1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ለትምህርት ፖላንድ ያቀኑት ኢትዮጵያውያን

ዓርብ፣ የካቲት 19 2013

በአሁኑ ጊዜ ጥሩ የሥራ ዕድል ለማግኘት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብቶ ተምሮ መመረቅ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል። ባመዛኙ ወደ ሌሎች ሃገራት ሄደው ልምድ የቀሰሙ ተማሪዎች የተሻለ የሥራ ዕድል ሲያገኙ ይስተዋላል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ለትምህርት ወደ ፖላንድ የተጓዙ ሦስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን እንግዳ አድርገናል።

https://p.dw.com/p/3pvtZ
Coronavirus | Symbolbild Universitätsstudium Online-Semester
ምስል Edith Geuppert/Ges/picture alliance

ለትምህርት ፖላንድ የተጓዙት ኢትዮጵያውያን

 የምዕራብ ሃገራት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያንም ጭምር የመጀመሪያ ወይም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ውጭ ሀገር ሄደው ለመማር ሲጥሩ ይስተዋላል። የሚሳካላቸው ግን ውስን ናቸው። በአብዛኛው ውጭ ሀገር ሄዶ መማር ከብዙ ክፍያ እና የይለፍ ፈቃድ ማለትም ቪዛ ጋር የተያያዘ ነው። ምሕረት ፤ ቤቲ እና ቃለ አብ ይህ ተሳክቶላቸው በአሁኑ ሰዓት የጀርመን ጎረቤት ሀገር ፖላንድ ይገኛሉ።  ምሕረት ወደ ፖላንድ ለመሄድ የመረጠችበትን ምክንያት ስትገልፅ« አውሮፓ ነው፣ ለሁሉም ነገር ምቹ ነው» ትላለች። የ 22 ዓመቷ ቤቲም ብትሆን ተመሳሳይ ነገር አሳምኗት ነው ትምህርቷን ፖላንድ ለመከታተል የወሰነችው። « እየተማርኩ መስራት እችላለሁ። የሚሰጠንም የሸንገን ቪዛ ስለሆነ አውሮፓ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ቀላል ነው»ትላለች። የትምህርት ቤት ክፍያውም በዓመት 2200 ዩሮ ስለሆነ «ርካሽ ነው» ስትል ምክንያቷን ታብራራለች። ቤቲ ኢትዮጵያ ሳለች የዮንቨርስቲ ተማሪ ነበረች። ይሁንና ፖላንድ ውስጥ ትምህርቷን እንደ አዲስ ነው የጀመረችው።  « የ12 ክፍል ውጤታችንን ያያሉ » ይህም ቪዛ ለማግኘት ወሳኝ ነው»።

ሌላው እንደነሱ ፖላንድ ሀገር የሚማረው ኢትዮጵያዊ ቃለ አብ ይባላል። የ24 ዓመቱ ወጣት የሁለተኛ ሴሚስተር ተማሪ ነው። ከሌሎቹ ቀድሞ ፖላንድ የገባውም እሱ ነው። « ኢትዮጵያ ውስጥ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ ነበረኝ፤ ነገር ግን አንድ አመት ሙሉ ስራ ማግኘት አልቻልኩም።» እሱም የታክሲ ስራ አንደጀመረ አንድ ጓደኛው ስለዚህ የትምህርት እድል ይነግረዋል።
ቃል አብም ተመዝግቦ የመማር እድሉን ያገኛል።
ሦስቱም የዓለም አቀፍ ንግድ አስተዳደር ተማሪዎች ናቸው። የ 20 ዓመት ወጣት የሆነችው ምሕረት፤ ወደ አውሮፓ ከመጣሁ « አምስት ወር ገደማ ሆነኝ » ትላለች። በዚህ በኮሮና ወቅት እየሠራች መማር መቻሏ ያስደስታታል።  ትምህርት የሚማሩት በኦንላይን ነው። ታድያ ትምህርታቸውን ኢትዮጵያ ሆነው መከታተል አይችሉም ነበር?

የፖላንድ ሉቢን ከተማ
የፖላንድ ሉቢን ከተማምስል Fotolia/Jaroslaw Grudzinski

ምህረት« እዚህ መጥተን ካልተመዘገብን ትምህርት መጀመር አንችልም።» ነገር ግን « መጥተው ተመዝግበው ከዛም ቤተሰባቸው ጋር ሆነው ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ኢትዮጵያ የሄዱ ልጆች አሉ» ትላለች።  እሷ እና ቤቲ ግን ፖላንድ ሆነው ምግብ ቤት ውስጥ ባገኙት ሥራ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወስነዋል። የቤተሰብ ድጋፍም አያስፈልገንም ትላለች ቤቲ። ሶስቱም የሚኖሩት አንድ ቤት ውስጥ ነው። « ከቤተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ይመጣል፤ ከዛ ሁሉም የሚያውቀውን የሰፈርም ሆነ ቤተሰብን ማምጣት ይጀምራል» ትላለች ቤቲ።  ወጣቶቹ በአሁኑ ሰዓት ፖላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ቁጥር በውል ባያውቁትም ብዙዎች ወደ ፖላንድ ለመሄድ የወሰኑበትን ምክንያት ግን ያውቃሉ። « ፕሮሰሱ  ከአሜሪካ፣ ከካናዳ እና ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር ስናስተያየው የፖላንድ ቀላል ነው» ይላል ቃል አብ። እሱም ምግብ ቤት ውስጥ ነው የሚሰራው።

ቤቲ የመጀመሪያ ሴሚስተር ፈተና ወስዳለች። ትምህርቱም እስካሁን «ቀላል የሚባል ነው» እንደሷ አገላለጽ። መጀመሪያ ላይ ግን ትንሽ ከብዷት እንደነበር አልሸሸገችም። « ኢትዮጵያ በኦላይን የሚሰጥ ትምህርትን ስለማናውቀው መጀመሪያ ላይ ይከብድ ነበር። » እስካሁን ትምህርት በኢንተርኔት ማለትም በኦንላይ መሆኑ ምሕረትን ጠቅሟታል። ሥራ ያገኘችበት ከተማ እና የምትማርበት ዮንቨርስቲ እንደሌሎቹ አንድ ከተማ ውስጥ አይደለም። ምሕረትም ትሁን ቤቲ ወደፊት እዛው ፖላንድ ውስጥ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ተምረው መያዝ ይፈልጋሉ። ቃለ አብ ደግሞ እስከ ዶክትሬት ዲግሪው ሊገፋበት ይፈልጋል «ከዚህ ወደተሻለ ዮንቨስቲ ወደ ብሪታንያ ሄጄ ብማር ደስ ይለኛል » ይላል። ሁሉም በአሁኑ ሰዓት የሚማሩት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ቢሆንም ለሥራቸው እንዲረዳቸው ፖላንድኛ መማር ጀምረዋል። 

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ