1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊስትሮዋ የልጅ እናት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 8 2008

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን ብዙ ፈተናዎችን ያሳለፈች ወጣት ናት። ከልጅነቷ አንስቶ የቤት ሰራተኛ ሆና አገልግላለች ፤ኃላም የጎዳና ተዳዳሪ ነበረች። እዛው ጎዳና ላይም ነፍሰ ጡር እና እመጫት ሊስትሮም ሆና ሰርታለች።

https://p.dw.com/p/1HNZl
Die Schuhputzerin Meseret
ምስል Hilina Abebe

ሊስትሮዋ የልጅ እናት

በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ መሠረትን ነፍሰ ጡር ወይም ልጇን በጀርባዋ አዝላ ጫማ ስትጠርግ ከተማ ውስጥ ያስተዋሏት አይጠፉም። ወጣቷ ወደ ሊስትሮ ስራ ከመግባቷ በፊት የቤት ሰራተኛም ነበረች። « ደብረ ዘይት ከተማ አቅራቢያ ድሬ የሚባል አባባቢ ነው ተወልዳ ከአያቶቿ ጋር ያደገችው። ከወላጆቿ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች አብራ መኖር ባለመቻሏ ከቤት ጠፍታ ሰውቤት በቤት ሰራተኝነት ታገለግል ጀመር። እድሜዋን በግምት የምትናገረው መሠረት ከእናቷ ቤት ስትወጣ «የዘጠኝ ዓመት ልጅ ብሆን ነበር» ትላለች። በወቅቱ እድሜዋ ትንሽ ስራዋ ግን ብዙ ነበር።
በቤት ሠራተኝነት ከአንዱ ቤት ሌላኛው ጋር እየገቡ መቀጠር ብቻ ሳይሆን፤ ከተማዎችንም እየቀያየረች ሰራች። በመሀልም ትምህርት የመማር ዕድል ገጥሟት ነበር። እስከ 3ኛ ክፍል ተምራለች። ትምህርቷን እና ስራዋን አቋርጣም ወደ ሀዋሳ፣ ሻሸመኔ በመጨረሻም አዲስ አበባ ገብታ መኖር ጀመረች። ወደ መዲናዋ ስትጓዝ የምታውቀው ሰው አልነበረም። በአጋጣሚ መንገድ ላይ ተዋወኳት የምትለው ወይዘሮ ከዛም እቤቷ ትቀጥራታለች። ዛሬ 20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው መሠረት አዲስ አበባ ውስጥም ቤት እየቀያየረች ሠራች፤መጨረሻዋ ግን የጎዳና ህይወት ይሆናል። በጎዳና ላይ ስትኖርም የሴት ልጇን አባት ተዋወቀች። የሊስትሮ ሥራም ጀመረች። ብዙም ሳትቆይ አረገዘች።
Die Schuhputzerin Meseret
የመሠረት ልጅ አንደኛ ዓመት ልደትምስል Hilina Abebe
እስከ መጨረሻው ቀን የሰራችው መሠረትም ሴት ልጇን በመንግሥት ሆስቲታል ያለ ምንም ክፍያ ትገላገላለች። ነገር ግን ኑሮ ስላስገደዳት ብዙም ሳትቆይ ወዲያው ወደ ስራዋ ተመለሰች።ሥራዋ ከብዙ ሰዎች ጋር የሚያገናኛት ስለነበረም አላፊ አግዳሚው ይገረም እና ያያት ጫማ የሚያስጠርጉትም አስተያየት ይሰጧት ነበር።
ይሁንና የመሠረት ደስታ ብዙም አልቆየም። ዛሬ ከልጇ አባት ተለይታ ፤ብቻዋን ልጅ አሳዳጊ እናት ናት። ህይወቴ ብዙም አልተቀየረም የምትለው መሠረት ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት የሊስትሮ ስራዋን አቁማ ሌላ ስራ ጀምራለች። የመሠረት አሁን ካለችበት ሕይወት የሚለውጣት ስራ አግኝታ መኖር የወደፊት ምኞቷ ነው። ለሕፃን ልጇ ደግሞ እሷ ያላገኘችውን የትምህርት እድል ማመቻቸት እና ትልቅ ቦታ ላይ ማድረስ ትመኛለች። መሠረት እራሷም ብትሆን መልሳ ትምህርት ቤት መግባት ብትችል ደስተዋ እንደሆነ ነግራናለች።
ሙሉውን ዘገባ በድምፅ ያገኙታል።
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ