1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሉሙምባ፥ የኮንጎ ስንኩል ዕጣ-ፈንታ

ሐሙስ፣ የካቲት 15 2010

«ኮንጎያውያን፤ መስዋዕትነት ሳትከፍሉ እንዳትመናመኑ ሁላችሁንም እጠይቃለኹ!» ፓትሪስ ሉሙምባ በኮንጎ የነፃነት ቀን እ.ጎ.አ. በ1960 ዓ.ም የተናገሩት ነው። መናገር ብቻ አይደለም ወጣቱ ጠቅላይ ሚንሥትር ለሌሎችም አብነትም ኾነዋል። ሌሎች በቀላሉ እጅ በሰጡበት ወቅት፤ የቅኝ ገዢዎችን በግልጽ እና በጽኑእ አለማመናቸው ሕይወታቸውን አስከፍሏቸዋል።

https://p.dw.com/p/2t5ty
Lumumba mit Joseph Mobutu
ፓትሪስ ሉሙምባ (መነጽር ያደረጉት) እና የኮንጎ አዲሱ ወታደራዊ አዛዥ ጆሴፍ ሞቡቶ ከጎናቸው ኾነው ሲያወሩምስል picture-alliance/dpa/TopFoto

እንዳከብረው ብታስገድድ ነጩ ሰውኽን እንደጌታ፤ እህ ብለህ አድምጥ ልንገርህ ለአንዳፍታ። ከእንግዲህስ አበቃ፤ ይህች ሀገር አይደለችም የእሱ መጫወቻ እቃ። ቀና ብለው እንዲያዩ፣ አጥርተው እንዲቃኙ ወንድሞችህ፤ ከቶ ብታደላ ለዘሮችህ፤ እኛስ ይታየናል ከፊታችን የነጻነት ብሩኅ ተስፋ።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1959 ዓ.ም. ፓትሪስ ኤምር ሉሙምባ የቤልጂግ ኮንጎ መዲና ሊዮፖልድቪል ውስጥ በተነሳው ዓመጽ ሠለባ ለኾኑ ሰዎች መታሰቢያ «ኦ ጥቊሩ ውድ ወንድሜ» በሚል ርእስ ካቀረቡት ግጥም የተቀነጨበ ትርጉም ነው። ለነጻነት የሚደረጉ ተቃውሞዎች በቤልጂግ ቅኝ ገዢ ባለሥልጣናት በኃይል ይደፈለቊ ነበር። ለነጻነት በሚደረገው ትንቅንቅም ፓትሪስ ሉሙምባ የጸረ-ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄው መሪ ኾነው ብቅ አሉ። በኪንሻሳ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምሕሩ ካምባዪ ብዋትሺያ ያብራራሉ።   

ይኽ ንቅናቄ ለበርካቶች አርአያ የኾነ መሪ አለው፤ ስሜቱ ጋል ያለ፣ ለዓለም ክፍት የኾነ ሰው፦ ሉሙምባ።  ብሩኅ የኾነው ሰው፤ ኢፍትሐዊነትን አጥብቆ የሚቃወም፤ መነጠል ምን እንደኾነ ጠንቅቆ የሚያውቅ፤ በጊኒ የነበረውን እንቅስቃሴ በቅርበት የተከታተለ፤ ጊኒያውያን ለፈረንሳይ ማኅበረሰብ ፖለቲካ እንዴት እምቢኝ እንዳሉ የተመለከተ ሰው። ሉሙምባ ይህን መንገድ በመከተል የቤልጂግ ቅኝ ገዢ ፖለቲካን በመቃወሞ ታግሏል።  

Fotograf Horst Faas - Patrice Lumumba
ፓትሪስ ሉሙምባ በኮንጎ አዲሱ ወታደራዊ አዛዥ ጆሴፍ ሞቡቶ ወታደሮች ተይዘው እጃቸው እንደተጠፈረምስል AP

እኚህ የቀድሞ የፖስታ ቤት ሠራተኛ የፖለቲካ ትምህርታቸውን የቀሰሙት ከማንበብ ነው። ነጻ እና የተባበረች ኮንጎን ማየትም ምኞታቸው ነበር። ሉሙምባ የጎሣ አስተሳሰብን ውድቅ በማድረጋቸው በኮንጎ ፖለቲከኞች ጥርስ ተነክሶባቸዋል። ይኽን አጋጣሚም ቅኝ ገዢ ባለሥልጣናቱ ተጠቅመውበታል። ኾኖም ራሱን በራሱ ያስተማረው፣ ሩቅ አሳቢው እና ባለ ግርማ ሞገሱ የሠላሳ ዓመቱ ወጣት ብዙኃኑን እንዴት ማሳመን እንደሚቻል በሚገባ  ተክኖበታል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1960 ግንቦት ወር ውስጥ በተደረገው የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ ምርጫም የፓትሪስ  ሉሙምባ ፓርቲ በሰፊው አሸናፊ ኾኗል። ሰኔ 30 ቀንም ፓትሪስ ሉሙምባ በኮንጎ ነጻነት ክብረ-በዓል ዕለት እንደ ጠቅላይ ሚንሥትር ንግግር አሰምተዋል። «ኮንጎ በቤልጂግ ባለ ምጡቅ አዕምሮዋውያን የተጸነሠች ናት» በሚሉት የቤልጂግ ንጉሥ ቦዶይን ላይ ያሰሙት ትችት  እጅግ የሠላ ነው።    

ክብር ለብሔራዊ ነጻነት ተፋላሚዎቻችን። ከማለዳው አንስቶ ቀኑን ሙሉ ብሎም ምሽቱን ጭምር በስድብ ውርጅብኝ መዋረዱን፤ መሸማቀቁን እና መንገላታቱን ዕናውቀዋለን፤ ምክንያቱም ባርያዎች ዎች ነበርና። ኧረ ለመኾኑ በርካታ ወንድሞቻችን ከምድረ ገጽ የጠፉበትን የተኩስ እሩምታዎች ማን ይኾን የሚዘነጋ? ኢፍትኃዊ፣ ጨቋኝ እና በዝባዡን መንግሥት በመቃወማቸው በርካቶችን በግፍ ያጎሩት እስር ቤቶችንስ? 

በአዳራሹ ውስጥ ተሰብሰበው የነበሩ ኮንጎያውያን ሞቅ ባለ ጭብጨባ ነው ያጀቧቸው። የፓትሪስ ሉሙምባ የማያወላዳ ንግግር ግን ለቤልጂጉ ንጉሥ ቦዶይን እንደ ስድብ ነበር የተወሰደው። ፕሮፌሰር ካምባዪ ብዋትሺያ ያብራራሉ።

በንግግሩ ንጉሡን አስከፍቷል፤ ቤልጂግን አስቆጥቷል። ከዚያ ንግግር በኋላ ፓትሪስ ሉሙምባ ሕይወት ተመሳቅሏል። የሕዝቡ ኃይል የተበታተነ ነበር። ከኅብረተሰቡ ተደማጭነት ያለው ይኼ ተብሎ የሚጠቀስ አንድም ጥቊር አልነበረም። ሕዝባዊ አገልግሎቱ አሽቆለቆለ፤ ፀጥታው ተናጋ። ሉሙምባ ለማስተዳደር ሕጋዊ መሣሪያዎች አልነበሯቸውም። ብቻቸውን ነበሩ፤ ብቻቸውን ቀሩ፣ ብቻቸውን። ቤልጂጎች እና ኢምፔሪያሊስቶች ሀገሪቱን ሙሉ ለሙሉ አመሳቀሏት። አደገኛ ትርምስ ነበር።

Lumumba Statue Patrice Lumumba Kinshasa
ለፓትሪስ ሉሙምባ መታሰቢያ የቆመ ሐውልት ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ሊሜቴ ውስጥምስል Getty Images/AFP/J.D.Kannah

በቤልጂግ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የተነሳ ኮንጎ ምሑራን አልነበሯትም። ይኽ ትርምስ በነጻነት ማግስት ውሎ ሳያድር በካታንጋ እና በደቡብ ካሳይ መገንጠል ተንጸባርቋል። ከሁለት ወራት በኋላም ሉሙምባ ከሥልጣናቸው ተወገዱ። ይኽም የቅኝ ገዢዎችን ጨዋታ ይጫወት ለነበረው ለወጣቱ ወታደር ጆሴፍ ዴዚር ሞቡቱ የተመቸ አጋጣሚ ኾነና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ራሱን የሀገሪቱ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሲል ሰየመ። የፓትሪስ ሉሙምባ መታሠር፤ ከዚያም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1961 ጥር ወር በአሰቃቂ ኹኔታ መገደል በመላው ዓለም ቁጣ ቀሰቀሰ። ሉሙምባ ለእንዲህ ያለ ዕጣ ፈንታ ተዘጋጅተው ነበር። ከመጨረሻዎቹ ደብዳቤያቸው በአንዱ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ «ሀገሪቱ ራሴን ለነጻነቷ ቤዛ አድርጌ ማቅረቤን አንድ ቀን ትገነዘባለች።»

ታማራ ዋኬርናግል/ ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

 ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ