባላለች። የዩ ኤስ አሜሪካውያን የወጣቶች ስብስብ የሆነው የሰን ራይዝ ሙቭመንት ወይም ሰን ራይዝ ንቅናቄ አባል ናት።  « ሰን ራይዝ ንቅናቄ  ከበባቢ አየር ለውጥን ለማስቆም ወጣቶችን ያስተባብራል። እና በሚሊዮን የሚቆጠር አዲስ ስራዎችን መፍጠር ይሻል። ወጣቱ ፖለቲካዊ ኃላፊነት እንዲኖረው እናነሳሳለን። መሰረት የሆነንን ንፁህ አየር እና ንፁህ ውሃችንን ዘላቂነት እንደኖረው መጠበቅ ይኖርብናል።» 
ዳይና ጄይ ፕሬዚዳንታችን ያለውን እውነታ ቢክዱም በቅርብ ጊዜ ዮናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰቱ አደጋዎች ሁኔታው ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆኑ ይጠቁማሉ ትላለች። እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው ከጥቂት ጊዜ በፊት ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስን ያጠቃው ሰደድ እሳትን እና  ከምስራቁ ክፍል  ብዙ ሰዎችን ያፈናቀለው ኤርማ የተሰኘው የአውሎ ንፋስ ወጀብ ጥፋትን ነው።
የከባቢ አየር ለውጥ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ ከሁለት አመት በፊት ፓሪስ ላይ የሙቀት ልቀት መጠንን ለመቀነስ ከስምምነት ቢደረስም ዶናልድ ፕራምፕ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ሀገራቸው ራሷን ከፓሪሱ ስምምነት እንደምታገል ተናግረዋል። ወጣቷ የአየር ንብረት ተሟጋች እንደምትለው ግን ፕራምፕ ይህንን እውን ሊያደርጉ አይችሉም።« የፓሪስን ስምምነት መሰረዝ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻዎች አንዱ ርዕስ ነበር። ነገር ግን ይህን ተግባራዊ ማድረግ አይችሉም። የፓሪስ ስምምነት የመልቀቅ እቅዳቸውን ሲናገሩም  እስከ 2020 ዓም ድረስ መልቀቅ እንደማንችል ማወቅ ነበረባቸው። »
ዳይና ጄይ በፕሬዚደንቷ ርምጃ ብታዝንም በየግዛቱ ያለው የአሜሪካ ህዝብ አቋም ተስፋ ሰጪ ነው ትላለች። እንደሷ ከሆነ አብላጫው ህዝብ የፓሪሱን ስምምነት ከመደገፍ ሌላ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ወሳኝ ርምጃም እንዲወስድ ይፈልጋል።  በሲያትል ነዋሪ የሆነው ሌላው አሜሪካዊ ወጣት ኪይነር ኡመንም የፕራምፕን አቋም ይቃወማል። ፕራምፕ ሀገራቸው ስምምነቱን እንድታፈርስ የሚያደርጋት አንዱ ምክንያት ከፍተኛ ወጪ ስለሚያስወጣት ነው ብለዋል። ኪይነር በዚህ አይስማማም። « እሳቸው ትናንሽ የንግድ ተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ነው ይላሉ፤  እዚህ ያሉ ትናንሽ የንግድ ተቋማት የሚሉት ግን በስምምነቱ መዝለቅ እንፈልጋለን ነው የሚሉት። አዲስ ስራ ይፈጥራል። ወደ ታዳሽ ኃይል መቀየሩ በሁሉም መልኩ ትርፋማ ነው የሚያደርገው። ለወደፊት የምናስብ ከሆነ  የንፋስ ፣ የጸሀይ ኃይል ላይ ማተኮር፣ አዲስ ቴኖሎጂ ላይ ሙዋለ ንዋይ ማፍሰስ ፤ እነዚህ ሁሉ ስራዎች ይፈጥራሉ። የዮ ኤስ ህዝብ ይህ ይገባዋል። ለምን የዩ ኤስ የመንግሥት ይህ እንደማይገባው ግን አይገባኝም።»
ይላል። ኪይነር ኡመን። ዳይናም ብትሆን የአሜሪካን የፀሀይ እና ታዳሽ ኃይል ድርጅቶች በርካታ የስራ መስኮች እየፈጠሩ ነው በሚለው ትስማማለች። ኪይነር በሚኖርበት በምዕራቡ ክፍል  ከጊዜ ወደ ጊዜ  ደኖች እየተቃጠሉ መሆኑ በግሉ ያሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ  ሰዎች አለርጂ እና አስም እያጠቃቸው መሆኑን በራሴ ወንድም ልታዘብ ችያለሁ ይላል። ወጣቱ ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ህንድ የሚኖሩ ዘመዶቹም ዮናይትድ ስቴትስ ከሚገኙት በላይ በአየር ንብረት ለውጡ እየተጎዱ መሆኑን ይናገራል።  ታድያ የህዝቡ ተሳትፎ የዮናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ውሳኔን ይቀይር ይሆን?« የትራምፕ አስተዳደር ራሱን ከፓሪሱ ስምምነት እንዳገለለ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ከተሞች አይሆንም ነው ያሉት። መንግሥት የፈለገውን ሊል ይችላል ነገር ግን ከተሞች ፣ ግዛቶች ሁሉም የወደፊቱ ሁኔታ ያሰጋናል ፤ ከሌላው የአለማችን ክፍል ጋር ትብብራችንን ማሳየት ይኖርብናል እያሉ ነው። ስለዚህ ዋሽንግተን ውስጥ ምንም ማድረግ የሚችሉት ነገር የለም። ምክንያቱም ሀገራችን ህዝባችን ነው እንጂ መንግስት አይደለም። »
በዚሁ ቦን ከተማ በተካሄደው የተመድ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ ላይ የተሳተፈችው ሌላዋ አሜሪካዊት ኩሪና ኮንሳለስ ትባላለች። ሰስቴን አስ የተባለ የወጣቶች ቡድንን ወክላ ነው በትልቁ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የተሳተፈችው። በዩናይትድ ስቴትስ ተወልዳ ያደገችው ወጣት ዮናይትድ ስቴትስን ወክላ ወደ ቦን ብትመጣም የዘር ሀረጓ በሆነችው ሀገር ሜክሲኮም ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ያሳስባታል።« ሜክሲኮ እጅግ በጣም ውብ ደን የሚገኝበት ቦታ የሚኖሩ በርካታ ዘመዶች አሉኝ። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን የአየር ንብረቱ ለውጥ ተጎጂ እየሆኑ ነው። የወቅቶች መለዋወጥ ገጥሟቸዋል። ዝናብ መዝነብ ባለበት ወቅት አይዘንብም። ይህ ደግሞ የበቆሎ እርሻው አስተዳደግን ይጎዳል። እንስሶችን ይጎዳል። ዘመዶቼ  የሚኖሩበት ደን  በጣም በሚያማምሩ ቢራቢሮዎች ይታወቃል። ወደ ጫካው ሲገባ ሰው እስከሚፈራ ድረስ በቢራቢሮ ነው የሚከበበው። አሁን አሁን ግን ቢራቢሮዎቹ ሲሰደዱ መታዘብ ተችሏል። እነዚህ በቀጥታ የታዩ ለውጦች ናቸው። ቀጥሎ የሚመጣውን ደግሞ ማን ያውቃል።»
ስለሆነም የዩናይትድ ስቴትስ ወጣት ልኡካኑ በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤው ላይ ተገኝተው የተቻላቸውን ያህል ተሰሚነት ለማግኘት ሞክረዋል። ኩሪናም ብትሆን ራሷን ከፕሬዚደንቷ አቋም አግላ የአየር ንብረት ለውጡ በቀጥታ ተጠቂ ከሆኑት ሀገሮች ጎን መሰለፏን እና ሀገሯ በካይ ጋዝ በመልቀቅ ለአየር ንብረት ለውጡ ተጠያቂ ከሚባሉት ተርታ እንደምትሰለፍ ትናገራለች። ይህ ብቻ አይደለም።« እዚህ የተገኘው ዩናይትድ ስቴትስ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ወንጀለኛ እንደሆነች ለመግለጽ ነው። ዶናልድ ትራምፕ እና አስተዳደራቸው የአሜሪካንን ህዝብ አይወክሉም። የህዝብ መጠይቆች እንደሚያሳዩት የአሜሪካ ህዝብ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ይፈልጋል። የአሜሪካ ህዝብ የፓሪሱን ስምምነት መጠበቅ ይፈልጋል። በአጠቃላይ ትራምፕ ህዝቤ የሚሏቸው እኛን አይወክሉም። »
የተለያዩ ተቋማትን ወይም ቡድኖችን ወክለው የተሰበሰቡት የዩናይትድ ስቴትስ ወጣት ልኡካን በአየር ንብረቱ ላይ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ ነው። እነሱ ብቻም አይደሉም 14 የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ከ400 በላይ ከንቲባዎች 1700 የንግድ ተቋማት እና ከ300 በላይ ዩንቨርስቲዎች የትራምፕን የአየር ንብረት ፖሊሲ ተቃውመዋል። ዳይና እንደምትለው ይህ ሰንራይዝ ንቅናቄ ገና በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስተባበረው ድጋፍ ነው።« ወጣቱ በትክክለኛው መስመር ላይ ይገኛል።ይህም ተስፋ ይሰጠኛል። በአሁኑ ሰዓት ለሁሉም ማህበረሰብ ጠቃሚ ነው የምንለውን እውን ለማድረግ የሚያስፈልገንን ስልጣን ለመቆጣጠር በአሁን ሰዓት አቅሙ እንደሌለን ግልፅ ነው። በርግጥ የሌሎች ድጋፍ አለን።  ብቻችንን አይደለንም። ነገር ግን በዚህ ትውልድ አቅም በጣም አምናለሁ። 
አገራቸውን ከፓሪሱ ስምምነት ለማስወጣት የወሰኑት ትራምፕ በቦኑ የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ አልተሳተፉም።  ዳይና ጄይን በትራምፕ የአየር ንብረት ለውጥ አቋም ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በአስተዳደራቸው ታፍራለች።« ፕሬዘዳንታችን በአለም አቀፍ ደረጃ የሚያሳፍር ነው። ይህ የተለመደው አይነት አመራር አይደለም። እስካሁን በታሪክ ከነበሩት ፕሬዚደንቶች በሙሉ ትራምፕ የመጨረሻውን ቦታ ነው የሚይዙት። እኛ አሜሪካውያን አሁንም እየታገልን ነው።ይህንን ራሱን ያገለለ አስተዳደር መቋቋም እንድንችል ዓለም አቀፉም ማህበረሰብም እየተባበረን ይገኛል።»
ለ 15 ሆነው ወደ ቦን የተጓዙት ሰስቴን አስ የተባለ የወጣቶች  ቡድንን  የምትመራው ኩሪና የተልዳ ያደገችው ካሊፎርኒያ ነው። ካሊፎኖርኒያ መቆጣጠር ያቃቷት ሰደድ እሳቶች በተደጋጋሚ ገጥመዋታል። እርስዋ እንደምትለው ችግሩ ከተባባሰ ሀብታም ሀገራት እንኳን ሊቆጣጠሩት ከሚችሉት አቅም በላይ ይሆናል።«እኛ እንደ ዮናይትድ ስቴትስ ያሉ ሀብታም ሀገራትም በቀጥታ የአየር ንብረት ለውጡ ተጠቂ ስንሆን ተመልክተናል። ይህ ገና ጅማሬው ነው። አንድ መፍትሄ ላይ አሁኑኑ መድረስ እንዳለብን ምልክቶች አይተናል። ለውጡን እያየን ነው። ሀብታም ሀገሮችም ፈተናውን እየተጋፈጡ ነው።»
ልደት አበበ

COP23 Klimakonferenz in Bonn Demonstration
በቦን የተካሄደው ስብሰባ በርካታ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።ምስል DW/G. Rueter
Hurrikan Irma | USA, Florida | Miami
ፍሎሪዳን የመታው አውሎ ንፋስምስል Reuters/C. Barria
USA Feuerwehr bekämpft Brände in Calistoga
የካሊሮርኒያ የሰደድ እሳት ምስል Reuters/J. Urquhart

ኂሩት መለሰ