1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፊሌ ባለሥልጣናት ላይ የተላለፈ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 5 2010

አፊሌ በተባለችው የኢጣልያ ከተማ ውስጥ በኢጣልያ ወረራ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ለጨፈጨፈው ፋሺሽት አዶልፎ ግራዝያኒ መታሰቢያ እንዲገነባ የፈቀዱ ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት ቅጣት ተበይኖባቸዋል። ብይኑ፣የመታሰቢያውን ግንባታ በመቃወም ጉዳዩ ፍትህ እንዲያገኝ ሲታገሉ የቆዩ ኢትዮጵያውያን አስደስቷል ።

https://p.dw.com/p/2ndA1
Benito Mussolini im Jahr 1943
ምስል picture alliance/Everett Collection

በአፊሌ ባለሥልጣናት ላይ የተላለፈው ውሳኔ

 አፊሌ ከኢጣልያ ርዕሰ ከተማ ሮም 79 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። በአስተዳዳሪዎችዋ ፈቃድ እና ድጋፍ የዛሬ 5 ዓመት በዚህች ከተማ የተገነባ መታሰቢያ ተቃውሞ አስነስቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ከቆየ በኋላ ባለፈው ሳምንት ብይን ተሰጥቷል። ብይኑ የተላለፈው በኢጣልያ ወረራ ወቅት የካቲት 12፣ 1929  ቁጥራቸው እስከ 30 ሺህ የተገመተ ኢትዮጵያውያንን ያለ አንዳች ርህራሄ በፈጀው በጀነራል አዶልፎ ግራዝያኒ የመቃብር ስፍራ መታሰቢያ እንዲገነባ ባደረጉ የከተማዋ ከንቲባ እና ሌሎች ሁለት ባለሥልጣናት ላይ ነው። በዚሁ መሠረት የከተማይቱ ከንቲባ ኤርኮሌ ቪሪ የ8 ወራት እሥራት ሲበየነባቸው ሁለቱ የአፊሌ አስተዳደር ባለሥልጣናትም የ6 ወራት እሥራት ተፈርዶባቸዋል። ከንቲባ ቪሪ ክሱን ለመሰረተው በምህጻሩ አንፒ በመባል ለሚጠራው «የኢጣልያ የጦርነት ጊዜ አርበኞች ማህበር» 8ሺህ ዩሮ እንዲከፍሉም ቅጣት ተጥሎባቸዋል። መቀመጫውን ቴክሳስ ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው«ዓለም አቀፍ ህብረት ለፍትህ የኢትዮጵያ ጉዳይ» የተባለው ማህበር ከኢጣልያ የጦርነት ጊዜ አርበኞች ማህበር አንፒ ጋር ጉዳዩ ፍትህ እንዲያገኝ ከታገሉት የኢትዮጵያውያን ማህበራት አንዱ ነው። ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረችበት ጊዜ ለደረሰው የሰው ህይወት እና የንብረት ጥፋት ተገቢ ፍትህ አልተሰጠም ሲል ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት የሚጠይቀው እና የሚያሳስበው ይህ ማህበር  በአፊሌ ለግራዝያኒ መታሰቢያ መሠራቱን በመቃወም ድምጹን ሲያሰማ መቆየቱን የማህበሩ ተጠሪ አቶ ኪዳኔ አለማየሁ ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ሙሉ አየለ በኢጣልያ የኢትዮጵያ ኮምኒቲ የሥራ አመራር አባል ናቸው ። በአፊሊ ለግራዝያኒ መታሰቢያ መሰራቱን እንዳወቁ ከኮምኒቲው አባላት እና ከሌሎች መታሰቢያው መገንባቱን ከማይደግፉ አካላት ጋር ወደ በአካባቢው በመሄድ ተቃውሞአቸው እንዲሰማ እና የአካባቢው ህብረተሰብም ጉዳይን እንዲረዳ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
ለፋሽሽቶች መታሰቢያ ማሰራት እና የመሳሰለው ድርጊት በኢጣልያ ህግ የሚያስቀጣ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሙሉ ለግራዝያኒ መታሰቢያ እንዲሰራ ድጋፍ የሰጡት አፊሌ የምትገኝበት አውራጃ አስተዳዳሪ ከተቀየሩ በኋላ ተቃውሞአቸው ውጤት ማምጣት መጀመሩን ገልፀዋል። 
ከዚያ በኋላ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተለያየ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት እየጨመረ መምጣቱን ወይዘሮ ሙሉ ያስታውሳሉ። ኢጣልያ በኢትዮጵያ የፈፀመችውን ግፍ እና በደል በተለያየ መንገድ እንዲተዋወቅ መደረጉም በተለይ ወጣቱ ታሪኩን እንዲረዳ አስተዋጽኦ አድርጓል እንደ ወይዘሮ ሙሉ። ወይዘሮ ሙሉን ጨምሮ የኢጣልያ የኢትዮጵያ ኮምኒቲ አባላት ሮማ በሚገኘው የአፊሌ ባለሥልጣናት ጉዳይ ሲታይ በቆዩበት የቲቮሊ ፍርድ ቤት በቀጠሮ እየተገኙ ለ5 ዓመታት የተካሄደውን የፍርድ ሂደት ከኢጣልያዎቹ አጋር ድርጅቶች ጋር ሲከታተሉ ቆይተዋል። ወይዘሮ ሙሉ የዛሬ ሳምንቱ ብይን ሲሰጥም ፍርድ ቤት ነበሩ። 
በውሳኔው መደሰታቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሙሉ መታሰቢያው እንዲሰራ ባደረጉት ባለሥልጣናት ላይ ብይን ከመተላለፉ ውጭ ስለ መታሰቢያው የዛሬ ሳምንት የተሰጠው ውሳኔ አለመኖሩ ያሳስባቸዋል።  አቶ ኪዳኔ አለማየሁ ባለፈው ሳምንት በአፊሌ ባለሥልጣናት ላይ የተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም አለው ይላሉ። ምክንያቱንም እንዲህ ያብራራሉ።
የእሥራት እና የገንዘብ ቅጣት የተበየነባቸው የአፊሌ ከንቲባ ይግባኝ ይላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Äthiopien Gedenken 80. Märtyrertag in Addis Abeba
ምስል DW/E. Zeleke

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
.