1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ላይቤሪያ እና አዲሱ የሽግግር መንግሥት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 3 1996
https://p.dw.com/p/E0lO

በብዙ ዓመታት የርስበርስ ጦርነት ለተጎዳችው ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ላይቤሪያ ዘላቂ ሰላም ለማውረድ በተጀመረው ሂደት ላይ በዛሬው ዕለት አንድ ወሳኝ ርምጃ ተንቀሳቅሶዋል። የላይቤሪያ ተቀናቃኝ ወገኖች ባለፈው ነሐሴ በጋና አክራ በደረሱት ስምምነት መሠረት፡ ጊድ ብራይንት ዛሬ የሽግግሩን መንግሥት አመራር ከተጠባባቂው ፕሬዚደንት ሞዘስ ብላ ተረክበዋል። ብራይንት በሀገሪቱ መረጋጋት እና አንድነትን ለማስገኘት በሚያያደርጉት ቀላል ያልሆነ ጥረታቸው ላይ ብዙ አዳጋች መሰናክችን ማለፍ ይኖርባቸዋል። በዚሁ ጥረታቸውም ላይ ግዙፉ የምዕራባውያን ርዳታ አስፈላጊ ይሆናል።

የላይቤሪያ ተቀናቃኝ ወገኖች በጠቅላላ በባለተቋሙና በፖለቲከኛው ብራይንት ምርጫ ላይ ተስማምተዋል። እንግዲህ አሁን ብራይንት ለላይቤሪያ፡ የራሳቸውን አነጋገር ለመጠቀም መድህን እና ተስፋ የሚጣልባቸው መሪ መሆናቸውን ወይም እያንዳንዱ ተፋላሚ ወገን ለራሱ እንደሚስማማ አድርጎ ተፅዕኖ ሊያሳርፍባቸው እንደሚችል በመገመት እንደመረጣቸው ማሳየት ይኖርባቸዋል። አዲሱ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚደንት በተመደበላቸው የሁለት ዓመት አመራራቸው የሀገሪቱን አንድነት ለማስገኘት፡ ሥርዓተ ዴሞክራሲ የሚተከልበትን እና ምርጫ የሚካሄድበትን መንግድ ለማስያዝ ከፈለጉ የጠቅላላ ላይቤሪያውያን ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ሀገሪቱ በወቅቱ የምትገኝበት ፖለቲካዊ፡ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ውድቀት ሁኔታ ሲታሰብ ግን ይህ ብራይንትን የሚጠብቃቸው ተግባራቸው እጅግ አዳጋች እንደሚሆን አላጠራጠረም። መንግሥት የሚመሠረትበት ድርጊት፡ ብራይንት በዚሁ ጥረታቸው ላይ ወደፊት የተሳካ ውጤት ለማግኘታቸው እንደ መጀመሪያው ምልክት ሆኖ ታይቶዋል። አዲሱ መንግሥት የቀድሞ መስተዳድር ተወካዮችን፡ የሁለቱን የዓማፅያን ቡድኖች የአሥራ ስምንቱ የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቭሉን ኅብረተ ሰብ አባላትን ጭምር ማጠቃለል ይኖርበታል። ካቢኔው ሰባ ስድስት ቦታዎች እንዲኖሩት በመወሰኑ፡ የመንግሥቱ ምሥረታ መሳካቱ አይቀር ይሆናል፤ ይሁንና፡ የካቢኔው እንዲህ መንዛዛት፡ በተለይ የሽግግሩ መንግሥት በወቅቱ ከመዲናይቱ ሞንሮቪያ ውጭ ሥልጣን እንደሌለው ሲታሰብ፡ አስቸኳዩንና ፍቱኑን የመንግሥት ሥራ ተጓታች ያደርገዋል። ከዚህ ሌላ በመንግሥቱ ውስጥ የጎላው የቀድሞው ግንኙነትና በተለይ፡ አሁንም በቀላሉ የማይገመተው የቀድሞው ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር ተፅዕኖ በሽግግሩ መንግሥት ሥራ ላይ ተጨማሪ መሠናክል እንደሚደቅኑ ግልፅ ሆኖዋል። ባለፈው ነሐሴ ከሥልጣን የወረዱትና ከዚያ ጊዜ በኋላም በናይጀሪያ የካላባር ከተማ በግዞት የሚኖሩት የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚደንት አሁንም ባንዳንድ የሀገራቸው ውስጣዊ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ የሚጫወቱት ሚና ያለ ነው የሚመስለው። ለላይቤሪያ ምሥቅልቅል ሁኔታ ተጠያቂ ናቸው የሚባሉት ቴይለር አሁንም ምን ያህል እንደሚፈሩ፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እና አስተናጋጃቸው የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንዦ ከጥቂት ቀናት በፊት ቴይለር የላይቤሪያን የሰላም ሂደት ለማሠናከል የሚያደርጉትን ሙከራ በጠቅላላ እንዲያቆሙ ያስተላለፉት የማስጠንቀቂያ መልዕክት በግልፅ አሳይቶዋል።

ብራንንት የሚመሩት የሽግግር መንግሥት አዎንታዊ ውጤት የሚያስገኝበት ድርጊት በመንግሥቱ የሚጠቃለሉት ሁሉ የራሳቸውን ጥቅም ወደ ጎን በመተው፡ ኃይላቸውን በሙሉ ለሀገሪቱ ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መልሶ ግንባታ ለማስተባበር ዝግጁ በሚሆኑበት አሠራር ላይ ጥገኛ ይሆናል። አዲሱን መንግሥት ከሚጠብቀው፡ ማለትም፡ ሚሊሺያዎችን የጦር መሣሪያ ትጥቅ ከማስፈታቱና ከመበተኑ አዳጋቹ ተግባር ጎን፡ ሕፃናት ወታደሮችን ከኅብረተ ሰቡ ጋር መልሶ ማዋኃድን፡ የኤሌክትሪኩን አቅርቦት ዝግጁ ማድረግን፡ የጤና ጥበቃ ተቋማትንን እና ትምህርት ቤቶችን መገንባትን የመሳሰሉት ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው። ሌላው አስቸኳይ መልስ ማግኘት አለበት የሚባለው ጉዳይ ደግሞ የሰብዓዊ ቀውስን ጉዳይ ሲመለከት፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥ ባሉ የመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉት አሥር ሺህ ላይቤሪያውያን፡ እንዲሁም በጎረቤት ምዕራብ አፍሪቃውያቱ ሀገሮች ተገን ላገኙት ከሦስት መቶ ሺህ ለሚበልጡት የላይቤሪያ ስደተኞች አስፈላጊው ርዳታ መቅረብ ይኖርበታል። የመጀመሪያዎቹ ስደተኝ ወደ ትውልድ መንደራቸው ሲመለሱ፡ ያኔ የሽግግሩ መንግሥት የሀገሩን ፀጥታ ሁኔታ እንዳሻሻለ ሊመሰከርለት ይቻላል።

የሽግግሩ መንግሥት ተግቶ ቢሠራም እንኳን ይህንን ሁሉ ተግባር ካለ ግዙፉ የውጭ ርዳታ ብቻውን ሊያከናውን አይችልም። የላይቤሪያን የተኩስ አቁም ደምብ እንዲቆጣጠር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሥራ አምስት ሺህ ወታደሮች የሚኖረው ሰላም አስከባሪ ጓድ ባካባቢው ለማሠማራት ቢወስንም፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የሆነው የዚሁ ሰላም አስከባሪ ጓድ አባላት በጠቅላላ ከመጋቢት ወር በፊት ላይቤሪያ ይገባሉ ተብሎ አይጠበቅም። እስካሁን ይኸው አካባቢ ችላ የተባለበት ድርጊት፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ በአፍሪቃ ለሚከሰቱ ቀውሶች የሰጠውን ንዑሱን ትኩረት አጉልቶዋል። የላይቤሪያን ችግሮች ለማስወገድ በወቅቱ የተጀመረው ጥረት ካልተሳካ በስተቀር ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ ወደፊትም መረጋጋት እንደማይኖር ተገምቶዋል።