1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሒሩት አባትዋ ማን ነዉ?

ዓርብ፣ ጥቅምት 13 2013

በፊልሙ ዉስጥ ዋናዉን ገፀ-ባህሪ ተላብሰዉ የተዉኑት እና ወደ  49 ዓመት ግድም በጀርመን ይኖሩ የነበሩት አቶ አለማየሁ አሰፋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀመርያዉ የሆነዉ "ሒሩት አባትዋ ማነዉ" የተባለዉ ፊልም የተሰራዉ በወቅቱ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተወሰደ ብድር ነበር።

https://p.dw.com/p/3kKZa
Alemayehu Assefa
ምስል privat

የሒሩት አባቷ ማነው ፊልም ተዋናይ ሕልፈት

በንጉሰ ነገስቱ ዘመን እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ 1957 ዓ.ም ተሰርቶ በዝያዉ  በ 1957 ዓመት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ቤት ለእይታ ስለበቃዉ እና ሒሩት አባትዋ ማነዉ ስለተባለዉ የኢትዮጵያ የመጀመርያ ፊልም አንጋፋዉ ከያኒ የጥበብ ሰዉ ጋሽ ደበበ እሸቱ ያስታዉሳል ፊልሙንም አይቶታል። በፊልሙ ዉስጥ ዋናዉን ገፀ-ባህሪ ተላብሰዉ የተዉኑት እና ወደ  49 ዓመት ግድም በጀርመን ይኖሩ የነበሩት አቶ አለማየሁ አሰፋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀመርያዉ የሆነዉ ሒሩት አባትዋ ማነዉ የተባለዉ ፊልም ያዘጋጀዉ (National Film and Publicity) የተባለ ድርጅት በወቅቱ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ዉል ገብቶ ለፊልሙ መስርያ የሚሆን ከባንኩ የብድር አገልግሎት እንዳገኘም ተመልክቶአል።  በዝያን ጊዜለፊልሙ ማሰርያ ከልማት ባንክ  200 ሺህ ብድር እንደተገኘም ታሪክ ያሳያል። ይሁንና ፊልሙን ያዘጋጀዉ  (National Film and Publicity) የተባለዉ ድርጅት ለፊልሙ ማሰርያ እንዲሆነዉ ከባንክ የወሰደዉን ብድር መክፈል ባለመቻሉ ሒሩት አባትዋ ማነዉ የተባለዉ ፊልም ባለዕዳ ሆኖ በባንኩ ተይዞ መቆየቱ ነዉ የሚነገረዉ።

በሰሜናዊ ጀርመን በምትገኘዉ የወደብ ከተማ ሃምቡርግ ለረጅም ዓመታት የኖሩት የመጀመርያዉ የኢትዮጵያ የፊልም ተዋናይ አቶ አለማየሁ አሰፋ፤ በፊልሙ ዉስጥ ጉግሳ የተባለ ባህሪን ተላብሰዉ ታሪካዊ ፊልም መስራታቸዉ የሃገራቸዉን ባህል እና ቱፊትን በማስተዋወቅ እንዲሁም በሥነ- ጽሑፍ እንደሚታወቁ በጀርመንዋ ከተማ በሃምቡርግ ረዘም ላሉ ዓመታት የሚያዉቋቸዉ ጓደኞቻቸዉ ይናገራሉ።  ሒሩት አባትዋ ማነዉ በተሰኘዉ በኢትዮጵያ የመጀመርያ ፊልም መሪ ተዋንይ የነበሩት የአቶ አለማየሁ አሰፋ የቅርብ ወዳጅ አቶ ተገኝወርቅ መንግሥቴ አንዱ ናቸዉ። በጀርመን ሲኖሩ እሳቸዉም እንዲሁ  ወደ 49 ዓመታት አስቆጥረዋል።  

Alemayehu Assefa
ምስል privat

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በእዳ ተይዞ የነበረዉ ሒሩት አባትዋ ማነዉ የተሰኘዉ ፊልም ባንኩ ይህ ታሪካዊ ፊልም ሸጦ ከሚያገኘዉ ጥቅም ይልቅ ታሪካዊነቱን ጠብቆ ለሕዝብ አገልግሎት ቢዉል የተሻለ ጠቀሜታ እና ዋጋ ይኖረዋል በሚል በባንኩ የስራ አስፈጻሚዎች በኩል የፊልሙ እዳ ተሰርዞ ፊልሙ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተሰጥቶ እንደ አንድ ታሪካዊ የሕዝብ ኃብት ተጠብቆና ተይዞ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲዉል በተወሰነዉ መሰረት ሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር በተከናወነዉ ደማቅ ሥነ -ስርዓት ፊልሙን ለባህላና ቱሪዝም ሚኒስቴር በስጦታ ማስተላለፉ ተመልክቶአል። ከ50ኛ ዓመታት በላይ የሆነዉ ይህ የኢትዮጵያ የመጀመርያ ፊልም ባንኩ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ማስተላለፉ ባንኩ በማኅበራዊ ተሳትፎ ረገድ ያለዉን ጉልህ ድርሻ ያሳያል ተብሎአል። የአቶ አለማየሁ አሰፋ የረጅም ጊዜ ባልንጀራ አቶ ተገኘ ወርቅ ፤ በፊልሙ ብቻ ሳይሆን አቶ አለማየሁ በማኅበራዊ ኑሮ እንዲሁም በኪነ- ጥበቡ ዘርፍ ሁለገብ መሆናቸዉን ተናግረዋል።

ሌላዉ የሰሜናዊ ጀርመን የሃምቡርግ ከተማ ነዋሪ እና የሒሩት አባትዋ ማነዉ መሪ ተዋናይ የነበሩት የአቶ አለማየሁ አሰፋ ባልንጀራ አቶ አበበ መቼ ናቸዉ። አቶ አበበ ከአቶ አለማየሁ ጋር በጀርመንዋ ከተማ ሃምቡርግ በኢትዮጵያዉያን ማኅበር ዉስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ።

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ቤት በ 1957 ዓ.ም ለእይታ የበቃዉ ሒሩት አባትዋ ማነዉ የተሰኘዉ ፊልም ታሪኩ ከናዝሬት ተነስቶ አዲስ አበባ ከዚያም አስመራ ሚዘልቅ ፊልም መሆኑን አንዳንድ ስለ ፊልሙ የተጻፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የታሪኩ ዋና ገጸ-ባህሪ ሒሩት በናዝሬት ከተማ ከቤተሰቦችዋ ጋር የምትኖር ተማሪ ነበረች። አቶ አለማየሁ አሰፋ ጉግሳ ባህሪን ተላብሰዉ የተጫወቱ ናቸዉ ጉግሳ  በዉጭ ተምሮ የመጣ  በሞያዉ «ዘፋኝ» ሲሆን ታሪኩ በሁለቱ ወጣቶች ፍቅር ላይ ያጠነጥናል። ነጭና ጥቁር  የሆነዉ የመጀመርያዉ የኢትዮጵያ ሲኒማ ቀረፃዉ የተካሄደዉ በናዝሬት ቆቃ ደብረዘይት አዲስ አበባ እና አስመራ መሆኑም ተመልክቶአል።

በፊልሙ የጉግሳ ባህሪ ተላብሰዉ የተወኑት አቶ አለማየሁ አሰፋን በግል የሚያዉቋቸዉ  እና  በጀርመን በተለይም በበርሊን በሚገኘዉ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር ዉስጥ ንቁ ተታፊ የሆኑት አቶ በላይነህ ተሾመ ፤ ሒሩት አባትዋ ማነዉ ስለተሰኘዉ ፊልም ከአቶ አለማየሁ የሰሙትን እንዲህ ይተርካሉ።

Glück wünschen: Deutsche Redensarten | Kreuzfahrtschiff Sea Cloud II im Hafen von Hamburg
ምስል picture-alliance/blickwinkel/McPHOTO/C. Ohde

በጥቅምት በ 1940 ዓም አዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት አቶ አለማየሁ አሰፋ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን እዝያዉ አዲስ አበባ አጠናቀዉ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአየር ኃይል አብራሪ «ፓይለት» በመሆን ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል። ከዝያም ወደ ሲቪልአቭየሽን በመዛወር የበረራ ፈቃድ ሰጭ ተቋም ዉስጥ አገልግለዋል።  እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ 1957 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በተሰራዉ ፊልም መሪ ተዋናይ ሆነዉ ተጫዉተዋል። አቶ አለማየሁ ሳቅበሳቅ እና ጉብል የሚል መጽሐፍ ደራሲም ናቸዉ። በ ጎርጎረሳዉያኑ 1971 ዓ.ም ወደ ጀርመን ሃምቡርግ ከተማ በመምጣት በሃምቡርግ የወደብ አገልግሎት ለ 25 ዓመታት አገልግለዋል። የሁለት ወንዶች እና የአንዲት ሴት ልጅ አባትም ነበሩ። ለረጅም ዓመታት በሕመም አልጋላይ የነበሩት አቶ አለማየሁ አሰፋ በ 80 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ባለፈዉ ማክሰኞ ጥቅምት 3 ፤ 2013 ዓም በሃምቡርግ ከተማ ጊዜዉ የኮሮና ወረርሽኝ ያገረሸበት ቢሆንም የቀብር ሥነ-ስርዓታቸዉ ኢትዮጵያዉያን በተገኙበት በሃምቡርግ ከተማ ተፈፅሞአል። ሒሩት አባትዋ ማነዉ ስለተሰኘዉ ፊልም በጥልቀት የሚነግረን ሰዉ አላገኘንም። የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስለ ፊልሙ ማብራርያ እንዲሰጠን ያደረግነዉም ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። ይሁንና አሁንም ስለ ኢትዮጵያ የመጀመርያ ፊልም ጉዳይ የሚነግረን እንፈልጋለን። ሒሩት አባትዋ ማን ነዉ ስለተሰኘዉ ፊልም የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ማብራርያ ቢሰጠን በሌላ ዝግጅት እንመለሳለን። ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ