1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐጫሉ ሙዚቃ እና አብዮት

ረቡዕ፣ ሰኔ 24 2012

“ሐጫሉ የሚሰራቸውን አዳዲስ ሙዚቃዎች አንሰማ ይሆናል። ግን ዘላለማዊ ነው። ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገሩ፤ ትውልድን ለትግል የሚያነሳሱ፤ ሐጫሉ የቆመለትን ዓላማ ከግብ የሚያደርሱ ሥራዎችን ሰርቶ አልፏል። መሞቱን እያወቀ፤ መስዋዕትነት እንደሚከፍል እያወቀ የኖረ እና የተሰዋ ሰው ነው። ሙዚቃዎቹን ለዘልዓለም እንሰማቸዋለን” አቶ በፍቃዱ ሞረዳ

https://p.dw.com/p/3eeyP
Äthiopien | Sänger und Aktivist Haacaaluu Hundeessaa
ምስል Reuters/T. Negeri

ሐጫሉ ሙዚቃ እና አብዮት

በልጅነቱ የሙዚቃ ተሰጥዖውን ከሞረደባቸው መካከል የዳዊት መኮንን ሥራዎች ቀዳሚ እንደሆኑ ይናገር ነበር። ጊታር፣ ኪቦርድ እና ክራር ይሞካክር የነበረው ሐጫሉ በአንድ ወቅት እንደተናገረው ሰኚ ሞቲ የተባለው የመጀመሪያ የአልበም ሥራ አብዛኛው የተፃፈው በእስር በቆየባቸው አምስት አመታት ነው።

የፍቅር ሙዚቃዎችም አቀንቅኗል። ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ሙዚቃዎቹ ግን የዛሬ ስብዕናውን ገንብተዋል። ከእነዚህ መካከል “ምኑን አለሁት” ያለበት ሙዚቃ ተጠቃሽ ነው። የቀድሞው ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ “ማለን ጂራ” የሚል ርዕስ የተሰጠውን እና ከአምስት አመታት በፊት ለአድማጭ የቀረበውን ሙዚቃ “በሕይወት እስካለሁ ድረስ እንጉርጉሮዬ ይሆናል” የሚሉት ነው። አቶ በፍቃዱ እንደሚሉት ይኸ ሙዚቃ የኦሮሞን ሕዝብ ባሕል፤ የኦሮሞን ሕዝብ ስሜት እና የልብ ትርታ የገለጸበት ነው።  

ይኸ ሙዚቃ ብርቱ ፖለቲካዊ መልዕክት ያዘለ ነው። “ሰባብረው ጨርሰውኛል። ምኑን ነው ያለሁት? በመካከላችን አጥር ሰርተው፤ ድንበር ሰርተው እንድንለያይ ያደረጉን እነሱ ናቸው። እነሱ ማን እንደሆኑ እኔ አላውቅም፤ እሱ ያውቃል፤ ጣት ይቀስርባቸዋል። እንዋደድ ነበረ፤ እንፋቀር ነበረ ግን እንዳንገናኝ አደረጉን። ይላል። እዚያ ውስጥ የሚያነሳቸው ታሪካዊ፣ ባሕላዊ የሆኑ ነገሮች አሉ” ሲሉ አቶ በፍቃዱ ይዘቱን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ሐጫሉ በሥራዎቹ ጠንካራ ፖለቲካዊ መልዕክት ማስተላለፍ የጀመረው ግን ቀደም ብሎ ነው። አቶ በፍቃዱ እንዲያውም አብዮተኛ ይሉታል። ቱሉ ጃላ የሚለው ሙዚቃው ሌላ ጠንከር ያለ ይዘት ያለው ነው። “ቱላ ጃላ [ወደ አማርኛ ሲተረጎም በተራራው ግርጌ] በሚለው ዘፈኑ ዐቢይ ሆኖ ይቀነቀን የነበረው ነገር እንደዋዛ ለምትጠፋው ሕይወታችን ሮሮን መሸከም ምንድነው? የሚል ነው። ሕይወታችን የትም እንደ ዋዛ ይጠፋል ግን ሮሮን መሸከም የለብንም። ተሸናፊነትን መቀበል የለብንም የሚል መልዕክት ነው የሚያስተላልፈው” ይላሉ አቶ በፍቃዱ።

አለን!

ሐጫሉ “ጂራ” ከማለቱ በፊት በሚሊኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ያሰማው ሽለላ የአገሪቱን ፖለቲካ የነቀነቀ ነበር። በወቅቱ ባለሥልጣናቱ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ የቀጥታ ሥርጭት በተላለፈው መሰናዶ በቀረበው የሐጫሉ ሽለላ ተበሳጭተው እስከመገሰጥ ደርሰዋል። አቶ በፍቃዱ ያ ሽለላ “በራሱ መጽሐፍ ሊሆን የሚችል ነው። ልብ ኖሮት ቁጭ ብሎ የሚጽፍ ደራሲ ካለ” ብለዋል።

በዚያ መድረክ ሐጫሉ

“ሸልል ሸልል ትሉኛላችሁ፤ ተነስቼ ልሸልል ወይ?

ጥፋ ጥፋ ትሉኛላችሁ ተነስቼ ልጥፋ ወይ?

እኔስ ምኑን ሸለልኩኝ በሀሳብ ተይዣለሁ፤

ሸልሎ ያልጠገበ ወንድ ቃሊቲ እስር ቤት ነው ያለው፤

ሸልሎ ያልጠገበ ወንድ ቂሊንጦ እስር ቤት ነው ያለው፤

ሸልሎ ያልጠገበ ወንድ ከርቸሌ ታስሮ ነው ያለው፤ አምቦ ከርቸሌ ነው ያለው፤

እኔስ ምኑን ሸለልኩኝ ሀሳብ እያናወዘኝ?”

ነበር ያለው።

“ሐጫሉ ዋናው ሞቱ የተደገሰለት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው በእኔ እይታ” ብለዋል አቶ በፍቃዱ ሞረዳ። ከዚያ ጂራ የተሰኘው ሙዚቃ በሌላ ፖለቲካዊ መልዕክት ቀረበ። ይኸን ሙዚቃ “ተስፋን የፈነጠቀበት” እንደሆነ አቶ በፍቃዱ ያምናሉ።

“አለን፣ አለን፣ አለን፣ አለን ውለን ንጋት ልናይ

ሆድ አስፍቶልን አይ እኛ!

አይ እኛ! አወይ ነገር መርሳት

አወይ ነገር መርሳት፤ የእኛ ነገር

ለቁንጫ ዝላይ፣ ለትኋንም ሽሽት፣ ለአሞራም ክንፏን፤ ለአሞራም ክንፏን ለኤሊም ድንጋይ፣ እና ማን እምቢ ይላል? አለን ሁሉን ችለን አለን ሁሉን ችለን”  ሲል ጂራ የሚል ርዕስ በሰጠው ሙዚቃው ሐጫሉ ሁንዴሳ አቀንቅኗል። አቶ በፍቃዱ በ36 አመቱ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች የተገደለው ሐጫሉ ሁንዴሳ ስኬታማ ሥራዎች አበርክቷል ሲሉ ይናገራሉ።

“ሐጫሉ የሚሰራቸውን አዳዲስ ሙዚቃዎች አንሰማ ይሆናል። ግን ዘላለማዊ ነው። የሰራቸው ከበቂ በላይ ናቸው። ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገሩ፤ አሁንም ትውልድን ለትግል የሚያነሳሱ፤ ሐጫሉ የቆመለትን ዓላማ ከግብ የሚያደርሱ ሥራዎችን ሰርቶ አልፏል። መሞቱን እያወቀ፤ ዋጋ እንደሚከፍል፤ መስዋዕትነት እንደሚከፍል እያወቀ የኖረ እና የተሰዋ ሰው ነው። ሙዚቃዎቹን ለዘልዓለም እንሰማቸዋለን፤ እስካሁን የሰራቸው በቂ ናቸው” ብለዋል። 

አምቦ ተወልዶ ያደገው የ36 አመቱ ሐጫሉ ሁንዴሳ ሞት የቀሰቀሰው ተቃውሞ ቀድሞም በቅጡ መርጋት የተሳነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ አዲስ ይንጠው ይዟል። ሐጫሉ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ መገደሉ ከተሰማ በኋላ በመላው ኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ እስካሁን በትንሹ 81 ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ መንግሥት አረጋግጧል።

አቶ በፍቃዱ “ሐጫሉ በሰው ልብ ውስጥ ሐውልት ሆኗል፤ ከዚህ በኋላ የሚዘፍነውም ዘፈን ላይኖር ይችላል፤ መዝፈን የሚገባውን፤ ማስተላለፍ የሚገባውን መልዕክት አስተላልፏል። እነዚህ ሥራዎቹ በትውልድ ልብ ውስጥ ለመኖር በቂ ሐውልቶች ናቸው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። ለዚህ ዘገባ ታምራት ዲንሳ አስተዋጽዖ አበርክቷል።

እሸቴ በቀለ