1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕይወት በዶኔትስክ መጠለያ

ማክሰኞ፣ የካቲት 24 2007

የዩክሬን መንግሥትና አማፅያን ከሁለት ሳምንት በፊት ሚንስክ ቤላሩስ ውስጥ የተስማሙበት የተኩስ አቁም አሁንም መጣሱ ቀጥሏል ። ከስምምነቱ በኋላ በሩስያ ይደገፋሉ የሚባሉት አማፅያን በአንዳንድ የምሥራቅ ዩክሬን ከተሞች ይዞታቸውን እያጠናከሩ ነው ። ለመሆኑ በምሥራቅ ዩክሬን ከተሞች ህይወት ምን ይመስላል ?

https://p.dw.com/p/1Ek2t
Ukraine - Schutzräume in Donetsk
ምስል DW/G. Koerkamp

ምሥራቅ ዩክሬን የምትገኘዋ ዶኔትስክ በኢንዱስትሪዎችዋና በዓለም ዓቀፍ የእግር ኳስ ክለብዋ ዝናዋ የናኘ ከተማ ነበረች ። የዩክሬን ዋነኛ የኤኮኖሚ የኢንዱስትሪና የሳይንስ ማዕከል የነበረችው ይህች ከተማ እስከ 1 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ይኖርባት ነበር ። የከሰል ድንጋይና የብረት ኢንዱስትሪ ማዕከል የነበረችው ዶኔትስክ ከ6 ዓመት በፊት በተገነባው ከአውሮፓ ትልቁ በሚባለው የእግር ኳስ ስታድዮሟም ትታወቅ ነበር ። ካለፈው ዓመት ሚያዚያ ወዲህ የዶኔትስክ ታሪክ ተቀይሯል ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ራሱን የዶኔትስክ ህዝቦች ሪፐብሊክ ብሎ በሚጠራው የአማፅያን ቡድን ስር የምትተዳደረው ዶኔትስክ የምሥራቅ ዩክሬን ዋነኛ የውጊያ ማዕከል ናት ። በውጊያው ታዋቂው አውሮፕላን ማረፊያዋ እንዳልነበረ ሆኗል ። ግንባታው425 ሚሊዮን ዶላር የፈጀው የዶኔትስኩ ስታድዮም ዛሬ ወደ ጦር መሣሪያ ማከማቻና የሰብዓዊ እርዳታዎች ማከፋፈያ ማዕከልነት ተቀይሯል ። ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ከሚካሄድባት ከዚህች ከተማ ነዋሪዎች አብዛኛዎቹ ቤታቸውን ትተው መጠለያዎች ውስጥ ነው የሚኖሩት ።የዶቼቬለው ጊርት ግሩት ኮአርካምፕ በአንድ የዶኔትስክ መጠለያ ህይወት ምን እንደሚመስል ተመልክቶ ነበር ።

ዶኔትስክ ፣ቅዳሜ ምሽት ፤በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ድምፃዊት ኦልጋ ፕሪዝ ታንጎራጉራለች ። ስፍራው በከተማይቱ ጦርነት መኖሩን ለጊዜውም ቢሆን ያስረሳል ። እውነታውን ለመረዳት ግን ከምግብ ቤቱ ወጣ ማለት ብቻ ይበቃል ።

በዶኔትስክ ዳርቻ የዩክሬን ወታደሮችና አማፅያን ቀን ተሌትየሚያካሂዱት ከባድ ውጊያ የመድፍ ና የሚሳይል ድብደባ መሃል ዶኔትስክ ድረስ ይሰማል ።አልፎ አልፎ ማዕከላዊ ዶኔትስክም ጥቃት ይደርስባታል ። በቅርቡ በከተማዋ ማዕከል አቅራቢያ የሚገኝ አንድ የአውቶብስ ፌርማታ ተመቶ ሰዎች ተገድለዋል ።ምንም እንኳን በዶኔትስክ የከባድ መሣሪያ ድብደባ ባይቆምም አንዳንዶች በየጎዳናው ሲንቀሳቀሱ ቲያትር ቤቶች ሲሄዱ ካልሚዩስ በተባለው ወንዝ ላይ የበረዶ ሸርተቴ ሲጫወቱም ያታያል ። ብዙዎች ግን ድብደባው ባልቆመባት በዶኔትስክ ይህን ለማድረግ አይደፍሩም ።ከከተማዋ ነዋሪዎች አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል በመጠለያዎች ውስጥ ተሸሽገዋል ። ከመጠለያዎቹ ትልቁ ፔትሮቭስሊ በተባለ ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ የቀድሞ የባህል ማዕከል ምድር ቤት ነው ። በሰላሙ ጊዜ ስፍራው የሙዚቃ ድግሶችና ሌሎችም ባህላዊ እንቅስቃሴዎች የሚቀርቡበት ማዕከል ነበር ።ከወራት ወዲህ ግን በማዕከሉ ምድር ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠልለዋል ።ኤልዮኖራ ትስቬትኮቫ ከነሐሴ አንስቶ በዚህ መጠለያ ውስጥ ነው ያለችው ።

Ukraine - Schutzräume in Donetsk
ምስል DW/G. Koerkamp

«ወደ ቤታችን የምንሄደው መታጠብ ስንፈልግ ብቻ ነው ። በተረፈ በቋሚነት እዚህ ነው ያለነው ።ትናንት ለሊት ከባድ ድብደባ ነበር ። በዚህ ህንፃ በአንደኛው ወገን ያሉት መስኮቶች በሙሉ ተሰባብረዋል። በቀንም ይሁን በማታ ድብደባ ሳይካሄድ የቀረበት ጊዜ የለም ።ማንነው ደብዳቢው ? አዎ ዩክሬኖች ናቸው ።»

በመጠለያው ውስጥ ከሚኖሩት በብዙ መቶዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች 70 ው ህፃናት ናቸው ። እነዚህ ህፃናት ትምህርት ቤት አይሄዱም ወደ ውጭ የሚወጡት እንኳን ከስንት አንዴ ነው ።የሚያገኙት ምግብ ጥቂት ከመሆኑም በላይ ጥራቱም ዝቅተኛ ነው ።የብዙዎቹ ተሞክሮ እጅግ አሳዛኝ ነው ።መጠለያው ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ወደ ውጭ መውጣት ይፈራሉ ።ደህንነታቸው አስተማማኝ ሊሆን ወደ ሚችልበት ሌላ አካባቢ ለምን እንደማይሄዱ ሲጠየቁ እንደ 70 ዓመትዋ ዚና የሲኮቫ ያሉት ወዴት እንደሚሄዱ እንኳን እንደማያውቁ ነው የሚናገሩት ።

Ukraine - Schutzräume in Donetsk
ምስል DW/G. Koerkamp

«ባለቤቴ በማዕድን ማውጫ ውስጥ ለ40 ዓመታት ሰርቷል ።ባለፈው ነሐሴ በልብ ህመም አረፈ ። ብቻየን ቤቴ ውስጥ መቆየት ስለፈራሁ ነው እዚህ የመጣሁት።ድብደባ ሲጀመር ሮጬ እዚህ ቦታ መድረስ አለብኝ ።ይህን ማድረግ መቻል አለመቻሌን እርግጠኛ መሆን አልችልም ። ቤታቸው መቆየትን የመረጡ ብዙ ሰዎች አሉ ።ብዙዎችም አካባቢውን ለቀው ሄደዋል ። እኔ ደግሞ እዚህ ቀርቻለሁ ።ምክንያቱም የት እንደምሄድ እንኳን አላውቅም ። ሴት ልጄ ማሪንካ አካባቢ ነው የምትኖረው እዚያ ደግሞ ከዚህ የባሰ ድብደባ ነው የሚካሄደው ።»

መሄጃ አጥተው አቅምም አንሷቸው መጠለያው የሚገኙት ዚና የሲኮቫ እንደሚሉት የሚኖሩት በተጠለሉበት ቦታ በሚሰጥ እርዳታ ነው ።ይህ እርዳታ ግን ለሁሉም የሚሰጥ አይደለም ።

«ድብደባውን ትሰማለህ ።ድብደባው ቀን ከሌት ይካሄዳል ።መውጣት አልቻልንም ። በአቅራቢያችን አንድ ትንሽ ሱቅ አለ ። በሩጫ ሄደን ገዝተን እንመለሳን ።ቢያንስ ገንዘብ ያላቸው ይገዛሉ ።እኛ ግን ገንዘብ የለንም ።እኔ ጥቂት ሰብዓዊ እርዳታ አገኛለሁ ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እዚህ ነበር የሚሰጠኝ ።አሁን ግን ማከፋፈያው ወደ ዛስያድኮ ማዕድን ማውጫ ተዛውሯል ። ዛስያድኮ ደግሞ ከዚህ ሩቅ ነው ። እንዴት አድርጌ እዚያ እሄዳለሁ ።ባሻገር ያለችው ሴት ወጣት ናት ። ምንም እርዳታ አታገኝም ።ግን ያለንን እንካፈላለን ።»

Ukraine - Schutzräume in Donetsk
ምስል DW/G. Koerkamp

የ70 ዓመትዋ አዛውንት ያመለከቱት ወደ ኤልዮኖራ ትስቬትኮቫ ነው ። ትስቬትኮቫ እንደተናገረችው እርስዋና ሌሎች በመጠለያው ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ያገኙትን ተካፍለው ነው የሚበሉት።

«ሰዉ በቤቱ ውስጥ የነበረው ሁሉ ተሟጧል ።እዚህ እንዲብቃቃ አድርገን በአንድ ላይ አብስለን አንድ ላይ ነው የምንበላው ። »

የኤልዮኖራ ትስቬትኮቫ ልጅ የሶስት ዓመትዋ ሊልያም መጠለያ ውስጥ ካሉት ህፃናት አንዷ ናት ። የኤልዮኖራ ባለቤት የሊልያ አባት ቤታቸው ውስጥ መቆየቱን መርጧል ። ከባድ ድብደባ ከተካሄደ ሮጦ ወደ መጠለያው መምጣት ይችላል በሚል እምነት ቤቱ ነው ያለው ።

«ድብደባ ቢካሄድ እኔ እዚህ ከልጄ ጋር ደህንነቴ የሚጠበቅበት ቦታ ነው ያለሁት።ባለቤቴ ረዥም ቀጭን ነው ።በፍጥነት እዚህ ሊደርስ ይችላል ።ራሱን ማዳን እንደሚችል ያውቃል ። አንድ ነገር ቢደርስ ግን ሶስታችንን ማዳን አይችልም ።»

። በመጠለያው ምድር ቤት ውስጥ የሚውሉና የሚያድሩት ልጆች ትምሕርት ቤት መሄድ አይችሉም ።ከቀድሞው የባህል ማዕከል ከአሁኑ መጠለያ አጠገብ የሚገኘው ትምሕርት ቤት በቦምብ ተመቶ ጣሪያው ክፉኛ ተጎድቷል ። በአካባቢው የነበረው አፀደ ህፃናትም ጥር አጋማሽ ላይ እንዳልነበረ ሆኗል ።በዚህ የተነሳም ወላጆች ለልጆቻቸው ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ይሞክራሉ ።

ላዩቦቭ ቮዬቭቺክ ቤቷ ውስጥ ያሉትን ውሾችዋን መግባ ልብስም አጥባ ተመልሳ ወደ መጠለያው መጥታለች ።ልክ መጠለያው እንደገባች ድብደባው ቀጠለ ።እንደ አብዛኛዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ቮዬቭቺክም ለጦርነቱ ተጠያቂ የምታደርገው የክየቭን መንግሥት ነው ።የአማፅያኑና የሩስያ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዋና ከተማይቱ ሥልጣን የያዙት የፋሽሽት ቡድኖች ናቸው የሚሉትን ታምናለች ።

Ukraine Separatisten Panzer bei Donetzk
ምስል Reuters/B. Ratner

«የልጆቻችንን ህይወት በአጭሩ ቀጥፈዋል ።በርግጥ የኛም ተዋጊዎች እየደበደቡ ነው ለምሳሌ ድባልትሴቭን ።ግን ምንማድረግ ትችላለህ ።ይህ ጦርነት ነው ።ዶኔትስክ ውብ ከተማ ነበረች ። ከአውሮፓ እጅግ ዘመናይ የአውሮፕላን ማረፊያ ነበረን ። አሁን ከተማችንን ምን እንደሆነች ተመልከቱ ? ከተማችንን ምን አደረጓት?

መጠለያው ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች የሚንስኩ ስምምነት ላይ እምነት የላቸውም ። ከዚያም በላይ በቮዬቭቺክ አስተሳሰብ ጦርነቱ ቢያበቃ እንኳን የዶኔትስክ ህዝብ ከተቀረው ዩክሬናዊ ጋር አብሮ መኖር መቻሉ ያጠራጥራል ። ቮዮቭቺክ የክየቭ መንግሥት ምሥራቅ ዩክሬንን የሚገኙትን ህዝቦች እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚቆጥር ያህል ነው የሚሰማት ።

«እርቀ ሰላም ምናልባት ይቻል ይሆናል ። ሆኖም ከዩክሬን ጋር አንድ ላይ በነበርንበት ጊዜ እንኳን ሰው እንዳልሆንን ባሪያዎች እያሉ ነበር የሚጠሩን ። እናም ጦርነቱ ሲያበቃ ምን ሊሆን ይችላል ?»

ቮዬቭቺክ እንዳለችው ጥላቻው አሳሳቢ ነው ። ሆኖም አሁን ከዚያ በላይ የሚያሳስበው የውጊያው አለመቆም ነው ። ትናንት የወጣው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዘገባ በምሥራቅ ዩክሬኑ ውጊያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ6 ሺህ መብለጡን አስታውቋል ። ኮሚሽኑ ሁሉም ወገኖች የሚኒስኩን ስምምነት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ