1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የምግብ ርዳታ ማስፈለጉ

Eshete Bekeleማክሰኞ፣ ነሐሴ 19 2007

በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች አስታወቁ። ችግሩን ለመቅረፍ በተጨማሪ ከ230 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰቱትን ችግሮች ለመቅረፍ እየሠራሁ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/1GLPr
Dürre ohne Ende Am Horn von Afrika droht Hungersnot
ምስል picture-alliance/dpa

[No title]

የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀድሞ ከተተነበየው በ1.5 ሚሊዮን መጨመሩን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ። ኢትዮጵያ የምግብ እገዛ የሚፈልጉ 4.5 ሚሊዮን ዜጎችን ለመመገብ ተጨማሪ የ230 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ከለጋሾች ትፈልጋለች ተብሏል።

96 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ብታስመዘግብም በበልግ ዝናብ እጥረት ምክንያት በምግብ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ቀውስ መፈጠሩን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚገኙት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ፤ የዓለም ምግብ ድርጅትና የዓለም ህጻናት ድርጅት አስታውቀዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታዎች አስተባባሪ ቢሮ ሃላፊ ዴቪድ ዴል ኮንቴ የዝናብ እጥረቱ የኢትዮጵያ አየር ትንበያ ባለስልጣን ከጠቆመዉ የከፋ መሆኑን መናገራቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Dürre – Äthiopien
ምስል European Commission DG ECHO / CC BY-SA 2.0

የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን ቁጥር መረጃ የለኝም ያሉት በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ መንግስት የዝናብ እጥረቱን ተጽዕኖ ለመቀነስ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን በተከሰተው የዝናብ እጥረት በኢትዮጵያ ትርፍ ምርት በማምረት የሚታወቁ እንደ መካከለኛው ኦሮሚያ ያሉ አካባቢዎች ጭምር መጠቃታቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች በጋራ ያወጡት መግለጫ አውስቷል። በምስራቅና ምዕራብ አርሲ የምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም ሰሜን ሸዋ ማግኘት የሚገባቸውን የክረምት ዝናብ ባለማግኘታቸው በእርሻ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ተፈጥሯል ተብሏል። የዝናብ እረቱ በእንስሳት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖም አሳሳቢ እንደሆነ መግለጫው አትቷል። አቶ አለማየሁ ብርሃኑ መንግስት የመኖ እና የመጠጥ ውሃ እጥረት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የእንስሳት ሃብት ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል እየሠራ ነዉ ይላሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዝናብ እጥረቱ እስከ መስከረም ሊዘልቅ እንደሚችል አስጠንቅቋል። ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች 2.9 ሚሊዮን ተገምቶ የነበረ ሲሆን በአሁኑ መረጃ መሠረት ቁጥሩ 55 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። መግለጫውን ያወጡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት በዝናብ መታጣት ምክንያት የተከሰተው የምግብ እጥረት የከፋ ችግር ከማስከተሉ በፊት ለጋሽ አገራት አፋጣኝ እገዛ ማድረግ አለባቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ በግብርና ላይ ጥገኛ ሲሆን ከ50 በመቶ በላይ አገራዊ ምርትም ከዚሁ ዘርፍ የሚገኝ ነው። ከአገሪቱ ህዝብ ሶስት አራተኛው ገበሬ ሲሆን አብዛኛው ዝናብን መሠረት ባደረገ አነስተኛ የእርሻ ሥራዎች ወይም የእንስሳት እርባታ ላይ የተሠማራ ነው።

Äthiopien Landschaft in Provinz Afar Kamele durch die Wüste
ምስል picture-alliance/dpa

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 39 በመቶ የነበረው የድህነት ምጣኔ ወደ 26 በመቶ ዝቅ ቢልም አሁንም ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ገቢያቸው ከ1.25 ዶላር በታች እንደሆነ ይገልጻል። በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት እስከ ሰኔ ወር 9.5 በመቶ እድገት ሲያሳይ የነበረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጎርጎሮሳዊው 2015-2016 ወደ 10.5 በመቶ ከፍ ሊል ይችላል ተብሏል። የኢኮኖሚ እድገቱ እንደ አሁኑ ለሚከሰት የዝናብ እጥረትና ድርቅን ተከትሎ ለሚመጣ የምግብ እጦት መፍትሄ የመፍጠሩ ጉዳይ ግን አሁንም አነጋጋሪ ነው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ