1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል ለተፈጥሮ ጥበቃ የተወሰደው ርምጃ

ማክሰኞ፣ የካቲት 6 2010

ላለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ የዉኃ አካላት በአካባቢያቸው የተገነቡ ልዩ ልዩ ፋብሪካዎች በሚለቁባቸው ፍሳሽ ምክንያት ለብክለት መዳረጋቸውን ምሁራን እና የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ሲያሳስቡ እና መረጃ ሲያካፍሉ ቆይተዋል።

https://p.dw.com/p/2sdUh
Landwirtschaft Äthiopien Dreschen von Hirse
ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu

ለተፈጥሮ ጥበቃ የተወሰደው ርምጃ

 ዶቼ ቬለም በዚሁ መሰናዶ ይህንን ስጋት አበክረው ያስገነዘቡ ምሁርን አቅርቦ በውኃው እና በአፈሩ ላይ የሚታየውን የብክለት መጠን ለመጠቆም ሞክሯል። ከሰሞኑ የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለዉጥ ባለስልጣን ብክለቱን አደረሱ ካላቸው ፋብሪካዎች አምስቱ ሥራቸው እንዲቆም ማድረጉን ይፋ አድርጓል። አቶ ቦና ያዴሳ በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የአየር ንብረት ለዉጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ርምጃው ስለተወሰደባቸው ፋብሪካዎች እንዲህ ይላሉ፤

«በተደጋጋሚ በሚደረግላቸዉ የክትትል እና ድጋፍ ሥራዎች የአካባቢ ሕግ በሚጠይቀው መሠረት በአካባቢ ላይ ብክለት ሲያደርሱ የቆዩ እና ማሻሻል ያልቻሉ ናቸው። ለረዥም ጊዜ ቅሬታ እና የሕዝብ አቤቱታ የነበረባቸው በተጨባጭ ደግሞ በአካባቢ ላይ ብክለት ሲያስከትሉ የነበሩ ፋብሪያዎች ነው የመዝጋት ርምጃው የተወሰደው እስኪያስከተካክሉ ድረስ።»

ፋብሪካዎቹ በተለያዩ ከተሞች ያሉ ሲሆን ለምሳሌም ሱሉልታ ላይ ያለውን የቆዳ ፋብሪካ፤ ሰበታ ላይ የሚገኘው የቆዳ ፋብሪካ እንዲሁም ቢሾፍቱ ላይ የፒቪሲ ማምረቻ ፋብሪካዎች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውንም ጠቅሰቃል።

ኢትዮጵያ በሀገር ደረጃ የሚካሄድ ማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ የሚያዝዝ የአካባቢ ጥበቃ ሕግ አላት። ፋብሪካዎችም ሆኑ የማዕድን ማውጣት ተግባራት ላይ የሚሰማሩ አካላት ይህን እንዲከተሉ ይጠበቃል። የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን እንዲዘጉ ያደረጋቸው ፋብሪካዎች ከዚህ ዉጭ ይሆኑ ይሆን?

Äthiopien, Zuckeranbau in Adama
ምስል DW/M. Yonas Bula

ርምጃዉም አምስት ፋብሪካዎችን በመዝጋት አላበቃም፤ ሌሎች ስድስት መቶ የሚሆኑ ማምረቻ እና ፋብሪካዎች ላይ የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ክትትል እና ቁጥጥር ማካሄዱንም አስረድተዋል።

ከዚህ ሌላ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸዉ 126 ማምረቻ እና ፋብሪካዎች መኖራቸዉንም አመልክተዋል። ማስጠንቀቂያው ደረጃ በደረጃ የሚሰጥ ሲሆን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸውም አሉ።

በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ባስከተሉት አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት ከተዘጉት በጉጂ ዞን የሚገኘው የቀንጢቻ ታንታለም ማዕድን ማምረቻ አንዱ ሲሆን ንብረትነቱ የፌደራል መንግሥት ነው። የኦሮሚያ ዉኃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቡሌ አበጋዝ በክልሉ የተለያዩ የማዕድን ማውጣት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በመጥቀስ፤ በተለይ ታንታለም የተባለውን ማዕድን በማምረቱ ሂደት በአካባቢዉ የተፈጥሮ ሀብት ላይ የደረሰው ብክለት ለሰዎች የጤና ጠንቅ እስከመሆን መድረሱን አውስተዋል።

ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሀገሪቱ ውስጥ ፋብሪካ እና ማምረቻዎች ብክለት ማስከተላቸው ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው። እንዲህ ያለው ዉሳኔ ላይ ለመድረስ ለምን ረዥም ጊዜ ወሰደ? አቶ ቦና ያዴሳ ፤ ምላሽ አላቸው።

«እንደሚታወቀው የአካባቢ ተቋም አደረጃጀት ጠንካራ አልነበረም፤ በክልልም በፌደራል ደረጃም። ማለት የአካባቢ ሕጎችን የማስከበር አቅም ደካማ ነበር፤ አደረጃጀቱም እስከታች ያልወረደ ነበር። ሁለተኛ ደግሞ ለአካባቢ የተሰጠው ትኩረት እዚህ ደረጃ አልደረሰም። ስለዚህ በተለይ ከባለፈው ሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው የተሀድሶ ሂደት ፤ የሕዝቡ ቅሬታ ዛሬ አይደለም በፊትም ነበር፤ በተለያየ መስክ የሚነሳውን የሕዝብ ቅሬታ በተገቢ መልክ ለመመለስ ከተሀድሶው ወዲህ የአደረጃጀቱም ይሁን የኮሚትመንቱ ጉዳይ ፖለቲካል ኮሚትመንትም ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረ ነው።»

በኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ለረዥም ጊዜያት ከኅብረተሰቡም ሆነ ለአካባቢ ተፈጥሮ ደህንነት በሚቆረቆሩ ወገኖች ሲቀርብ ለከረመው አቤቱታ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠበትን ርምጃ አስመልክቶ ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን ከልብ እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ