1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል የሚሰጠው ድጋፍ

sdestaዓርብ፣ ነሐሴ 28 1996

በምዕራባዊ ሱዳን ክፍለሃገር በዳርፉር የተፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ ለማስቆም እና ሰላም ለማረጋጋት የአፍሪካ ህብረት ተጨማሪ ኃይል ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው ። ሆኖም ህብረቱ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ከማዋጣት ባሻገር የስንቅ እና ትጥቅ እንዲሁም የመጓጓዣ አገልግሎትን ለማሟላት አቅም የለውም ። በመሆኑም የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን ለህብረቱ ብቻ እየተወ መሆኑ የተተቸው ዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ህብረቱን በገንዘብ እና በቁሳቁስ እንዲረዳ ተጠይቋል ። በሱዳ

https://p.dw.com/p/E0kt

� የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዑክ ዣን ፕሮንክ ደግሞ የዳርፉር ሰብአዊ ቀውስ መሻሻል ቢታይበትም ግድያና ስደት አሁንም ቀጥሏል ይላሉ ።

ፕሮንክ ግድያና ስደት እንዳለ ቢገልፁም ትናንት ለፀጥታው ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት የሱዳን መንግስት ከፀጥታው ምክር ቤት የተጣለበትን ግዴታ ለመወጣት ጥረት ማድረጉን አልሸሽጉም ። ተጨማሪ የፀጥታ ሃይል በማሰማራት እና ሰብአዊ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በአካባቢው እንዳይንቀሳቀሱ ጥሎት የነበረውን ገደብ በማንሳት ተመስጋኝ ተግባር ፈፅሟል ። ግን በዳርፉር ችግር ዙሪያ ለሁለት መሰረታዊ ችግሮች መፍትሄ አልፈለገላቸውም ። እንደ ፕሮንክ ዘገባ በዳርፉር አሁንም ሰላማዊ ዜጎች ይገደላሉ ። መንግስት ወንጀል የሰሩትን ግለሰቦች እና ቡድናት ወደ ህግ ለማምጣት ግዴለሽ ሆኗል ።

የፀጥታው ምክር ቤት ከወር በፊት ባሳለፈው ውሳኔ የሱዳን መንግስት እነዚህን ሃላፊነቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲወጣ የጊዜ ገደብ ሰጥቶ ነበር ። ሰሞኑን እና ትናንት የተሰበሰበው ምክር ቤት ግን ሱዳን ኃላፊነቷን አልተወጣችም ማዕቀብ ይጣልባት ለማለት ተስኖታል ። ከምክር ቤቱ አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚገልፁት በጉዳዩ ላይ የተከፋፈለ አቋም እየተንፀባረቀ ነው ። በሱዳን የንግድ እና የምጣኔ ሃብት ፍላጎታቸውን ላለማጣት ሲሉ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት ሩሲያና ቻይና በሱዳን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አይፈልጉም ። እናም የፀጥታው ምክር ቤት አሁን የሚከተለው አካሄድ ሱዳን ላይ ጫና መፍጠር ሳይሆን የዳርፉርን ቀውስ ለማስወገድ የአፍሪካ ህብረት ሃላፊነቱን እንዲወስድ ነው ።

ህብረቱም ቢሆን አሁን ካሰማራው ሶስት መቶ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ሌላ ተጨማሪ ኃይል ለመላክ እቅድና ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ገልጿል ። ናይጀሪያ ፣ ቦትስዋና እና ታንዛኒያ ወታደሮችን ለመላክ ፤ ደቡብ አፍሪካ ስንቅና ትትቅ ለማቅረብ ቃል ከገቡት ሃገራት ውስጥ ይገኙበታል ። ሆኖም እነዚህና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ወታደሮቻቸውን ሊልኩ ቢችሉም የወታደሮቻቸውን ወጪ የመሸፈን አቅም የላቸውም ። የአፍሪካ ህብረት ከእነዚህ ችግሮች ጋር ሰላም እንዲያስከብር ሃላፊነት መስጠቱ የፀጥታውን ምክር ቤት ውሳኔ የይስሙላ ያደርገዋል የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው ። ፅህፈት ቤቱ ዋሽንግተን የሆነው ‘’ አፍሪካ አክሽን ‘’ የተባለው ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሳሊህ ቡከር የፀጥታው ምክር ቤት እና የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የዳርፉርን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቆም ሃላፊነቱን ለአፍሪካ ህብረት በመስጠት ይወጣው ብሎ እጁን ማጣጠፉ ለጊዜው ከሃላፊነት ለመዳን ይቻላል ይላሉ ። ለዚህ ይቻላል የምፀት አባባላቸው የተናገሩት በዳርፉር ምንም ዓይነት ችግር ቢደርስ አሳሳቢ አይደለም ። ምክንያቱም ክፍለ ዓለሙ አፍሪካ ነውና በማለት ነበር ።

‘’ የትራንስ አፍሪካ ፎረም ‘’ ፕሬዝዳንት ቢል ፍሊቸር ይህንን የቡከር ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል ። እንደሳቸው እምነት የፀጥታው ምክር ቤት እና የተባበሩት መንግስታት አባል ሃገራት የሱዳን ዳርፉር ችግርን ለማስወገድ ቸልተኝነት ማሳየታቸው በሶስት ምክንያቶች ነው ። በአንድ ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እየተበረታታ እንዳይሄድ የሚለው አንደኛው ስጋት ሆኖ ተጠቅሷል ። በሱዳን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የነዳጅ እና የሌሎች የተፈጥሮ ሃብቷን የመቀራመት ዕድል ሊፈጠር ይችላል የሚል ሰበብ የሚሰጡ ሃገራት መኖራቸው ደግሞ ሁለተኛው ምክንያት ነው ። በሶስተኛው ምክንያት ለዳርፉር የሰላም ዘመቻ ተልዕኮ በቂ ገንዘብ ሊኖር አይችልም የሚል እምነት አለ ። ፊሊቸር እንደሚሉት ለዳርፉር ቀውስ መፍትሄ መፈለግ ያለበት የአፍሪካ ህብረት ተነሳሽነት ነው ። የምዕራባውያኑ ጣልቃ ገብነት ጥፋትን ያስከትላል ። ዩናይትድስቴትስ እና የአውሮጳ ህብረት የገንዘብ እና የሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ መስጠት ይችላሉ ። በአስቸኳይም መስጠት አለባቸው ብለዋል ።

ዩናይትድስቴትስ እና የአውሮጳ ህብረት የራሱን ችግር በራሱ ለመፍታት ለተነሳሳው የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ እንዲሰጡ የሚጠይቁ ወገኖች ጥቂት አይደሉም ። በምፅሃረ ቃል ‘’ ዩስ ኢዩ ኮም ‘’ በመባል የሚታወቀው የዩናይትድስቴትስ እና የአውሮጳ ጥምር እዝ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይላትን ለማጓጓዝ የአይሮፕላን እና ከአይሮፕላን ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን ለመስጠት ቃል ገብቷል ። ይህ ብቻ በቂ አይደለም የሚሉት ወገኖች ከልምድ ተነስተው እንደሚገልፁት በሰላም ማስከበር ተግባር ወታደሮቻቸውን የሚያሰማሩ የአፍሪካ ሃገራት ለሰራዊታቸው የሚከፈልት ደሞዝ እየታጣ ችግር ሲከተል ቆይቷል ። በመሆኑ ዩናይትድስቴትስ እና የአውሮጳ ህብረት የሚሰጡት ድጋፍ ውጤታማ እንዲሆን በርዳታ ስሌታቸው ገንዘብን ሊጨምሩ ይገባል ።