1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕንድ፦ ግዙፉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማራዘሟ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 8 2012

ሕንድ  የኮሮና ተሐዋሲ ስጋት በመላ ሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀደም ሲል አስነግራ በድጋሚ እንዲራዘም ባደረገችው ሕንድ ኢንዱስትሪዎች ኢንዱስትሪዎች እና የንግዱ ዘርፍ ቀስ ብሎ በጥንቃቄ እንዲጀመር ትሻለች።

https://p.dw.com/p/3atDG
Coronavirus | Indien | Kalkutta | Lockdown
ምስል DW/Prabhakar

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ ጎዳናዎች ሰው አልባ ኾነዋል

በሕንድ መጠነ ሰፊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘም የሀገሪቱ ዜጎች በተለይ በመካከለኛ እና አነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩት መጎዳታቸው ተዘግቧል። ሕንድ  የኮሮና ተሐዋሲ ስጋት በመላ ሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀደም ሲል አስነግራ በድጋሚ እንዲራዘም ባደረገችው ሕንድ ኢንዱስትሪዎች ኢንዱስትሪዎች እና የንግዱ ዘርፍ ቀስ ብሎ በጥንቃቄ እንዲጀመር ትሻለች።  

የኮሮና ተሐዋሲ ቊጥር በጨመረባት ሕንድ የተከሰተውን ምጣኔ ሐብታዊ ድቀት ለመታደግ በሚል መንግስት አንዳንድ ኢንዱስትሪዎቹ በድጋሚ ወደ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ይሻል። የሕንድ ቴሌቪዥን እንደዘገበው ከኾነ የተሽከርካሪ ኢንዱስትሪዎች እና የጨርቃጨርቊ ዘርፍ ንግድ የሀገሪቱ የኅልውና ምንጭ በመኾናቸው ሥራ ይጀምራሉ። በአንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ላይ በከፊል አንዳንዶቹ ጋ ደግሞ እጅግ ጥብቅ በኾነ የንጽህና አጠባበቅ መርኅ ነው ሥራ ይጀመራል የተባለው። በጂንዳል የንግድ ትምህርት ቤት መምህር እንደኾኑት ፕሮፌሰር ራጂሽ ቻክራባርቲ ከኾነ፦ በተለይ የመካከለኛ ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በብርቱ ተጎድተዋል።  

«አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ለሀገሪቱ የሥራ ምንጭ ዋነኛ የጀርባ አጥንት ናቸው። ስለዚህ መንግስት ቅጥር ላይ እና ድኆች በቂ ድጋፍ እንደሚያገኙ ዋስትና መስጠቱ ላይ የሚያተኩር ከኾነ፤ ያ በእርግጥ ምርጫ ሳይኾን የግድ መደረግ ያለበት ነው፤ አነስተኛ ተቋማቱን መደገፍ ይኖርበታል። መካከለኛ የንግድ ተቋማት ደግሞ ከግብር እፎይታ አንስቶ እስከ የብድር ዋስትና ድረስ ማናቸውም አይነት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። መንግሥት የገንዘብ እና የበጀት ድጋፍ ሊያቀርብ ይችላል።»

Coronavirus | Indien | Kalkutta | Lockdown
ምስል DW/Prabhakar

ከሦስት ሳምንት በፊት በመላ ሕንድ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በድጋሚ ሊራዘም እንደኾነ ተነግሯል። ጠቅላይ ሚንሥትር ናሬንድራ ሞዲ በሳምንቱ መጨረሻ ከሀገሪቱ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ጋር ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ተወያይተዋል። አንዳንድ የሀገሪቱ ግዛቶች የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭትን ለመግታት ተጨማሪ የዐሥራ አምስት ቀን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከወዲኹ ተግባራዊ እንዲኾን ወስነዋል። የካርናታካ ግዛት ርእሰ ብሔር ቡክአናኬሬ ሲዳሊንጋፓ፦

«ጠቅላይ ሚንሥትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያለአንዳች ማመንታት ለ15 ቀናት ማራዘም እንደሚገባን ነግረውናል። ከዚያ በኋላ በሒደት ለቀቅ ማድረጉ ላይ እናስብበታለን ብለውናል።»

በሕንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ ኢንዱስትሪዎች እና የንግድ ተቋማት በመዘጋታቸው በተለይ የተጎዱት የዕለት ጉርሳቸውን ተሯሩጠው ለማግኘት የሚጥሩ ምንዱባን እና የቀን ሠራተኞች ናቸው። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ወደ እየ መንደሮቻቸው ተመልሰዋል። አብዛኛዎቹ ታዲያ ወደ ገጠራማ መንደሮቹ በመቶ ኪሎ ሜትር የሚቆጠረውን መንገድ የተያያዙት በእግር ነበር። ምክንያቱ ደግሞ፦ የባቡር እና የአውቶብስ መጓጓዣ አገልግሎቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በመላ ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ ቀጥ እንዲሉ መደረጋቸው ነው። እነዚህ በርካታ ምንዱባን በኮሮና ተሐዋሲ ሳይኾን በረሐብ አለንጋ ተገርፈው እንዳይሞቱ ስጋት የገባቸው መኾኑን የድኆች ድኆችን የሚደጉመው አንድ መንግስታዊ ያልኾነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ኃላፊ ራጄሽ ኩማር ይናገራሉ።    

«በዚህም አለ በዚያ ሥራ የማይጀመር ከኾነ በብርቱ የሚጎዱት እነዚህ ድኆች ናቸው። ወይ ኹሉም ወደ ቤታቸው እስካልሄዱ ድረስ ማለት ነው። አኹን እንደሚወራው ከኾነ እርግጠኛ መኾን ባይቻልም በርካታ ነገሮች የሚያመላክቱት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገና ሙሉ ግንቦት ወርንም እንደሚያካትት ነው። ያ ከኾነ መንግስት ለድኆች የጤንነት ዋስትና፣ የኑሮ ድጎማ እና ሌሎች አስፈላጊ ርዳታዋችን ለማቅረብ ርግጠኛ መኾን ይገባዋል።»     

Indien Neu Delhi Yamuna Fluss sauber nach Lockdown
ምስል AFP/M. Sharma

የሕንድ መዲና ዴልሂ ውስጥ ከቆዩት የቀን ሠራተኞች መካከል ካራን ኩማር ይገኝበታል። ቀሪ የቀን አበሉን እስኪቀበል ድረስ መዲናዪቱ ውስጥ ለመቆየት ቢወስንም ቤተሰቦች ግን በአስቸኳይ ወደመንደሩ እንዲመለስ እየወተወቱት መኾኑን ይናገራል።

«ባለቤቴ በቃ ኹሉንም ተውና  በፍጥነት ወደቤት ተመለስ እያለችኝ ነው። ገንዘቡን ተውና ወደ ቤተሰብህ ተመለስ። በቃ ብንጠማም ብንራብም ቢያንስ ተርበን አንድ ላይ መሞት ካለብንም አንድ ላይ ነው መኾን ያለብን ነው የምትለው።»

በግብርና ሞያ የሚተዳደረው ፓራስ ናታህም የቀን ሥራ ፍለጋ ዴልሂ መጥቶ መውጣት ካቃታቸው አንዱ ነው።

«በመንደራችን አኹን የመኸር ወቅት ነው። እዚህ የመጣነው ትንሽ ገንዘብ ለመሰብሰብ ለጊዜው ነበር። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ወደቤታችን መመለስ አንችልም። ማሳው ላይ ሰብሉን ካላጨድን ቤተሰቦቻችን የሚላስ የሚቀመስ ያጣሉ።»  

በሕንድ የኮሮና ተሐዋሲ የሚጠቃው እና የሚሞተው ሰው ቊጥር እየጨመረ ነው። እስከ ትናንት ድረስ ከዐስር ሺህ አምስት መቶ በላይ ሰዎች በተሐዋሲው ሲጠቊ፤ ከ350 በላይ ደግሞ ኮቪድ 19 ባስከተለባቸው ብርቱ ኅመም የተነሳ ሞተዋል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ