1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለእናቶች ምርጥ ስፍራዎች

ማክሰኞ፣ ግንቦት 7 2004

እናቶች በሚያገኟቸዉ የጤና፤ የተመጣጠነ ምግብ፤ የትምህርት፤ የኤኮኖሚ ይዞታና እንዲሁም ለልጆች ጤና የሚሰጠዉን መሠረታዊ አገልግሎት ተመርኩዞ የሚኖሩባቸዉ ሀገሮች በየዓመቱ ደረጃ ወጥቶላቸዉ ምርጥና የከፉ በሚል ይፈረጃሉ። የዘንድሮዉን ምርጥ

https://p.dw.com/p/14w54
ምስል picture-alliance/dpa

የእናቶች መኖሪያነትን ክብር ኖርዌይ ስትይዝ፤ በተቃራኒዉ ኒዠር ለእናቶች መኖሪያነት እጅግ የከፋችዉ አገር ተብላለች። ለየሚኖሩበት ማኅበረሰብ እናቶች ጤናማና በእዉቀት የታነፀ ትዉልድ በማፍራት ትልቅ ሚና አላቸዉ። ዓመት ዞረዉ ቀን ቆርጠዉ የእናቶችን ዕለት በወጉ የሚያስቡና የሚከብሩት ወገኖችም የዝክራቸዉ ዋነኛ መንስኤ ከሆኑት አንዱ ይኽ መሆኑን ይገልፃሉ። ዕለቱ የሚታሰብባቸዉና ደምቆ የሚዉልባቸዉ ባህሎች የመኖራቸዉን ያህል በአንፃሩ ትዉስ የማይልባቸዉ አልጠፉም። ጤና ይስጥልኝ የዝግጅታችን ተከታታዮች እንደምን ሰነበታችሁ፤ ይህን የእናቶች ዕለት ተንተርሶ የወጣ ዘገባ ዘንድሮም ኖርዌይና ስዊድንን ከምርጥ የእናቶች መኖሪያነታቸዉ ክብር ዝቅ እንዳላሉ አሳይቷል። ኒዠርና አፍጋኒስታን፤ ደግሞ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም እነኤርትራን አስከትለዉ ለእናቶች የማይመረጡ ማለትም የከፉ ስፍራዎች ተብለዉ ተደርድረዋል።

Mutter mit Kind
ምስል bilderbox.com

የእናቶች ቀን ዓመት ቆጥሮ ሲታሰብ ለእናቶችና እናትነት ክብር በመለገስ፤ እናቶች በማኅበረሰቡ ዉስጥ የሚያሳድሩትን አዎንታዊ ተፅዕኖ ለማዘከር ታስቦ እንደሆነ ይነገራል። ነፍሰጡር ሴቶችም ሆኑ የወለዱ እናቶች በሚኖሩባቸዉ አገሮችና አካባቢዎች ለእነሱም ሆነ ለልጆቻቸዉ ተገቢዉ የጤና ክብካቤ፤ የተመጣጠነ ምግብ ብሎም ትምህርት ማግኘት ይችሉ ዘንድ የሚደረጉ ሙከራዎች በየስፍራዉ ቢኖርም፤ ይህ ጥረት ተሳክቶላቸዉ፤ እናቶች ቢኖሩባቸዉ የተሻሉ ብቻ ሳይሆን ምርጥ ቦታዎች ናቸዉ የተባሉ አገሮች በየጊዜዉ ደረጃቸዉ ይመዘናል።  Save the children የተሰኘዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በእናቶች ቀን ዋዜማ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ ኖርዌይ፤ አይስላንድ፤ ስዊድን፤ ኒዉዚላንድ፤ ዴንማር፤ ፊንላንድ፤ አዉስትራሊያ፤ ቤልጂየም፤ አየርላንድ፤ ኔዘርላንድ እንዲሁም ብሪታንያን በቅደም ተከተል ከመጀመሪያዎቹ ምርጥ አገሮች ተርታ አስፍሯል። 165አገሮችን አካቶ የተካሄደ መሆኑ የተገለፀዉ ይህ ጥናት በየአገሮቹ ለእናቶች የስነተዋልዶ ጤና፤ የሚያገኙት ትምህርት፤ የኤኮኖሚ ይዞታ፤ የልጆች ጤና አገልግሎት እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት እድልን መሠረት አድርጎ መሰራቱ ተገልጿል። ከምንም በላይ ደግሞ ነፍሰጡር እናቶችና እስከ ሁለት ዓመት የእድሜ ደረጃ የደረሱ ህፃናት የሚያገኙት የተመጣጠነ ምግብ ይዞታ ላይ አተኩሮ ነዉ የተዘጋጀዉ። ዘገባዉ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረበት ዋና ምክንያትም በየዓመቱ 2,6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ህፃናት ሞት ምክንያት በመሆኑ እንደሆነም ተመልክቷል።

Retterbaby für kranke Schwester in Brasilien
ምስል picture-alliance/Agencia Estado

እናም አፍሪቃዊቷ አገር ኒዠር እንዲሁም መካከኛዉ እስያ ዉስጥ የምትገኘዉ አፍጋኒስታን ረሃብ ለእናቶች ጥሩ ያልሆኑ ቦታዎች ተብለዉ በግንባር ቀደምትነት ተለይተዋል። በእነዚህ አገሮች ምንም እንኳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ከሞት ቢተርፉም በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ባለማግኘታቸዉ አካላቸዉም ለእድሜ ልክ ጉዳት ሲዳርግ፤ አዕሞሯቸዉ በወጉ ተገቢዉን ተግባር እንዳያከናዉን እንቅፋት እንደሚሆን ተጠቅሷል። ከእነዚህ ሀገሮች በተጨማሪ የመን፤ ጊኒቢሳዉ፤ ማሊ፤ ኤርትራ፤ ቻድ፤ ሱዳን፤ ደቡብ ሱዳን እና ዴሞክራቲክ ኮንጎም ለእናቶች የከፉ መኖሪያዎች በሚል ከሰንጠረዡ እታች ሰፍረዋል። ዘገባዉ እንዳመለከተዉም ከእነዚህ ለእናትነት መጥፎ ከተባሉ አስር አገሮች መካከል ሰባቱ በምግብ ቀዉስ ላይ ይገኛሉ። በተለይ ከሁሉም የዝርዝሩ መጨረሻ ላይ የሰፈረችዉ ኒዠር የምትገኝነት የምግብ እጥረትና ረሃብ ይዞታ በመባባሱ በሚሊዮን የተገመቱ ህፃናት ህይወት አደጋ ላይ መሆኑ ተገልጿል። ኒዠር  ዉስጥ ካሉት አጠቃላይ የህፃናት ቁጥር አንድ ሶስተኛዉ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጎድተዋል፤ ከሰባቱ አንዱ ደግሞ አምስት ዓመት ሳይሞላዉ ይቀጠፋል፤ በተጨማሪም ከአስር ህፃናት አንዱ ቀኑሳ ይደርስ ቀድሞ ይወለዳል።

Verbesserung der Gesundheitsversorgung der Mütter Millennium Development Goals
ኢትዮጵያዊቱ የልምድ አዋላጅ ድርስ ነፍሰጡር ቤት ዉስጥ በማዋለድ ሂደትምስል picture-alliance/dpa

በነገራችን ላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአገራት የስም ዝርዝር የመጨረሻዋ የነበረችዉ አፍጋኒስታን ዘንድሮ ቦታዋን ለኒዠር በማስረከብ ባሳየችዉ መጠነኛ መሻሻል አንድ  እርከን ከፍ ብላለች። ከአፍሪቃ አገሮች የተሻለ ደረጃ ላይ የተቀመችዉ ኬንያ ናት። ኬንያ አንድ መቶዎቹን የዓለም አገሮች አስከትላ በ65ተኛ ደረጃ ለእናቶች ምርጥ ስፍራ ተብላለች። ከምዕራብ አገሮች ነፍሰጡር እናት ከሰባት እጅ በላይ ህይወቷን የማጣት እድል ይኖራታል የተባለባት ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ አምና ከነበረችበት 31ኛ ደረጃ ወደ25ኛ ከፍ ማለቷን ጥናቱ አመልክቷል። በበለፀጉት አገሮች ወደትምህርት ቤት ከመግባታቸዉ አስቀድመዉ ወደሚቆዩባቸዉ የመጀመሪያ ደረጃ መዋያ ስፍራዎች በርካታ ህፃናትን በመላክ ደግሞ በአስረኛ ደረጃ ተመዝግባለች። ከሁለት ዓመታት በፊት በወጣ ተመሳሳይ ዘገባ ከዝቅተኞቹና ለእናቶች የማይመረጡ ከተባሉ አገሮች አንዷ የነበረችዉ ኢትዮጵያ፤ ዘንድሮ ከታችኞቹ አስር አገሮች መደዳ ስሟ አልሰፈረም።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ