1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአየር ንብረት ለዉጥ ተጠያቂ ማነዉ?

ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 2005

የዓለም የአየር ንብረት ለዉጥ መንስኤዎች ዛሬም እያከራከሩ ቢሆንም የምድራችን የአየር ጠባይ መለዋወጥ መቀጠሉን የሰሞኑ ክስተቶች ያመላክታሉ። አሜሪካን ኦክላሆማን ደጋግሞ ኃይለኛ ንፋስ ያገዘዉ ዉሽንፍር ሲገርፍ ደቡብና ምስራቅ ጀርመንም የወረደዉ ዝናብ ጎርፍ አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/18jh8
ምስል Reuters

አንዳንድ የምርምር ጽሑፎች ምድራችን ከጎርጎሮሳዊዉ 1998ዓ,ም ወዲህ የሙቀት መጠኗ ሳይጨምር መቆየቱን ያመለክታሉ። በዚህ ዓመት ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት አጋጣሚ መኖሩን ይጠቁሙና መንስኤዉ ግን የኤሊኞ ክስተት እንደሆነ ነዉ ይገልጻሉ። ከተጠቀሰዉ ዓመት ወዲህ የሙቀት መጠኑ ዝቅ እያለ ሄዷል የሚለዉን መከራከሪያ የማይቀበሉት ወገኖች ይህ ማነፃፀሪያ ሳይንሱን እንዳያዛባ ስጋታቸዉን ነዉ የሚገልፁት። በስዊዘርላንድ የበርን ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ ዑርዝ ኖይ «የክረምቱ ሙቀት ከበጋዉ ሲነፃፀር እጅግ ፈጥኖ የመቀዝቀዝ ሂደት ነዉ የሚያሳየዉ። ይህን የሚያስተዉል ደግሞ ለዚህ የሚያበቁትን በርካታ ምክንያቶች ከግምት ማስገባት ይኖርበታል። ለምሳሌ አንደኛዉ ተፈጥሮ ነዉ።» እዚህ ላይ ይላሉ ኖይ፤ የእሳተ ጎሞራ መፈንዳት ወይም ኤሊኞም ሆነ ላኒኛን እንደምክንያትነት መጥቀስ ትርጉም አይኖረዉም። ኤሊኞ በምድር ወገብ አካባቢ የሚገኘዉ ፓስፊክ ዉቅያኖስ ከወትሮ የበለጠ ሙቀት ሲኖረዉ ሲሆን ላኒኛ ደግሞ በተቃራኒዉ ያልተለመደ ዓይነት ቅዝቃዜ ሲከሰት እንደሚችልም ያመለክታሉ ተመራማሪዋ። በዚህ አካባቢ የሚታየዉ የሙቀት መጠን መለዋወጥ የዓለማችን የአየር ጠባይ እንዲቀያየር ምክንያት እንደሚሆንም ይታመናል። እሳቸዉ እንደሚሉትም ለምሳሌ ኤሊኞ ፔሩ ላይ ከባድ ዝናብ ሲያስከትል አዉስትራሊያ ደግሞ የከፋ ድርቅ ይከሰታል። እነዚህን መንስኤዎች የሚያስተዉልም የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ቀጣይነቱን ልብ እንደሚል ኖይ ያመለክታሉ።

Feld in Indien
ምስል CC/Peter Blanchard

ይህን ትንታኔ የሚተቹት ታዲያ ያለፈዉን የሰሜናዊ ንፍቀ ክበብን የክረምትና የበረዶ ወራት በማጣቀስም ረዥም የክረምት ወቅት፤ ቀዝቃዛ የበጋ ወራት እያስተናገድን የቱ ጋ ነዉ የዓለም የሙቀት መጠን የሚታየዉ ሲሉ ይሞግታሉ። በእነሱ እምነትም የሙቀት መጠኑ እየቀነሰ ነዉ። የጀርመን የአየር ንብረት ትንበያ የመዘገበዉ ሪከርድ የክረምቱ የሙቀት መጠን ለሩብ ምዕተ ዓመት ከነበረዉ በአማካኝ በሁለት ዲግሪ መቀነሱን ማመላከቱም የዓለም የሙቀት መጠን እየቀነሰ ለመሄዱ እንደማሳያም ይጠቅሳሉ። ስለአየር ንብረት የሚመራመሩ ወገኖች በአንፃሩ እነዚህ ሁኔታዎች የግድ ከዓለም የሙቀት መጨመር ጋ ይገናኛሉ የሚለዉን አይቀበሉም። በአልፍሬድ ዋግነር ተቋም የዋልታዎችና የባህርን ይዞታዎች የሚመረምሩት ክላዉስ ዴቶልፍ ምዘናዉ አንድ አካባቢ ላይ ብቻ ያተኮረ ከሆነ የሚደረስበትን ድምዳሜ እንደሚያዛባዉ ነዉ የሚያሳስቡት። ለምሳሌ በበጋ የአርክቲክ በረዶ ሲቀነስ በክረምት የማዕከላዊ አዉሮጳና የእስያ ክረምት ጠንካራ ቅዝቃዜ እንደሚኖረዉ በተከታታይ የተመዘገበበት ሁኔታ መኖሩን በማመልከት፤ ይህ በአንድ ወገን ሚዛን የሠራ ቢመስልም በተቃራኒዉ ረዥም ክረምትም ሆነ ቀዝቃዛ የበጋ ወቅት እየታየም የሙቀት መጠን እየጨመረ መሄዱ እየታየ እንደሆነ ያመለክታሉ።

የሙቀት መጠን አለመጨመሩን ለማስረዳት የሚጥሩት ወገኖች ለማሳየት የሚሞክሩት ሰዎች ወደከባቢ አየር ካርቦን ዳይኦክሳይድ በመስደዳቸዉ የበከሉት ነገር የለም ለሚለዉን አቋማቸዉን በመረጃ ለማጠናከር ይመስላል። የዛሬ 420 ሺህ ዓመታት ክስተቶችን በማጣቀስም ለሙቀቱ መጨመር የሰዉ ልጅ ተጠያቂ እንዳልሆነ የሚሞግቱም አሉ።

እነዚህ ወገኖች ካርቦን ዳይኦክሳይድ ጉዳት አያደርስም እንደዉም ተፈጥሮ ይፈልገዋል ሲሉም ሙግታቸዉን ያስፋፋሉ። በተቃራኒዉ ወገን ያሉት ተመራማሪዎችም ይህን አይቃረኑም፤ ተክሎች ምግባቸዉን ለመስራት CO2 ይፈልጋሉና። ዑርዝ ኖይ እንደሚሉትም ለዚህ ተፈጥሮ የራሷ ሚዛን አላት። ክምችቱ ከመጠን በላይ በሚሆንበት ጊዜ ግን ሌላ መዘዝ ይኖረዋል። ለምሳሌ ይላሉ ኖይ፤ «ይህን በገላ መታጠቢያ ገንዳ ማነፃፀር ይቻላል፤ ገንዳዉ ዉስጥ በበቂ ሁኔታ ከቧምቧዉ ዉሃ እንዲፈስ ቢደረግ መልካም ይሆናል፤ ነገር ግን የቧምቧዉን ኃይል ጨምረን ዉሃዉ በኃይል ቢወርድ ጥቂት ቆይቶ ከገንዳዉ ዉጭ ለመፍሰስ ይገደዳል።» ሲሉ ጉዳቱን ለማስረዳት ይጥራሉ።

Rauchende Schornsteine
ምስል CC/Quinn Dombrowski

ምሑራኑን የአየር ንብረት ለዉጥ መንስኤ ሲያነጋግር ከጸደይ ወደበጋ የተሸጋገረዉ የሰሜኑ ንፍቀክበብ ከአትላንቲክ ማዶ ኃይለኛ ንፋስ እና ዝናብ፤ ከወዲህ ማዕከላዊ አዉሮጳ ዉስጥ ደግሞ ጎርፍ ለህይወት እና ንብረት ጥፋት ምክንያት ሆነዋል። ምስራቅና ደቡብ ጀርመንን ጨምሮ ቼክ ሪፑብሊክ፤ ኦስትሪያ፤ ስሎቬኪያ፤ ሃንጋሪ እና ፖላንድ ክሳምንቱ መጨረሻ አንስቶ በዉሃ ሙላት ተጨንቀዋል። ከአስርት ዓመታት ወዲህ የከፋ መሆኑ የተነገረለት ጎርፍ እስከትናንት ቼክ ዉስጥ ከአምስት በላይ፤ ኦስትሪያ ደግሞ የአንድ ሰዉ ህይወት አሳጥቷል፤ ሶስት ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም። ቼክ ዋና ከተማ ፕራግ አገር ጎብኚዎች የሚያዘወትሩት በ14ኛዉ ክፍለ ዘመን እንደተሠራ የሚነገርለት ቻርለስ ድልድይ መተላለፊያዉ እንዲዘጋ አስገድዶ፤ አካባቢዉ በዉሃ ተጥለቅልቆ ዛፎች በደፈረሰዉ ቡናማ ጎርፎ ግማሽ በግማሽ ተዉጠዉ ቅጠሎቻቸዉ ሲንሳፈፍ ታይቷል። የሁለቱ ሰዎች ህይወት ያለፈዉ ለበጋ ወቅት የሚዝናኑበት ጎጆ ቤት በጎርፍ ተደርምሶ ነዉ። በሰሜን ምዕራብ ኦስትሪያ መሬት በመንሸራተቱ የባቡር መስመሮች የተሰናከሉ ሲሆን ዉሃዉ ስዊዘርላንድም እንደሚያሰጋ ተገምምቷል። 

 የሙቀቱ መጠን ከፍ ይላል ተብሎ በተጠበቀበት በሳምንቱ መጨረሻ በደቡብና ምስራቅ የጀርመን ግዛቶች የጣለዉ ዝናብ ከጀርመን ተነስቶ ኦስትሪያ ስሎቫኪያ እና ሃንጋሪን አዳርሶ ጥቁር ባህር የሚገባዉ ጀርመኖች ዶናዉ የሚሉት ዳኒዩብ ወንዝ መጠኑ በጣም መጨመሩ ተገልጿል። ቼክ ሪፑብሊክና ኦስትሪያ ወንዙ በሚያልፍባቸዉ ቦታዎች የሚኖሩ ወገኖች አካባቢዉን እንዲለቁ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ፤ ሃንጋሪ በበኩሏ ወደ አራት መቶ ሰዎችን አሰማርታ ውሐዉ ከመስመሩ እንዳያልፍ ጆንያ በተሞሉ ጆንያዎች ግድብ እያሰራች ነዉ። 

Hochwasser Deutschland Flut Überschwemmung Katastrophe
ጎርፍ በጀርመንምስል Reuters

ሶስት ወንዞች የሚገናኙባት የጀርመን የድንበር ከተማ ፓሳዉ እሁድ በዉሃ ተጥለቅልቃ ነዉ የዋለችዉ። ከአንድ ቀን በፊት ደረቅ የነበሩት ጎዳናዎችዋ እሁድ ጉልበት ድረስ በሚያጠልቅ ዉሃ ተዉጠዉ ለተመለከታቸዉ ዉሃዉ ከየት መጣ የሚለዉ ግራ አጋቢ ነበር።

ከኗሪዎች አብዛኞቹ ከመሬት ስር የሚገኝ ምድር ቤታቸዉን ጨምሮ ቀጣይ ክፍሎች በዉሃዉ በመጥለቅለቃቸዉ ከላይ የሚገኙትን ለማድረቅና ቅዝቃዜዉን ለመቀነስ ሲታገሉ ዉለዋል። ነጋዴዎችና የሆቴል ባለቤቶች ከዉሃዉ ለማዳን የሚችሉትን ለማትረፍ ሲዋከቡ ቢታይም አብዛኞቹ አስቀድሞ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ባለመኖሩ ከፍተኛ ቅሬታ አድሮባቸዋል። እንዲያም ሆኖ የሚችሉትን ለማድረግ መሞከራቸዉን  በከተማዋ የሆቴል ኃላፊ የሆኑት ዛብሪና ብሮግሊ የሚናገሩት፤

«መደበኛ የሆነ የዉሃ ሙላት ቢመጣ ሰዉ ምንድነዉ ብሎ ሊቀልድ ይችላል፤ አሁን ያለዉ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለዉን ግን እኔ እንደማምነዉ ነገር የነፍስ አድን ሠራተኞችም ሆኑ ኗሪዎች ሊገምቱ የሚችሉ አይመስልም። አዎ እኛ የምንችለዉን ሁሉ በተቻለ መጠን አድርገናል፤ ሠራተኞች ሁሉ በትጋት የሚገባቸዉን ሁሉ አድርገዋል፤ ከእንግዲህ የሚደርሰዉን ከመጠበቅ በቀር የምናደርገዉ አይኖርም።»

የከተማዋ ከንቲባ ሳይጠበቅ የተከሰተዉን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የመከላከያ ዘርፉን ድጋፍ መጠየቃቸዉን ነዉ የተናገሩት፤

Hochwasser Politiker Hochwasser Politiker Platzeck Merkel
ምስል Getty Images

«ሳይጠበቅ በተከሰተዉ አደጋ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዉጀናል። ከጎርፉ አደጋ አካባቢዉን ለመታደግምት የጦር ኃይሉን ድጋፍም ጠይቀናል።»

በባየርን /ባቫሪያ ግዛት ከተሞች ሮዘንሃይም አቅራቢያ የሚገኝ ግድብን የሰበረዉ ጎርፍ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ለቀጣይ ስራቸዉ እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት መሆኑ ተገልጿል። በምስራቃዊ ጀርመን ከተሞችም ከአስር ዓመታት በፊት የደረሰዉን የጎርፍ አደጋ በማስታወስ ኗሪዎች ስጋት ገብቷቸዋል። ብዙዎቹ ይዞታዉ ለህይወት እንደሚያሰጋ የገለፁ ሲሆን ባለስልጣናት ሰዎች ቤታቸዉን ትተዉ ወደሌላ አካባቢ እንዲሄዱ እያሳሰቡ ነዉ። ከኗሪዎቹ አንዷ

«ከተማዉን ለቅቀን መዉጣት ይኖርብናል፤ ባለስልጣናት መሃል ከተማዋ ጭምር ልትጥለቀለቅ እንደምትችል ገምተዋል፤ እናም ከመጀመሪያዉ እንደተገመተዉ አስከፊ ሊሆን ይችላል።»

ሰኞ ዕለትም እንደሚቀጥል በተገመተዉ ዝናብ ምክንያትም ዶናዉ ብቻ ሳይሆን ከጀርመን ወደሌሎች የአዉሮጳ አገራት የሚጓዘዉ ራይን ወንዝም እንዲሁ ለወትሮ የሚሰጡትን የእቃ ማጓጓዝ ተግባር ለጊዜዉ ገትተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ