ለናይጄሪያ አገልግሎት የሚሰጠው ኢትዮጵያዊ ኩባንያ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:17 ደቂቃ
10.10.2018

አዲስ አበባ ተቀምጦ የናይጄሪያን ቴክኖሎጂ ማቀላጠፍ

በኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች በሀገሪቱ ያለውን የመንግስትን እና የግል ተቋማትን አሰራር ለማዘመን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ከሀገር ቤትም አልፈው በሌሎች ሀገራት ላሉ ተቋማት ጭምር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። አፖዚት የተሰኘው ኢትዮጵያዊ ኩባንያው ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።

ፓጋ የተሰኘው የናይጄሪያ የቴክኖሎጂ ድርጅት የተንቀሳቃሽ ስልክ የክፍያ ስርዓትን በሀገሪቱ ዘርግቶ ይንቀሳቀሳል። አስር ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉ ተጠቃሚዎች እንዳለው የሚናገረው ድርጅቱ የክፍያ አገልግሎቱን የሚያቀላጥፉለት 17 ሺህ 587 ወኪሎች አሉት። የእዚህ ሁሉ ሰው መረጃ ያለ እንከን በቅጽበት እንዲተላለፍ የሚያስችለውን ስርዓት የሚከታተሉት 25 የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች ናቸው። ባለሙያዎቹ ስራቸውን የሚከውኑት ሌጎስ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ሆነው አይደለም። ይልቁንም ወደ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር በሚጠጋ ርቀት ላይ በምትገኝ የሌላ ሀገር ዋና ከተማ ሆነው ነው። ያች ከተማ አዲስ አበባ ነች።

ባለሙያዎቹ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉበት ምክንያይ አፖዚት በተሰኘው ኢትዮጵያዊ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው። አፖዚት የናይጄሪያውን ድርጅት ቴክኒካዊ ስራዎች ተረክቦ በመስራት ላይ የሚገኝ ነው። ከ10 ዓመት በፊት የተመሰረተው አፖዚት ከናይጄሪያዊው ድርጅት ጋር በአማካሪነት ነበር ስራውን የጀመረው። ከአፖዚት መስራቾች አንዱ የሆኑት እና ኩባንያውን በዋና ስራ አስፈጻሚነት እየመሩ ያሉት አቶ አዳም አባተ አጀማመሩን ያስታውሳሉ።

አፖዚት ኩባንያ ካሉት ሃምሳ ሰራተኞች ግማሽ ያህሉ ለናይጄሪያው ስራ የተመደቡ እንደሆኑ አቶ አዳም ይናገራሉ። ከአንደኛው በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው። ከገንዘብ ስርዓት ጋር በተያያዙ ስራዎች ላይ የዓመታት ልምድ ያካበተው አፖዚት ተመሳሳይ አገልግሎቶችን ለመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ባንኮች እና የግል ድርጅቶች ሲሰጥ ቆይቷል። ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በዋናነት ከሚሰጣቸው ሶስት አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ ይሄው እንደሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚው ያስረዳሉ።   

ግብርና እና ቴክኖሎጂን የማጣመር ሙከራዎች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እየተተገበሩ ይገኛሉ። አፖዚት ከመንግስታዊው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር  በኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገው ደግሞ የግብርና ግብዓት ስርዓትን ነው።  የአፖዚት እና የግብርና ዘርፉ ቁርኝት የጀመረው ከኩባንያው ቀደምት ዓመታት አንስቶ ነው። ኩባንያው የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ግብይትን በከፍተኛ ሁኔታ አሻሽሏል በሚል በሚሞካሸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቴክኖሎጂ እመርታ ላይ አሻራውን ያኖረው የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ግድም ነበር። አፖዚት ለምርት ገበያ የዘረጋውን ስርዓት አቶ አዳም “በሀገሪቱ ከዚያ ቀደም ያልተተገበረ ነው” ይሉታል። 

አፖዚት ኩባንያ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሰራው ስርዓት ለቀጣይ ስራዎቹም እርሾ ሆኖ እንዳገለገለ አቶ አዳም ይናገራሉ። ለናይጄሪያው ድርጅት የተሰራው የተንቀሳቃሽ ስልክ የክፍያ ስርዓትም ከዚያ የተዋሰው ግብዓት እንዳለ ይገልጻሉ። አዳም የኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማት የሚገለገሉባቸውን ስርዓቶች የመዘርጋቱን ስራ የተቀላቀሉት ገና የራሳቸውን ኩባንያ እንኳ ሳይመሰርቱ ነው። ነገሩ የሚጀምረው የዛሬ አስራ አምስት አመት ግድም የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ከተከታተሉበት እና ይኖሩበት ከነበረው አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ነው።

አቶ አዳም ከአሜሪካ እንደተመለሱ በገንዘብ ሚኒስቴር ለአራት ዓመታት ሰርተዋል። በቆይታቸው አብረዋቸው አፖዚት ኩባንያን ከመሰረቱት ኢትዮጵያዊው አቶ ስምዖን ሰለሞን እና ናይጄሪያው ኤሪክ ቺጂዮኬ ጋር የመስራት ዕድል ገጥሟቸዋል። እንደውም በዩኒቨርስቲ ጭምር የሚያወቁትን ኤሪክን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያስደረጉት እርሳቸው ናቸው።

በአሜሪካ ስርዓት ውስጥ የተማሩት እና የሰሩት እኒህ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት እንኳ በሌለባት ኢትዮጵያ ውስጥ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ለማቋቋም እንዴት ደፈሩ? ያለፉት ዓመታት ተሞክሮዎቻቸውስ ምን አመላከቷቸው? ወደ ናይጄሪያ በመሻገር አገልግሎት እየሰጠ ያለው አፖዚት ኩባንያ ወደፊት ስራዎቹን ወደ ሌሎች ሀገራት የመስፋት ዕቅድ አለው ወይስ በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ረገድ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ይጥራል? የአፖዚት ዋና ስራ አስፈጻሚ ምላሽ አላቸው።

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።  

ተስፋለም ወልደየስ 

አርያም ተክሌ 

ተከታተሉን