1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን በሚደግፍ ሰልፍ ላይ ድምጻዊ ታሪኩ "ሽምግልና ይሻላል" ብሏል

እሑድ፣ ጥቅምት 28 2014

ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማሳየት በተካሔደ ሰልፍ ድምጻዊ ታሪኩ ጋንካሲ "ሽምግልና ይሻላል" የሚል ጥሪ አቀረበ። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታዳሚ በተገኘበት ሰልፍ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "እንነሳ፤ የመከላከያ ሠራዊታችንን እንቀላቀላቸው፤ አብረናቸው እንቁም" የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/42h86
Ätopien | Unterstützer des Premierministers feiern
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ኃይሎች ለገጠመው ውጊያ ድጋፍ ለማሳየት በተጠራ ሰልፍ ላይ ድማጻዊ ታሪኩ ጋንካሲ ውጊያ ቆሞ ሽምግልና እንዲጀመር ጥሪ አቀረበ። በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በዛሬው ዕለት በተካሔደው እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታዳሚ በተገኘበት ሰልፍ ላይ ህወሓት እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት "ሸኔ" እያሉ የሚጠሩትን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ተወግዘዋል። 

"አገሬን እጠብቃለሁ መስዋዕትነት እከፍላለሁ” በሚል የተካሔደው ሰልፍ ታዳሚዎች "ኢትዮጵያ በውክልና ጦርነት አትንበረከክም" እንዲሁም "ኢትዮጵያ የማትሰምጥ መርከብ ነች" የሚሉ መፈክሮች ይዘው ታይተዋል። 

የሰልፉ ተሳታፊዎች እና በመድረኩ ንግግር ያደረጉ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ መንግሥት ውጊያ ከገጠመው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ እና ባለሥልጣናቱ "ሸኔ" እያሉ ከሚጠሩት የኦሮሞ ነጻነት ጦር በተጨማሪ ምዕራባውያን አገራት ላይ ብርቱ ትችት ሰንዝረዋል። 

"ኢትዮጵያ በእኛ በልጆቿ ክንድ ታሸንፋለች" የሚል መፈክር ከፍ ብሎ በተጻፈበት መድረክ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "እኛ ነን የዴሞክራሲ ደቀ-መዛሙርት" ይላሉ ያሏቸው አገሮች ኢትዮጵያውያን "በዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠቅመው መንግሥታቸውን ሲመርጡ ´እኛ እውቅና ካልሰጠነው መንግሥት መሆን አይችልም። እኛ አሻንጉሊት እናስቀምጥላችሁ` ብለው ምኞታቸውን እያሳዩን ነው" ሲሉ ተደምጠዋል። 

Ätopien | Unterstützer des Premierministers feiern
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

ከንቲባዋ "ሚዲያዎቻቸውን አዝመተውብናል። ለአንድ አመት ሳይታክቱ የኢትዮጵያን ስም በማጠልሸት ´ያልተደረገውን ተደረገ` እያሉ ዓለም እንዲያድምብን ወትውተዋል" ሲሉ በንግግራቸው ከሰዋል። ከንቲባዋ በንግግራቸው በስም የጠቀሱት አገርም ሆነ የብዙኃን መገናኛ ተቋም አልነበረም። 

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በመፈክሮቻቸው ከተቿቸው መካከል አሜሪካ እና የብሪታኒያው ብዙኃን መገናኛ ቢቢሲ ይገኙበታል። ሰሞኑን አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ኬንያ በኢትዮጵያ ውጊያ ቆሞ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በተከታታይ ጥሪ አቅርበዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሰላማዊ ሰልፉ ታዳሚዎች "እንነሳ፤ የመከላከያ ሠራዊታችንን እንቀላቀላቸው፤ አብረናቸው እንቁም" የሚል ጥሪ አቅርበዋል። አዳነች "ለአገራችን ነጻነት ነገ ዛሬ ሳንል አሁኑኑ እንዝመት፤ አጥፊዎች ምንም አይነት መፈናፈኛ እንዳያገኙ አድርገን መውጪያ መግቢያ እናሳጣቸው" ብለዋል። 

በመድረኩ አስተናባሪዎች የተጋበዘው ድምጻዊ ታሪኩ ጋንካሲ "እኔ አልዘፍንም። የመጣሁት ልዘፍን አይደለም" ሲል ተደምጧል። "በደስታውም በሐዘኑም መዝፈን ብቻ ነው እንዴ?" የሚል ጥያቄ ያቀረበው ድምጻዊው "እኔም እራሴ የሚዘፈንበት እና የማይዘፈንበት ቀን ልወቃ" በማለት ተናግሯል።

Ätopien | Unterstützer des Premierministers feiern
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

"የቱ ጋ ቆሜ ልዝፈን? የቱጋ ቆሜ ልዘምር? የቱጋ ቆሜ ልናገር? እኔ የምዘፍነውም የለም። የምናገረውም የለም" እያለ በሰልፉ ከተንጸባረቀው ለየት ያለ አስተያየት ሰጥቷል። "በዘፈኑም ካልተማርን፤ በመዝሙሩም ካልተማርን አሁን የሚዘፈን ነገር የለም። የሚዘመርም ነገር የለም። በመዝሙሩም አልተማርንም። በቤተ-ክርስቲያን በሚያስተምሩ በቄሶችም አልተማርንም። በፕሮቴስታንት በሐይማኖት አባቶች፤ ፓስተሮች የሚያስተምሩንን ካልተማርን፤ በሙስሊሞች የሚያስተምሩንን ካልተማርን ዘፈኑም አያስተምረንም" ያለው ታሪኩ "ምን አለ ብዬ ነው የምዘምረው?" እያለ በመጠየቅ ጠንከር ያለ ትችት አቅርቧል። 

"ሁሌ ጥቁር መልበስ አያምርብንም። ጥቁር መልበስ ይበቃል፤ ጆሯችን ደማ" ያለው ታሪኩ ድምጹን ከፍ አድርጎ "ይበቃል" ሲል ተደምጧል። "ማን መጥቶ ነው የሚናገረን? ማን ነው እየሔደ እየሞተ ያለው? ለምንድነው ለመሞት ብቻ ወደ ፊት የምንለው?" የሚሉ ጥያቄዎች አቅርቦ "አሁን ወጣቶቹ ይቁሙ አይሒዱ። ሽማግሌዎቹ ይሒዱ፤ ድንጋይ ያንሱና ሳር ይበጥሱ...በሽምግልና ይሻላል። አፈሙዙ ይበቃል። መፍትሔ የለውም" በማለት ድምጹን ከፍ አድርጎ ጥሪ አቅርቧል። 

Äthiopien | Musiker Tariku Gankise
ድምጻዊ ታሪኩ ጋንካሲምስል Privat

"ደም አላስተማረንም። ጉልበት አላስተማረንም" ያለው ታሪኩ በ"ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር የሁሉም ደሙ ትኩስ ነው" በማለት ንግግሩን አሳርጓል። በመድረኩ ባለሥልጣናት ያደረጓቸው ንግግሮችም ሆነ አስተናባሪዎቹ ያሰሟቸው መፈክሮች ድምጻዊ ታሪኩ ጋንካሲ ካቀረበው ጥሪ የተለዩ ሆነው ታይተዋል። 

የመድረኩ አስተናባሪዎች ካሰሟቸው መፈክሮች መካከል "ኢትዮጵያ በፈተና በሚጸኑ አሸናፊ ልጆቿ የምንጊዜም ጠላቶቿን እስከ ወዲያኛው ትደመስሳለች፤ ነጻነቷም ይረጋገጣል" የሚል ይገኝበታል። 

የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበበ ባሰሙት ንግግር "የፖለቲካ ልዩነት ከሀገር በታች ነው። ሀገር ከማንም በላይ ናት" ብለዋል። "ባገራችን ከውስጣችን የወጡ የውክልና ጦርነት የሚያካሒዱ፤ ለወራሪ እና ለባንዳ በአባዜነት የተለከፉ መርከብ የሆነችውን አገራችንን ለማተራመስ ቢሞክሩም በተባበረ ክንዳችን እንደቁሳቸዋለን" ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ተደምጠዋል።