1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያና ያልተሳካው የአፍሪቃ ኅብረት ሽምግልና፣

ረቡዕ፣ ግንቦት 24 2003

የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ፤ የአፍሪቃ ኅብረትን የሽምግልና ሐሳብ፣ ለሊቢያው መሪ ኮሎኔል ሙኧመር ጋዳፊ ትሪፖሊ ድረስ በመጓዝ ቢያቀርቡም፣ ሽምግልናው ሳይሠምር ነው የቀረው።

https://p.dw.com/p/RR4J
ሊቢያና ያልተሳካው የአፍሪቃ ኅብረት ሽምግልና፣
ምስል dapd

የአፍሪቃ ኅብረት ፣ በመንግሥት ወታደሮችና በአማጽያን መካከል 3 ወራት ገደማ የሆነው ውዝግብ ወይም የተኩስ ልውውጥ፣ የኔቶ የአየር ድብደባ ጭምር ባስቸኳይ እንዲቆም ነበረ የጠየቀው። ውዝግቡን በእርግጥ በሰላማዊ መንገድም ሆነ በዲፕሎማሲ ለመፍታት ዕድሉ አሁንም አለ ማለት ይቻላል? ተክሌ የኋላ፣ በፕሪቶሪያ የዓለም አቀፉ ስልታዊ ጥናት ተቋም ስራ አስኪያጅ የሆኑትን ጃኪ ሲልየርስን አነጋግሮ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

የአፍሪቃን ኅብረት የሰላም ሐሳብ ይዘው ነበረ ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ ወደ ትሪፖሊ ጎራ ያሉት። የሊቢያው መሪ ፤ ተኩስ ቆሞ፣ ውይይት እንዲጀመር የቀረበውን የሰላም ሐሳብ ቢቀበሉትም፤ ከአማጽያኑ አሁንም በጎ ምላሽ ያገኘ አይመስልም። ከእንግዲህ ውዝግቡን በሰላም ለመፍታት የዲፕሎማሲው ጥረት አክትሟል ወይስ ሌላ ዕድል ይኖራል? ጃኪ ሲልየርስ--

«ፕሬዚዳንት ዙማ፤ የአፍሪቃን ኅብረት ወክለው ነው በሊቢያ የተገኙት። ከውዝግቡ መላቀቅ የሚቻልበትን መላ ለመሻት!በግልጽ እንደሚታየው፣ የአየር ድብደባው በራሱ ጋዳፊን ከሥልጣን የሚያፈናቅል አይደለም እንደሚመስለኝ ለሆነ የሰላም ሂደት፣ ድጋፉ እየጨመረ በመሄድ ላይ ሲሆን፤ ይህ የሚንቀሳቅስበትን በር ክፍቷል። ፕሬዚዳንት ዙማም ይህን መነሻ አድርገው ነው በዚያ የተገኙት።»

ለመሆኑ፤ ጋዳፊ ውሎ-አድሮ አስተማማኝ ሁኔታ ከተገኘ አገር ጥለው ምናልባት ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚሰደዱ ይመስሎታል?

«እንደሚመስለኝ፤ በመጀመሪያ በጋዳፊና በአማጽያኑ መካከል ያላንዳች ቅድመ-ግዴታ ድርድር የሚካሄድበት ሁኔታ እንደሚኖር ማረጋገጥ ግድ ይላል። ጋዳፊ ፣እስካሁን ፣ ሥልጣን እንደሚለቁ የሰጡት ፍንጭ የለም።

አማጽያኑ ደግሞ ለድርድር የጋዳፊን ሥልጣን መልቀቅ ቅድመ- ግዴታ አድርገው አቅርበዋል። ድርድር፤ ያለቅድመ-ሁኔታ እንዲካሄድ ከተፈለገ፤ ይህ ጉዳይ እልባት ማግኘት ይኖርበታል። ይህን ካልኩ በኋላ፣ ጋዳፊ አገር, ለቀው ይውጡ በሊቢያ ይቆዩ፣ ይህ የድርድሩ አንድ ከፊል መሆን አለበት። ጋዳፊ፣ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ስለሚመጡበት ሁኔታ አንዳች ውይይት አልተደረገም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በደቡብ አፍሪቃና በሊቢያ መካከል በተለይ ከጋዳፊ ጋር ያለው ግንኙነት ጥሩ አይደለም። ደቡብ አፍሪቃ፤ ተገን ልስጥ ካለች፣ ወይም ጋዳፊን በፖለቲካ ስደተኛነት ለመቀበል ከተዘጋጀች በጣም ነው የሚገርመኝ።»

ጋዳፊ የ ANC ጥሩ ወዳጅና ባለውለታ መሆናቸው ይረሳል ወይ?

«አዎ ታሪካዊ ግንኙነቶች አሉ። ይህ አውነት ነው። ነገር ግን ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፣ በደቡብ አፍሪቃናበሊቢያ በተለይ ከጋዳፊ ጋር አለመግባባትም ሆነ ውጥረት ነበረ። የውጥረቱ መንስዔ ደግሞ፤ አፍሪቃን ለማስተባበር ወይም ለማዋኻድ የጋዳፊ ሚና ነበረ፤ በተለይት ፕሬዚዳንት ታቦ እምቤኪና ጋዳፊ በደቡባዊውና በምሥራቃዊው አፍሪቃ በበጎ ዐይን አይታዩም። ተቀባይነት የላቸውም። ችግር ፣ ደንቃራ፤ የሚፈጥሩ ሆነው ነው የሚታዩት።»

መውጫው መንገድ መፍትኄው ታዲያ ምንድን ነው ይላሉ?

«ከዚህ ውዝግብ ለመውጣት፤ የፖለቲካ ሂደት ያስፈልጋል። ድርድር፤ ያሻል። ድርድሩ አማጽያኑንና ጋዳፊን የሚያቅፍ መሆን አለበት። ብቸኛው የመፍትኄ ጎዳና፤ የአፍሪቃ ኅብረት ያቀረበው ሐሳብ ነው።በሂደቱ ፣ የአፍሪቃ ኅብረት ችላ የተባለበት ሁኔታ አለ። በዚህም ሳቢያ የአፍሪቃ ኅብረት- ብቸኛው ዐቢይ የክፍለ ዓለሙ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፤ ጉዳዩ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ በማለት ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ ለጋዳፊ ተገን መሆኑ አልቀረም። የፖለቲካው ሂደትም እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ ነው። «ኔቶ» በግልጽ በራሱ የሚፈጽማቸው ጥቃቶች በቂ አይደሉም። ከጊዜ ወደጊዜ እንደሚታየውም፣ ድርጊቱ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃውን ም/ቤት፣ ውሳኔ ፣ አንቀጽ 1972 የሚጻረር ነው። ውሳኔው፣ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ ሳይሆን፤ ሲብሎችን ለመጠበቅ ብቻ መወሰድ ያለበት እርማጃ መሆኑን ነው የሚገልጸው።»

ተክሌ የኋላ

መሳይ መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ